1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቀረቡ ቅሬታዎች ውስጥ 95 በመቶው ተፈትቷል ተብሏል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 18 2009

በአዲስ አበባ መርካቶ የተወሰኑ ሱቆች ዛሬ ለሁለተኛ ቀን ተዘግተው ውለዋል፡፡ የንግድ ተቋማቱ ባለቤቶች መደብሮቻቸውን የዘጉት መንግሥት አዲስ የጣለዉን የቀን ገቢ ግምት በመቃወም እንደሆነ የአካባቢው ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ ሱቃቸውን ከዘጉት ጋር መነጋገሩን እና መግባባት ላይ መደረሱን አሳውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/2h8Ly
20.06.2013 DW Online Karten Basis Aethiopien spanisch

Shops shutdown in Merkato for 2nd day - MP3-Stereo

በአዲስ አበባ በከፊል የመርካቶ አካባቢዎች ተጀምሮ የነበረው ሱቆችን የመዝጋት አድማ ዛሬም በተወሰኑ ቦታዎች ቀጥሎ መዋሉን ነጋዴዎች ለዶይቸ ቬሌ ገለጹ፡፡ ዛሬ ተዘግተው የዋሉት ሱቆች በአስፋወሰን ሆቴል አቅራቢያ፣ ሰባተኛ እና ጎጃም በረንዳ አካባቢ የሚገኙ እንደሆኑ ነጋዴዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አንድ ነጋዴ በአካባቢያቸው የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፡፡ 

“በተለምዶ አስፋ ወሰን ወይም አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ያሉ አክሲዮን ማህበራት ሙሉ ለሙሉ አዲሱን የገቢ ግምት በማስመልከት ዘግተዋል፡፡ እኛ ግምታቸን ባይሰጠንም የተሰጣቸው ሰዎች እኛ ጋር መጥተው መገበያየት ስላልቻሉ ስራችንም ስለተበላሸ በዚያ ምክንያት ነው የዘጋነው ብለዋል፡፡ አስገድደው ለማስከፈት ሞክረው ነበር ያም የተሳካላቸው አይመስለኝም፡፡ የቀበሌ ሱቆች ግን እናሽጋለን ብለው በማስፈራራት የተወሰኑ ሱቆች ተከፍተዋል” ይላሉ፡፡ 

እኚሁ ነጋዴ እንደተናገሩት ትናንት ሱቃቸውን የዘጉት አብዛኞቹ በደረጃ “ሐ” የተመዘገቡ እና የቀን ገቢ ግምታቸውን ያወቁ ነበሩ፡፡ ዛሬ ተቃውሞውን የተቀላቀሉት ግን አስመጪዎች እና ትላልቅ ሱቆች ናቸው፡፡ ከውሳኔያቸውንም የደረሱት ከአነስተኛ ንግድ ተቋማት ባለቤቶች ጋር በአጋርነት ለመቆም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ “የተወሰኑ ቦታዎች የቀን ገቢ ግምት ደርሷቸው ነበር፡፡ የተወሰኑት ደግሞ አልደረሳቸውም ነበር፡፡ ትላንትና የደረሳቸው ሰዎች ሲዘጉ ዛሬ ደግሞ እኛ አነርሱን ልናግዝ ይገባል ብለው ዘግተዋል” ሲሉ ዛሬ በአድማው የተሳተፉ ነጋዴዎች ምክንያት አብራርተዋል፡፡ 

የዛሬውን አድማው ያስተባበሩት ሰዎች ማንነት በግልጽ ባይታወቅም ተቃውሞው ግን ለሁለት እና ሶስት ቀን የመቀጠል ሀሳብ እንዳለ ነጋዴው ገልጸዋል፡፡ ሌላኛው ነጋዴም የንግድ ተቋማት የመዝጋት አድማው ለሁለት ቀናት እንደሚቀጥል መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስራቸውን በሚያከናውኑባቸው ቦታዎች ያዩትን እንዲህ ይገልጹታል፡፡ 

“መርካቶ የተወሰኑ ቦታዎች ዝግ ነበሩ፡፡ ሰባተኛ አካባቢ የኤሌክትሮኒክስ መሸጫ ቤቶች ተዘግተው ነበር፡፡ አስመጪዎች፣ ወንበር እና የመሳሰሉትን የሚሸጡ አካባቢ የተዘጉ ሱዎች ነበሩ፡፡ የተዘጋ ሆቴልም ነበር፡፡ ትላንት እና ዛሬ ርኆቦት ሆቴል አካባቢ መደዳውን ዝግ ሆኖ ነበር የዋለው፡፡ ጎጃም በረንዳ ነበር የጀመረው፡፡ እንደገና ደግሞ ወደ ልደታ የሚወስደው ወደ ሰባተኛ መውረጃ፣ ወደ አብነት አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ዝግ ነበር” ሲሉ በዛሬ ውሏቸው ያስተዋሉትን አጋርተዋል፡፡

ሁለቱም ነጋዴዎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ፖሊሶች ሱቆቻቸውን የዘጉ ሰዎችን እንዲከፍቱ ሲያስገድዱ እና ለማሸግም ሲያስጠንቅቁ እንደነበር መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ የተወሰኑ ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን በገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ የታክስ ፕሮግራም እና ልማት ስራዎች ኃላፊ ወይዘሮ ነጻነት አበራ ይቀበላሉ፡፡ ሆኖም ከባለቤቶቹ ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ በመደረሱ ሱቃቸውን ከፍተዋል ይላሉ፡፡ 

“በእኛ በኩል መርካቶን አይተነዋል፡፡ በእርግጥ የተወሰኑ ቦታዎች የተዘጉ እንዳለ አይተናል፡፡ የዘጉትን ጠርተን አወያይተናቸዋል፡፡ መከፈት እንዳለበትም የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰናል” ብለዋል ኃላፊዋ፡፡ 

ወይዘሮ ነጻነት መስሪያ ቤታቸው የቀን ገቢ ግምቱን መረጃ በደረጃ “ሐ” ለተመዘገቡ ዝቅተኛ የግብር ከፋዮች ማሰራጨቱን አስታውሰዋል፡፡ ከቀረቡላቸው ቅሬታዎች ውስጥ 95 በመቶውን መፍታታቸውንም ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ የቀሩትን ቅሬታዎችም በቀጣይ ሁለት ቀናት ውስጥ እንደሚጨርሱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህ ውጭ ስለሆኑ የግብር ከፋዮች ደግሞ ተከታዩን ብለዋል፡፡ 

“ቀሪው እንግዲህ የደረጃ ለውጥ ያመጡ የደረጃ  ‘ሀ’ እና ‘ለ’ ግምት ያረፈባቸው ናቸው፡፡ እነርሱን ደግሞ ቀጥሎ ነው ቅሬታውን የምናየው፡፡ ስለዚህ አሁን ዘጉ የሚባሉት የደረጃ “ሐ” ሳይሆን የደረጃ ለውጥ ያመጡ፣ ጭራሽም ያልተገመተላቸው [ናቸው]፡፡ በዚህ ግምት ስርዓት ጭምር የማይታዩ አስመጪዎችም ጭምር ነው የዘጉት፡፡ ስለዚህ ይሄ ከግብር በዛብኝ እና አልበዛብኝ ጋራ በቀጥታ ይይዛል የሚል እምነት የለኝም፡፡”

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ