1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት

ሰኞ፣ ጥቅምት 15 2003

በአውሮፓ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ያለፈው ሣምንት አጋማሽ የሻምፒዮናው ሊጋ ሶሥተኛ የምድብ ግጥሚያዎች ዓቢይ ትኩረትን የሳቡበት ሆኖ ሲያልፍ ሰንበቱም እንደተለመደው የየብሄራዊው አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ውድድር የተካሄደበት ነበር።

https://p.dw.com/p/Pnbo
ምስል dapd

በእግር ኳስ እንጀምርና በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር የትናንቱ ሰንበት ለአንዴው የአውሮፓ ሻምፒዮን ለፋየኖርድ ሮተርዳም የውርደት ሆኖ ነው ያለፈው። ክለቡ በወቅቱ ሊጋውን በሚመራው በአይንድሆፈን 10-0 ሲቀጣ እንደዚህ የከፋ ሽንፈት የደረሰበት ቀደም ያለ ጊዜ አይታወስም። በአንጻሩ በሌሎቹ የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድሩ ከሞላ-ጎደል በአብዛኛው የተጠበቀ ሂደቱን ይዞ እንደቀጠለ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ የሬያል ማድሪድና የድንቅ ኮከቡ የክሪስቲያኖ ሮናልዶ የስኬት ጉዞ በዚህ ሰንበትም አልተገታም። ሬያል በዝናኛው ቤርናቤዉ ስታዲዮም ሬሢንግ ሣንታንዴርን 6-1 አከናንቦ ሲሸኝ በስምንት ግጥሚያዎቹ አንዴም ሳይሸነፍ ሊጋውን በሃያ ነጥቦች በበላይነት ይመራል። ከስድሥት አራቱን ጎሎች ያስቆጠረው ደግሞ ሮናልዶ ነበር። ቡድኑ በወቅቱ በግሩም ሁኔታ ላይ ሲገኝ ባለፉት አራት ግጥሚያዎቹ ብቻ 18 ጎሎችን ማስቆጠሩ ጥንካሬውን በግልጽ ያንጸባርቃል።

በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ሰንበት ቪላርሬያል አትሌቲኮ ማድሪድን 2-0 ሲያሽንፍ ከሬያል ማድሪድ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ባርሤሎናም ሣራጎሣን በተመሳሳይ ውጤት ሲረታ በእኩል ነጥብ ሆኖም በጎል ልዩነት ብቻ ሶሥተኝነቱን እንደያዘ ቀጥሏል። በነገራችን ላይ ለባርሣ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው የአርጄንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር።

Fußball 1. Bundesliga 9. Spieltag Borussia Dortmund gegen TSG Hoffenheim
ምስል dapd

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የዘንድሮው አስደናቂ ክለብ ማይንስ ሌቨርኩዝንን 1-0 በማሽነፍ ከሣምንት በኋላ እንደገና ወደ አመራሩ ተመልሷል። ቡድኑ ከዘጠኝ ግጥሚያዎቹ ስምንቱን ሲያሸንፍ በወቅቱ 24 ነጥቦች አሉት። ጎሏን በሰባኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ተቀያሪው የአውስትሪያ ተጫዋች አንድሬያስ ኢቫንቺትስ ነበር። ባልተጠበቀ ሁኔታ ሊጋውን ማስገረም የቀጠለው ቡድን የማይንስ አሠልጣኝ ቱሽል የስኬቱ ምስጢር ምን እንደነበር የገለጸው እንደሚከተለው ነው።

“በጨዋታችን ብዙ ዕድል አግኝተን ነበር። እናም በጥሩ ቅብብል ነው ጎሏን ያስቆጠርነው። በተለይም ካለፈው ሣምንት የሃምቡርግ ሽንፈታችን በኋላ ሌቨርኩዝን ውስጥ መልሰን ማሽነፍ መቻላችን ተጫዋቹንና እኔንም በጣም የሚያኮራ ነው። የአጨዋወታችንን ሁኔታም በተመለከተ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ባሳየነው ደስተኛ ነኝ”
በማይንስ ድል ዶርትሙንድ ቦታውን ለቆ አመራሩን ማስረከቡ ግድ ሆኖበታል። ክለቡ ባለፈው ሣምንት በጎል ብልጫ ጨብጦት የነበረውን አመራር ያጣው ከሆፈንሃይም ጋር በመጨረሿ በገባችበት ጎል እኩል ለእኩል 1-1 በሆነ ወጤት በመለያየቱ ነው። ይህም ሆኖ አሠልጣኙ ዩርገን ክሎፕ በውጤቱ ብዙም አለመከፋቱን ነው የተናገረው።

“ዛሬ ባገኘናት አንድ ነጥብ እርግጥ መርካት ይኖርብናል። አሁን ከጨዋታው በኋላ በትኩሱ ውጤቱ የሚሰማን የማሸነፍን ያህል ሆኖ ነው። በሣምንቱ ሂደት ምናልባት ያጣነውን ነጥብ እያጤንን መሄዳችን አይቀር ይሆናል። አሁን ግን ዋናው ነገር ስኬታችንን ማጣጣሙ ነው”

ጅማሮው በተገለባበጠበት ቡንደስሊጋ ከቀደምቱ ክለቦች መካከል ባየርን ሙንሺን ከሃምቡርግ ጋር ባዶ-ለባዶ በመለያየቱ በ 11ኛ ቦታው ሲቀጥል ብሬመን ግን መንሸን ግላድባህን በማሸነፍ ከመሃል ሜዳ ወደ ስምንተኛው ቦታ ከፍ ሊል ችሏል። በሌላ በኩል ሽቱትጋርት ሣንት ፓውሊን 2-0 አሸንፎ ከመጨረሻው ቦታ ሲሰናበት በአንጻሩ ኮሎኝ በሃኖቨር 1-0 ተረትቶ ከታች ወደ ላይ ተመልካች፤ የመጨረሻ፤ 18ኛ ሆኗል። ታዲያ ውድቀቱ ለአልጣኙ ለዝቮኒሚር ሶልዶ መባረርም ምክንያት ነው የሆነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ አመራሩን የያዘው ላሢዮ በስምንት ግጥሚያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ 19 ነጥቦችን በማግኘት አንደኛ እንደሆነ ቀጥሏል። ላሢዮ ካልጋሪን 2-1 ሲረታ አራት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛው በገዛ ሜዳው ከሣምፕዶሪያ 1-1 የተለያየው ኢንተር ሚላን ነው። ኢንተር ከለየለት ውርደት ላተረፈችው የበኩሉ ጎል ሣሙኤል ኤቶን ሊያመሰግን ይገባዋል። ሶሥተኛው ኤ.ሢ.ሚላን አንድ ግጥሚያ የሚጎለው ሲሆን ካሸነፈ ቀደምቱን ላሢዮን በሁለት ነጥብ ልዩነት ሊቃረብ የሚችል ነው።

በፈረንሣይ ሊጋ በርካታ ክለቦች በጠባብ ፉክክር ላይ የሚገኙበት ሁኔታ ባለበት ቀጥሏል። ስታድ ሬንስ ባለፈው ሰንበት አሥረኛ ግጥሚያው ምንም እንኳ በሞንፔልዬር 1-0 ቢረታም በ 19 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሶሥት ክለቦች፤ ማለት ማርሤይ፣ ሣንት ኤቲየንና ስታድ ብሬስት አንዲት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብለው ይከተሉታል። በጠቅላላው የመጀመሪያውን ክለብ ከስድሥተኛው የሚለዩት ሁለት ነጥቦች ብቻ ናቸው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና በአንጻሩ ፖርቶ በአስተማማኝ ሁኔታ መምራቱን ቀጥሏል።

በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮንም ቢያንስ አራት ክለቦች ከሣምንት ሣምንት ለመሪነት መፎካከራቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን የሰንበቱን ውድድር ይበልጥ ማተኮሪያ ያደረገው ግን የፋየኖርድ በአይንድሆፈን እንዳልነበር ሆኖ በ 10-0 ከሜዳ መውጣት ነበር። አይንድሆፈን ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ በ 24 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አያክስ አምስተርዳም ከኤክሤልሢዮር 2-2 በመለያየቱ ከሁለት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ተንሸራቷል። የዚህ ውጤት ተጠቃሚ ዴን ሃግን 3-2 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ያለው ትዌንቴ ኤንሼዴ ነው።

Champions League Halb-Finale FC Liverpool - FC Chelsea
ምስል AP

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር የትናንቱ ሰንበት በተለይም የአርሰናል፣ የማንቼስተር ዩናይትድና የሊቨርፑል ነበር። በሣምንቱ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎችና አጠቃላይ ይዞታ ላይ ሃና ደምሴ ከለንደን የላከችውን ዘገባ አጠቃለናል።

ዓለምአቀፍ ቴኒስ

በስቶክሆልም ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ ሮጀር ፌደረር ትናንት ጀርመናዊ ተጋጣሚውን ፍሎሪያን ማየርን በለየለት ሁኔታ 6-4, 6-3 በማሸነፍ ለ 64ኛ የፍጻሜ ድሉ በቅቷል። ይህም በሁልጊዜው የማዕርግ ተዋረድ ላይ በአራተኝነት ከፒት ሣምፕራስ ጋር የሚያስተካክለው ነው። ሮጀር ፌደረር ባለፈው ሣምንት የሻንግሃይ ፍጻሜ በብሪታኒያው ተወላጅ በኤንዲይ መሪይ በፍጹም የበላይነት መሸነፉ ሲታወስ የትናንቱ ድል መጽናኛ እንደሆነው አያጠራጥርም።
በሞስኮ የክሬምሊን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ የሰርቢያው ቪክቶር ትሮይኪ የቆጵሮስ ተጋጣሚውን ማርኮስ ባጋዳቲስን 2-1 ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ ሩሢያዊቱን ማሪያ ኪሪሌንኮን በሁለት ምድብ ጨዋታ ረትታለች። በሉክሰምቡርግ ሻምፒዮና የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያም ሮቤርታ ቪንቺ ከኢጣሊያ ጀርመናዊቱን ዩሊያ ጆርጅስን በተለየ ጥንካሬ በማሸነፍ ለድል በቅታለች። በተረፈ ዛሬ የወጣው ዓለምአቀፍ የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ የራፋኤል ናዳልን ቀደምትነት እንደገና አረጋግጧል። ሁለተኛ ሮጀር ፌደረር፣ ሶሥተኛ ኖቫክ ጆኮቪች፤ እንዲሁም አራተኛ ኤንዲይ መሪይ ነው።

Formel 1 Südkorea Vettel
ምስል AP

ፎርሙላ-አንድ ደቡብ ኮሪያ

በፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽቅድድም ለማጠቃለል ዝናብ ባስተጓጎለውና ቀውስ በፈጠረበት በመጀመሪያው የደቡብ ኮሪያ ግራንድ-ፕሪ ውድድር የፌራሪው ዘዋሪ ፌርናንዶ አሎንሶ አሸናፊ በመሆን እጅግ ጠቃሚ ለሆነ ድል በቅቷል። ቀደምት ተፎካካሪዎቹ ሻምፒዮናውን ሲመራ የቆየው የአውትራሊያው ማርክ ዌበርና ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ሁለቱም የሬድ ቡል ዘዋሪዎች ውድድሩን እንኳ መፈጸሙ አልሆነላቸውም። ለስፓኙ ተወላጅ የትናንቱ ድል ካለፉት አራት እሽቅድድሞች ሶሥተኛው ሲሆን ውጤቱ በአጠቃላይ ነጥብ አመራሩን እንዲይዝ አብቅቶታል። ከኮሪያው እሽቅድድም ወዲህ አሎንሶ 231፤ ዌበር 220፤ ሃሚልተን 210፤ ፌትል 206 ነጥቦች አሏቸው። የዓለም ሻምፒዮናው ሊጠቃለል የሚቀሩት ሁለት ውድድሮች ብቻ ናቸው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ