1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀናት የቀሩት የኬንያ ምርጫ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10 2000

ከጥቂት ቀናት በኋላ በኬንያ ምክር ቤታዊና ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች እንደሚጠቁሙት በፕሬዝደንት ሙዋይ ኪባኪና በፖለቲካ ተቃዋሚያቸዉ በራይላ ኦዲንጋ መካከል ጠንከር ያለ ፉክክር እየታየነዉ። በኢንተርኔት ድረ ገፅ ሳይቀር ነዉ ቅስቀሳዉ።

https://p.dw.com/p/E0a1
ፕሬዝደንት ሙዋይ ኪባኪ
ፕሬዝደንት ሙዋይ ኪባኪምስል AP

የድረ ገፁን መገኛ ዝርዝር በመፃፍ ቱዌባ ዲዋኒ በቀላሉ የኬንያን የምርጫ ፉክክፍ ትከታተላለች። ከትዉልድ አገሯ 6,000 ኪሎ ሜትር ርቃ ብትገኝም የ34 ዓመቷ የዶክትሬት ተማሪ እዚህ ቦን ከተማ በሚገኘዉ የተማሪዎች መኖሪያ ክፍሏ ባላት የኢንተርኔት መረብ ተጠቅማ ኬንያን ትቃኛለች። በርግጥ በምርጫዉ ለመሳተፍ እጅግ ሩቅ ናት። ያም ሆኖ የሟይ ኪባኪን የኢንተርኔት ድረ ገፅ በመክፈት የፈለገችዉን ማዳመጥ አልተሳናትም።


«በዚህ በዕረፍት ቀን ስለእቅዳቸዉ ከሰዎች ጋ ሲነጋገሩ ስከታተል ኬንያ ቴሊቪዥን የምመለከት ወይም ናይሮቢ ያለሁ ዓይነት ስሜት ነዉ የሚሰማኝ።»


ድህነትን በመዋጋት ረገድ ኪባኪ ለህዝቡ በምርጫዉ ወቅት የገቡት ቃል ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ድረስ ያለዉን የትምህርት ዘመን ከክፍያ ነፃ እንደሚያደርጉና ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች ለሆኑ ህፃናት ደግሞ ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ይጠቁማል። በፖለቲካ ጨዋታዉ እነዚህ በኢንተርኔት በቀጥታ የሚያገለግሉ ድረ ገፆች በርግጥም ተጨማሪ ጥቅም ይኖራቸዋል። ይህም ለኪባኪ እንደስኬት ተቆጥሯል። የመረጡት የመቀስቀሻ መንገድም እንደ ቱዌባ ዲዋኒ ያሉ ወጣት መራጮችን በተለየ መንገድ የሚደርሱበት ስልት መሆኑ እየታየ ነዉ።


«የምርጫ ቅስቀሳዉ ጉዳይ ነዉ፤ የማሸነፍ ነገር ነዉ፤ ህዝብ ሊያገኘዉ በሚችል መልኩ ግልፅ ነዉ። በኬንያ ምናልባት ወጣቱ ሊመርጥ የሚችል ትልቁ ቡድን ነዉ ማለት ይቻላል። እሱ ጋ ለመድረስ እየጣሩ ነዉ፤ በሚግባባበት ቋንቋ ሊያነጋግሩት ኦክረዋል፤ ሊሰማዉ የሚፈልገዉን ሂፕ እያሰሙት ነዉ፤ ስማዉ። ዜማዉ ቀልብ የሚስብ ነዉ፤ ሊያስደንሰዉ የሚችል ዓይነት።»


በርግጥ በኬንያ 34ሚሊዮን ኗሪ ቢኖርም ኢንተርኔት ተጠቃሚዉ ከሶስት ሚሊዮን አይበልጥም። ዋናዉ ግብ ግን አንድ የተለየ ቡድን ላይ ታልሟል። ወጣቱ! የትምህርት ነፃ መሆን በተለይ መማር የፈለገ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሁለተኛ ደረጃምሆነ ዩኒቨርሲቲን እንዳለመ ለሚኖረዉ የአገሪቱ ወጣት ታላቅ ማማለያ ዕቅድ ይመስላል። ሆኖም ምን ያህሉ የምርጫ ቅስቀሳዉን በኢንተርኔት ይከታተላል? አነጋጋሪ ይሆናል። የኢንተርኔት አገልግሎቱም ቢሆን አዝጋሚ ከሚባሉት የሚሻል አይደለም። ወደአንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ኬንያዉያን ከአገራቸዉ ዉጪ ይኖራሉ። ከዉጪ ሆነዉ የመምረጥ መብት ግን የላቸዉም። ፕሮፌሰር ኮዲ ባርዝ እንደሚሉት ምንም እንኳን መምረጥ ባይችሉም ጫና የሚያሳድሩበት አቅምና ተቀባይነት አላቸዉ፤


«በሌላዉ ዓለም የሚገኙ ኬንያዉያን በአገር ዉስጥ ሁኔታዉን ለማንቀሳቀስ የፈረጠመ የገንዘብ ኃይላቸዉ አላቸዉ። አሱ አንዱ ነዉ። ሌላዉ አገር ቤት ባሉ ቤተሰቦቻዉ አመለካከት ላይ ጫና ማሳደርም ይችላሉ። በዉጪ ያሉ ኬንያዉን ተነጋግረዉ መግለጫ ቢልኩ አገር ዉስጥ ካሉት ይልቅ ክብደት እንዳለዉ ይታመናል።»


በእሳቸዉ እምነትም የኢንተርኔት ቴክኒዎሎጂ የዲሞክራሲን ሂደት የሚረዳ በመሆኑ ጠቀሜታዉ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል። በኬንያዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሁለቱም ተፎካኪዎች ለምርጫ ቅስቀሳዉ የዋለ የየራሳቸዉ ድረ ገፅ አላቸዉ። የቻለ አገር ዉስጥ ያልቻለዉ ባለበት አገር ሆኖ ይከታተላቸዋል። የራሱን አስተያየት ይልካል፤ እርስ በርስም ይነጋገርበታል።

ከተጎራባቾቿ ጋ ስትተያይ ኬንያ መረጋጋት የሰፈነባት የምስራቅ አፍሪቃ አገር ናት። ምርጫዉ በተቃረበበት በዚህ ሰሞን ደግሞ ማጭበርበር ይኖራል በሚል ግጭትና ትርምስ አስግቷል። የምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ካለፈዉ ሰኔ ወር ወዲህ የ70 ሰዎች ህይወት አልፏል። ወደ2 ሺ የሚደርሱ ቤተሰቦችም ፖለቲከኞች እንዳባባሱት በሚነገረዉ የጎሳ ግጭት ሳቢያ ከመኖሪያቸዉ ተፈናቅለዋል።

የፊታችን ሃሙስ የሚካሄደዉ ምርጫ በኬንያ የምርጫ ታሪክ ተፎካካሪዎች አንገት ለአንገት ተያይዘዉ የተፋለሙት ተብሏል። አሁን በስልጣን ላይ ያሉትና ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ የሚፍጨረጨሩት ሟይ ኪባኪና ተቃዋሚያቸዉ ራይላ ኦንዲንጋ እጅግ በተቀራረበ የድምፅ ዉጤት ላይ እንደሚገኙ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች እየጠቆሙ ነዉ። በምስራቅ አፍሪቃ ኬንያ በምጣኔ ሃብቷ ማደግ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዉም የፖለቲከኞቿን ብስለቷን እያሳየች ያለችበት ወቅት ነዉ።