1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማልያ ግጭት እና የተባበሩት መንግስታት አስቸኳይ ጉባኤ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18 1999

በኢትዮጽያ በሚደገፈዉ የሶማልያ ሽግግር መንግስት እና በሶማልያ የእስላማዊ ሸርያ ፍርድ ቤቶች ኅብረት መካከል ዘጠነኛ ቀኑን የያዘዉ ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን በትናንትናዉ እለት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታዉ ምክርቤት በሶማልያ ጉዳይ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ጉባኤ ጠርቶ የጋራ መልስ ሳያገኝ ተበትኖአል።

https://p.dw.com/p/E0hZ
የሶማልያ ሽግግር መንግስት ጦር በቡርሃካባ
የሶማልያ ሽግግር መንግስት ጦር በቡርሃካባምስል AP

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታዉ ምክርቤት በትናንትናዉ እለት ባደረገዉ የአስቸካይ ጉባኤ በአንድ ነጥብ መድረስ አልቻለም። የምክር ቤቱ አስራ አምስት አባላት የሶስት ሰአታት ስብሰባ የክርክሩ ዋና ነጥብ በተለይ ያተኮረ ኢትዮጽያ በሶማልያ አስገብታለች የተባለዉን የጦር ሰራዊት በአፋጣኝ እንድታስወጣ የሚል ነበር። እንደ ተባበሩት መንግስታት ልዩ መልክተኛ Francois Lonseny ችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል ነዉ። በትናንትናዉ እለት የሶማልያ የሽግግር መንግስት ከኢትዮጽያ ጋር በመሆን በጦርነቱ ድልን እያገኙ መሆናቸዉን ሲገልጹ የእስላማዊዉ ሸርያ ፍርድ ቤቶች ህብረት በበኩላቸዉ ታክቲካዊ ስልት ሲሉ ወደ ኳላ ማፈግፈጋቸዉን ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት የሶማልያ ተለዋጭ መልክተኛ Idd Bedel Mohamed ባሰሙት ንግግርም
«ማሳየት የምንፈልገዉ ደካማ እና የማይረባ አይነት መንንግስት እንዳልሆንን ነዉ። በነገራችን ላይ ጦራችን በእስላማዊ ጦረኞች የታፈነዉን የአገራችንን ክፍል ማስለቀቅ ይችላል። በዚህ ሰአት መንገር የምችለዉ እና እራሳችሁም ማየት እንደምትችሉት ምን ያህል እንደታገስን፣ ምንያህል የአለም አቀፉን ህግጋት እንዳከበርን ነዉ። ነገር ግን የእስላማዊዉ ፍርድ ቤቶች ህብረት ሃይላት የተወሰዱትን ከተሞች መቆጣጠር አለብን። እዚህ ላይ በርግጥም ልገልጽላችሁ የምወደዉ ይኸዉ የእስላማዊ ፍርድቤቶች ህብረት ይቆጣጠረዉ የነበረዉን አብዛኛዉን ክልል የሶማልያ የሽግግር መንግስት አስለቅቆአል።»

በትናንትናዉ እለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ በሶማልያ በተለይ ኢትዮጽያ ያስገባችዉን የጦር ሃይላት እንድታስወጣ የተጀመረዉም ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም የሚለዉ ጥያቄ ነጥብ ላይ አሜሪካ እና ብሪታንያ ስምምነታቸዉን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ይህን ይህን አይነቱን የሃሳብ ነጥብ ያቀረቡት የተባበሩት መንግስታት የፈረንሳይ መልክተኛ Jean- Marc de la Sabliere ም

«ሁሉም የቁች ሃይላት ባስቸኳይ መዉጣት አለባቸዉ እዚህ ላይ ሁሉንም ስል ደግ’ሞ ባጠቃላይ ማለቴ ነዉ።

የሶማልያ የሽግግር መንግስት ከሶማልያዉ የሸርያዎች ፍርድ ቤቶች ሚሊሽያ ጋር በሚያደርገዉ ጦርነት በኢትዮጽያ ጦር በመታገዙ ድልን እያገኘ እና እየተጠናከረ እንደሆነ ይገልጻል። የሶማልያ የሽግግሩ መንግስት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር Ismail Hurre Buba በትናንትናዉ እለት በበናይሮቢ ተገኝተዉ ባሰሙት ንግግር
«የሽግግር መንግስቱ ትኩረት በየክልሉ የሚገኙትን የእስላማዊ ፍርድቤቶች ሚሊሽያ ማጽዳት ነዉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት ትኩረታችን በሁለት ቦታ ማለት የኪስማዮ ከተማ በደቡባዊ ክልል እና መቆዋዲሾን እንደ ዋና ከተማነት ነዉ።»

የሶማልያ የሽግግር መንግስት አባላትም በሺዎች የሚቆጠሩ የእስላማዊ ህብረት ሚሊሽያዎች ገለናል ብለዋል። የኢትዮጽያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዜናዊ ጦርነቱ ከሰባት ቀናት የበለጠ እንደማይፈጅ ገልጸዋል።
«የሶማልያ ፍርድቤቶች ህብረት ሚሊሽያዎች ከመሸጉበት ክልላቸዉ አፈግፍገዋል። እኛም የሚጠበቅብንን ግማሹን ግዴታችንን ተወጥተናል። ቀሪዉን እና ግማሹን እንደጨረስን ጦራችን የሶማልያን ምድር ለቆ ይወጣል።» ባይ ናቸዉ

በሶማልያ ዘጠነኛ ቀኑን የያዘዉ ጦርነት የሽግግር መንግስቱ ወታደሮች ወደ መቆዋዲሾ እየተጠጉ ናቸዉ ሲል አስታዉቋል። በኤርትራ ይደገፋል የሚባለዉ የእስላማዊ ፍርድቤቶች ህብረትም በበኩሉ በመቶ የሚቆጠሩ የሽግግር መንግስቱን ወታደሮች እንደገለ አስታዉቋል።


አዜብ ታደሰ