1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሊቢያ ላይ የሚደረገዉ ድብደባና ኔቶ

ዓርብ፣ መጋቢት 16 2003

አንካራ ላይ በሚንስትሮች፥ ብራስልስ ደግሞ በአምባሳደሮች ደረጃ ዉይይቱ በሚደረግበት መሐል የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተን የፈረንሳይ፥የብሪታንያና የቱርክ መሪዎች እንዲስማሙ በስልክ አግባብተዋቸዉ ነበር

https://p.dw.com/p/RCeD
የኔቶ አባላት ባንዲራምስል AP

ምዕራባዉያን ሐገራት በሊቢያ ላይ የሚፈፅሙትን ድብደባ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንዲመራዉ የድርጅቱ አባላት ተስማሙ።ድብደባዉን ኔቶ ይምራዉ የሚለዉ ሐሳብ ድብደባዉን በጀመረችዉ በፈረንሳይና የድብደባዉን ኢላማ በምትቃወመዉ ቱርክ መካከል በተፈጠረዉ ልዩነት ምክንያት እስከትናንት ድረስ አባል ሐገራትን ሲያወዛግብ ነበር። ትናንት ግን በዩናይትድ ስቴትስ ግፊት የኔቶ አባላት ልዩነታቸዉን አስወግደዋል።በስምምነቱ መሠረት ከመጪዉ እሁድ ጀምሮ ኔቶ የድብደባዉን የአዛዥነት ሥልጣን ይረከባል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «የበረራ እግድ» ያለዉን ማዕቀብ እንዲጥል ከማርቀቅ እስከ ማፀደቅ በግንባር ቀደምትነት የባተለችዉ ፈረንሳይ ሰሜን አፍሪቃዊቷን ሐገር የሚያጋየዉን ድብደባ ለመጀርም የቀደማት አልነበረም።ይሁንና የሚሳዬል፥ የመርከብ፥ አዉሮፕላን ጠንካራ ጡንቻ የሚጠይቀዉ ዘመቻ ከዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ ፍቃድና ተሳትፎ ዉጪ በርግጥ የሚታሰብ አልነበረም።

ዘጠነኛ አመቱን ያጋመሰዉ የአፍቃኒስታኑ ጦርነት የተጫጫናት፥ስምንት አመት ከዘለቀዉ የኢራቅ ወረራ በቅጡ ያላገገመችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ከሰብአዊ፥ ምጣኔ ሐብታዊ ኪሳራ ባለፍ በሁለቱ ሙስሊም ሐገራት ጦርነት ምክንያት የጠፋዉ ስሟ በሰወስተኛ ሙስሊም ሐገር ድብደባ ይጎድፋል ብላ ትሰጋለች።በዚሕም ሰበብ ዋሽንግተን የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መንግሥት ጦርን ለመደምሰስ ባለመዉ ድብደባ፥ ድብደባዉን አጥብቃ ከፈለገችዉ ከፓሪስ እኩል ምናልባትም ይበልጥ ብትካፈልም የደብዳቢዉ ጦር አዛዥ ሆና መቀጠሉን አልፈለገችዉም።

No Flash Italien NATO Libyen
ኔቶ የሚረከበዉ ሐይልምስል AP

ድብደባዉን ኔቶ ይምራዉ ነዉ-የዋሽንግተኖች አቋም።ፈረንሳይ በፋንታዋ ብሪታንያን አሳድማ የበላይነቱን እንደያዘች መቀጠሉን እንጂ ለኔቶ ሙሉ በሙሉ አሳልፎ መስጠቱን አትፈልገዉም ነበር። ሌላዋ የኔቶ ነባር አባል ቱርክ ደግሞ በሊቢያ ላይ የሚፈፀመዉ ድብደባ የሊቢያን ጦር ሐይል ከማጥፋት አልፎ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት፥ አካል ንብረትና የመሠረተ ልማት አዉታርን ማዉደሙን ትቃወማለች።

የአንካራ ባለሥልጣናት «ኔቶ ደብዳቢዉን ጦር ማዘዙን ይዘዝ የሚያዘዉ ድብደባ ግን በጦር ሐይል ላይ ብቻ ያነጣጥር አይነት» ነበር የሚሉት።ከድብደባዉ እኩል ስድስት ቀን ያወዛገበዉ ልዩነት የኔቶ ዋና ፀሐፊ አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን እንዳስታወቁት ትናንት ተወግዷል።

«የኔቶ ተሻራኪዎች በሊቢያ ላይ የተጣለዉን የበረራ እገዳ ለማስከበር ተስማምተዋል።የምንወስደዉ እርምጃ ሠላማዊ ሰዎችን ከቃዳፊ ሥርዓት ጥቃት ለመከላከል የሚደረገዉ ሰፊ ዘመቻ አካል ነዉ።ከአካባቢዉ ወዳጆቻችን ጋር በቅርብ እንተባበራለን።አስተዋፅዋቸዉንም እንቀበላለን።»

ልዩነቱን ለማስወገድ ላክሰንበርግ፥ ብራሳልስ፥ ፓሪስ የተደረገዉ ዉይይት ለትናንቱ ዉጤት የበቃዉ ግን አነሰም በዛ በዩናይትድ ስቴትስ ግፊትና ጫና ነዉ።ትናንት አንካራ ላይ በሚንስትሮች፥ ብራስልስ ደግሞ በአምባሳደሮች ደረጃ ዉይይቱ በሚደረግበት መሐል የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተን የፈረንሳይ፥የብሪታንያና የቱርክ መሪዎች እንዲስማሙ በስልክ አግባብተዋቸዉ ነበር።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ ግን አዲስ ከተደረሰዉ ስምምነት ይልቅ እስካሁን በተገኘዉ ዉጤት መርካታቸዉን ነዉ ለአዉሮጳ ሕብረት አቻዎቻቸዉ ትናንት የነገሩት።
«እስቡት፥ እንዲያዉ እስኪ አስቡት ጥምረታችን ቤንጋዚ ላይ ዝም ብሎ ቢሆን ኖሩ ሕዝብ ይጨፈጨፍ ነበር።እዚሕ የምንገኘዉ ታሪካዊ መርሆችን ለማስፈፀም ነዉ።ሕዝብን ከጥቃት ለመከላከል።»

በዚሕም ብሎ በዚያ ዉዝግቡ መወገዱ ለኔቶ አባላት በጣሙን ለዩናይድ ስቴትስ እፎይታ አይነት ነዉ።ራስሙስን የአካባቢዉ ወዳጆቻችን ያሏቸዉ እንደ ተባበሩት አርብ ኤምሬቶችና ቀጠር ያሉ የአረብ ሐገራት አቅማቸዉ «እዚያሕ ግባ» የሚባል ባይሆንም በድብደባዉ ለመሳተፍ መፍቀዳቸዉ ደግሞ ዋሽንግተኖች ስማቸዉን ለመጠበቅ ታላቅ ደስታ ነዉ። «የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጥምረቱን እንደሚቀየጡና የሊቢያን ሲቢል ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል የሚደረገዉን ጥረት የሚያግዙ አዉሮፕላኖች እንደሚልኩ አስታዉቀዋል።ይሕን ጠቃሚ እርምጃ በደስታ እንቀበለዋለን።»

Belgien NATO Generalsekretär Anders Fogh Rasmussen in Brüssel
ዋና ፀሐፊ ራስሙስንምስል dapd

አሉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ