1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሽታይንማየር ወደ ኩባ ተጓዙ

ዓርብ፣ ሐምሌ 10 2007

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ወደ ኩባ አቀኑ።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሁለት ቀናት ጉብኝት በበርሊንና ሃቫና መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽትይንማየር ወደ ኩባ ሲጓዙ በ25 አመታት ውስጥ የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/1G0Fr
Steinmeier außenminister wien
ምስል picture-alliance/dpa/EPA/H. Punz

[No title]


የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአገራቸው ውህደት 25 አመታት በኋላ ኩባን የጎበኙ የመጀመሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ዛሬ ሃቫና ደርሰዋል። የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም የምትከተለው ኩባ ከቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን ጋር ወዳጅነት የነበራት ቢሆንም ከጎርጎሮሳዊው የ1959 ዓ.ም. አብዮት በኋላ ከምዕራብ ጀርመን ግን አንድም አንድም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጎብኝቷት አያውቅም። ኩባን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኙት የኢኮኖሚ ሚኒስትር የነበሩት ቬርነር ሙለር በጎርጎሮሳዊው 2001 ዓ.ም. ነበር። ዛሬ ወደ ሃቫና ያቀኑትና ከ25 አመታት በኋላ ኩባን በመጎብኘት ቀዳሚ የሆኑት በጀርመን ምክር ቤት አባል የሆኑት ክላውስ ባርቴል ምዕራብ ጀርመን ኩባን ችላ ማለቷ ስህተት እንደነበር ይናገራሉ።
«በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም ቢሆን ጀርመን በኩባ ላይ ያላትን አቋም ነጥላ ልትቆም ትችል ነበር። ይህንን ሌሎች የምዕራብ ሃገራትም ያደርጉ ነበር። ቆየት ብሎ ሳስበው ከኩባ ጋር ያለውን ግንኙነት ለምስራቅ ጀርመን መተዋችን ስህተት ነበር።»
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በሃቫና በሚኖራቸው ቆይታ የኩባውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድርጌዝ ፓሬላን ጨምሮ በርካታ የኩባ ሚኒስትሮችን እና የኩባ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ካርዲናል ጄሚ ሉካስ ኦርቴጋን ያነጋግራሉ።

Kuba Präsident Raul Castro im Parlament
ምስል Imago/Xinhua

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጉብኝት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከትንሿ የካሪቢያን የደሴት አገር ጋር ለአምስት አስርት አመታት አገራቸው የገባችበትን ፍጥጫ መቋጫ አበጅተው አንዳቸው በሌላው ኤምባሲ ለመክፈት ሁለት ሳምንት ሲቀራቸው የሚደረግ ነው።

ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ኩባ የግል ኩባንያዎችን በማበረታታት እና የግብርና ማሻሻያ በማድረግ ለአመታት የዘለቀውን የእዝ ኢኮኖሚ ከፈት ማድረግ ችላለች ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩባ ቆይታቸው አሁን በጡረታ ላይ ከሚገኙት የኩባ አብዮት መሪ ፊደል ካስትሮ ጋርም ይሁን ከታናሽ ወንድማቸውና የአሁኑ ፕሬዝዳንት ራዑል ካስትሮ ጋር የመገናኘት እቅድ የላቸውም።

ባለፈው አመት ብቻ ጀርመን ወደ ኩባ 191 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጡ ምርቶቿን የላከች ሲሆን ማሽኖች፤ኬሚካሎችና መድሃኒቶች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። ኩባ በበኩሏ 33 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጡ መጠጦችና የትምባሆ ምርቶች ለጀርመን ሸጣለች። ኩባን በከፍተኛ ደረጃ ከሚጎበኙ የውጭ አገር ዜጎች ጀርመናውያን በሶስተኛ ደረጃ ይገኛሉ። የሁለቱ አገሮች የንግድ ግንኙነት ግን ያን ያህል የጠነከረ አይደለም። ኩባ ከጀርመን የውጭ ንግድ መዳረሻዎች በ101ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ በገቢ ንግድ ደግሞ 125ኛ ደረጃን ይዛለች።

በጀርመን ምክር ቤት አባል የሆኑት ክላውስ ባርቴል ጀርመን ከኩባ ጋር የሚኖራት የተሻሻለ ግንኙነት ለመላው ደቡብ አሜሪካ መልካም መሆኑንና ሚዛናዊ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

US-Präsident Obama und Präsident Raul Castro geben sich die Hand beim Amerika-Gipfel in Panama
ምስል Reuters/Jonathan Ernst

«ከኩባ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ጣታችንን መጠቆማችንን ትተን ከሌሎች የዓለማችን አገራት እንዳለን ሁሉ እኩል በሆነ መልኩ ልንቀጥል ይገባል።»ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኩባ ሲያቀኑ ጥቂት የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮችን አስከትለዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኩባ ጋር ያለውን ወዳጅነት ለማሻሻል ለጉብኝት መንገድ ቢገቡም በዴሞክራሲ እና የፕሬስ ነጻነት ላይ ግን ጋር ልዩነት እንዳላቸው አልሸሸጉም።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ