1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያና የዓረብ መንግሥታት ማኅበር

ሐሙስ፣ ኅዳር 7 2004

ዋና ጽ/ቤቱ በካይሮ ፤ ግብፅ የሚገኘው የዐረብ መንግሥታት ማኅበር፤ ሶሪያ በተቃውሞ ወገኖች ላይ የኃይል እርምጃዋን ታቆም ዘንድ ተጨማሪ የ 3 ቀን የጊዜ ገደብ መስጠቱ ተነገረ።

https://p.dw.com/p/Rx36
በዐረብ መንግሥታት ማኅበር ስብሰባ፤ የሶሪያ ወኪል ያልተገኘበት ባዶ ወንበር፣ምስል dapd

የማኅበሩ አባላት ይህን የወሰኑት ትናንት ውጫ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸው ፣ ትናንት ራባት ፣ ሞሮኮ ውስጥ ከመከሩ በኋላ ነው። ሶሪያ የቀረበላትን ማሳሰቢያ በመርመር ላይ መሆኗን በዩናይትድ እስቴትስ የደማስቆ መንግሥት አምባሳደር ኢማድ ሙስጠፋ ገልጸዋል። ሶሪያ ዐረባውያን ተቆጣጣሪዎችን እንድትቀበልና በተቃዋሚዎች ላይ የምትወስደውን የኃይል እርምጃ እንድታቆም ነው በዐረቡ ራቢጣ የተጠየቀች። ከካይሮ ፤ ብዮርን ብላሽከ ፤ የላከውን ዘገባ ተክሌ የኋላ አጠናቅሮታል።

ሶሪያ ለጊዜውም ቢሆን ከዐረብ መንግሥታት ማኅበር አባልነት ትወገዳለች አትወገድም፤ የ 22ቱ አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች፤ ትናንት ራባት ላይ በአስቸኳይ ስብሰባ ሲመክሩ የዋሉበት ጉዳይ ነበር። የሶሪው ፕሬዚዳንት በሺር አል አሰድ ፣ በሲብሎች ላይ እየወሰዱ ያሉትን የኃይል እርምጃ ካልገቱ እገዳው የሚቀርላቸው አይመስልም። አሰድ ሌላም አማራጭ አላቸው ነው የሚባለው። እርሱም እንደተጠየቁት፣ 500 የሰብአዊ መብት ታጋዮች ልዑካንና የዐረብ መንግሥታት ማኅበር ተወካዮችን ፣ ሶሪያ ውስጥ ገብተው እንዲመረምሩ መፍቀድ ነው። የዐረቡ ራቢጣ ዋና ጸሐፊ ናቢል ኧል አረቢ ትናንት እንዲህ ነበረ ያሉት---

«በዐረብ መንግሥታት ማኅበር ውስጥ 16 የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ተሰብስበው ነበር። እናም በዛሬው ዕለት ፣ አንድ ተስማሚ ውሳኔ ከተላለፈ፣ እያንዳንዱ ድርጅት ተወካዮችን እንደሚልክ ነው ስምምነት የተደረገው። ሁሉም ፣ በተልእኮው ለመሳተፍ ዝግጁ ሲሆኑ፣ በሙያቸውም ሰፊ ተመክሮ ያላቸው ናቸው። እንደሚመስልኝ፣ የራቢጣው የሚንስትሮች ም/ቤት በተቻለ ፍጥነት ተልእኮው እንዲከናወን ውሳኔ ሳያስተላልፍ አይቀርም። »

እንደተገለጠው ፤ ማኅበሩ የ 3 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ገደብ ሰጥቷል።

የቓጣር ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፤ ሃማድ ቢን ጃሲም ኧል ታኒ ግን ውሳኔው«የመጨረሻ » ሊባል አይገባም ባይ ናቸው--

«ይህ የመጨረሻ ዕድል ነው ብለን መናገር አንፈልግም፤ ምክንያቱም ፣ ማስጠንቀቂያ እንዲመስል ስልማልፈልግ ነው። ማለት የምችለው፤ የዐረብ መንግሥትት ማኅበር ባደረገው ጥረት ፤ ሁኔታው ፍጻሜ ከሚያገኝበት ጫፍ ላይ መደረሱን ነው።ለአግዚአብሄር የምንጸልየውና ተስፋ የምናደርገው፤ሶሪያውያን ወንድሞቻችን ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ፍጻሜ እንዲያገኝ በማብቃት እንደሚረዱን ነው።»

አንድ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተመልካች እንደሚያዩት፤ የሰብአዊ መብት ልዑካኑ፤ የሶሪያን ውዝግብ ለማስወገድና የኃይል እርምጃውን ለመግታት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። የአገሪቱ መገናኛ ብዙኀንም ፤ የደማስቆ አገዛዝ፤ ዐረባውያን ታዛቢዎች ቢገቡ ይፈቅድላቸዋል በማለት ዘግበዋል።

አንዳንድ የዐረብ መንግሥታት፣ ሶሪያን ማገዱ የአገሪቱን ውዝግብ ያባብሳል የሚል ሥጋት ነው ያላቸው። በመጨረሻም ሂደቱ ጣልቃ ገብነትን ሊጋብዝ የሚችል ሲሆን፤ ከዐረብ ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች መካካል፤ ጣልቃ ገብነቱን የሚሻ አንድም አይገኝም። በሌላም በኩል፤ የዐረብ መንግሥታት ውሳኔ ፤ የአውሮፓው ኅብረት እገዳ ታክሎበት ፤ ለመፍትኄ መንገድ ይጠርግ ይሆናል።

ይፋ ያልተነገረው ፤ የአሰድ የሥልጣን ይልቀቁ ጥያቄና የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ፤ ፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ፤ በይፋ ጉባዔ ይነሣ ይሆናል። ከካይሮ እንደሚነገረው፤ ፕሬዚዳንት አሰድ ሥልጣን እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ የሽግግሩ መንግሥት ቅርፅ እንዴት ሊሆን እንደሚገባ ሳይመከርበት አይቀርም።

የዴሞክራሲው ንቅናቄ በየጊዜው ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል። የተቃውሞው ወገን የብሔራዊ ም/ቤቱ ሊቀመንበር ቡርሃን ጋሊውን ከትናንት በስቲያ ከጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቨለ ጋር ከተገናኙ በኋላ፤ እንደገና ትናንት በሞስኮ ይፋ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ጋሊውን ፤ በአሳድ ላይ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጫና፣ ሩሲያ፤ ልትደግፍ ይገባል ማለታቸው ተጠቅሷል።

«ከፈላጭ ቆራጩ መንግሥት አባላት ፣ በተለይ፣ በእጃቸው የሰው ደም ከሌለባቸው ጋር ውይይት ማካሄድ እንፈልጋለን። አሻፈረን አላልንም። በአንጻሩ፤ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትንና የእርስ-በርስ ጦርነትን ከወዲሁ ለመግታት፣ በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር ይደረግ ዘንድ መደራደር እንሻለን።»

የተቃውሞው ወገን ሊቀመንበር፤ ከሩሲያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚኻኢል ቦግዳኖቭ ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ ሩሲያዊው ባለሥልጣን፤ በሶሪያ ላይ ፣ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ተፈላጊ አይሆንም ሲሉ ተደምጠዋል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ፣የሩሲያ መንግሥት ፤ በስደት የሚገኘውን የሶሪያን የተቃውሚ ድርጅት መሪ ተቀብሎ ማነጋገሩ፤ ፕሬዚዳንት በሺር አል አሰድ ግፊኅ እንዳየለባቸው ጠቋሚ ሳይሆን አልቀረም። የሩሲያ መንግሥት፤ የአሰድ ጠንካራ ተጓዳኝ መሆኑ የታወቀ ነው።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ