1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት

ዓርብ፣ መጋቢት 5 2006

ፖላንድ ውስጥ በተካሄደው የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድንቅ ውጤት አስመዝግበዋል። እንደ ሩስያ ሁሉ ኢትዮጵያም 5 ሜዳልያ አግኝታ በ 1 ወርቅ በመበለጥ በሶስተኛነት አጠናቃለች። ጀርመን 18ኛ ደረጃን ይዛለች። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ እየገሰገሰ ነው። ሊቨርፑል እና አርሰናል ተናንቀውታል።

https://p.dw.com/p/1BMuu
800 Meter Lauf Männer Goldmedaille Mohammed Aman Leichtathletik Weltmeisterschaft 2013 Moskau
ምስል Getty Images

ማንቸስተር ሲቲ ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል፤ ከቸልሲ በ9 ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል። በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙንሽን አሁንም የሚያቆመው አልተገኘም። ቮልፍስቡርግን 6 ለ 1 ጉድ አድርጓል። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ተሸንፏል፤ ሪያል ማድሪድ ግን መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። በመጀመሪያ ግን ፖላንድ ውስጥ የተካሄደውን የአትሌቲክስ ውድድር ነው የምንቃኘው።

የቦልቲክን ባሕር ተንተርሳ በተቆረቆረችው የፖላንዷ ሶፖት ከተማ ካለፈው አርብ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር በትናንትናው ዕለት በተሳካ ሁናቴ ተጠናቋል። ኢትዮጵያ በ5 የርቀት አይነቶች፣ በ9 አትሌቶች ተካፋይ ሆና በመወዳደር በሜዳሊያ ሰንጠረዝ 3ኛ ደረጃን አግኝታለች። የፈረንሣዩዋ ወኪላችን ሐይማኖት ጥሩነህ ውድድሩ የተካሄደበት ኤርጎ ስታዲየም በመገኘት ፉክክሩን ለመከታተል ችላለች። አትሌቶቹንም ከድል በኋላ እዛው ስታዲየም ውስጥ አነጋግራለች።

Polen - Hallen WM 2014
መሃመድ አማን ከድል በኋላምስል DW/T. Haimanot

በተለይ ገንዘቤ ዲባባ እና መሐመድ አማን ከትናንቱ ድል አስራ አምስት ቀን ቀደም ድብሎም ተመሳሳይ ድል ማስመዝገባቸው ይታወሳል። በወቅቱ ባደረግንላቸው ቃለምልልስ በፖላንዱ ውድድር ላይም አሸናፊ ሆነው አገራቸውን እንደሚያስጠሩ ቃል ገብተው ነበር።

አትሌቶቻችን በዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያዎችን አጥልቀው ብቃታቸውን አስመስክረዋል፤ ሀገራቸውንም አስጠርተዋል። ወደፊትም በሌሎች የውድድር አይነቶች እና በኦሎምፒኩ መስክ ተጨማሪ ድል እንደሚያስመዘግቡ እንመኛለን። በነገራችን ላይ በእዚሁ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር 12 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ዩናይትድ ስቴትስ አንደኛ ሆናለች። ሩስያ ከኢትዮጵያ እኩል 5 ሜዳሊያ በማግኘት ሆኖም የወርቅ ብዛቷ ከኢትዮጵያ በአንድ ስለሚበልጥ ሁለተኛ ወጥታለች። ኢትዮጵያ ሁለት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው ሶስተኛ ደረጃን ልትይዝ የቻለችው። ጀርመን ሶስት የብር ሜዳሊያዎችን ብቻ በማግኘት በ18ኛ ደረጃ ውድድሩን አጠናቃለች።

የቸልሲው ሣሙኤል ኤቶ
የቸልሲው ሣሙኤል ኤቶምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

በቀጥታ ወደ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ነው የምንሻገረው። ቅዳሜ ማን ዩናይትድ ዌስት ብሮሚችን 3 ለ ባዶ ሲሸኝ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከአቪላ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቶ ነጥብ ጥሏል። ቸልሲ ቶትንሐምን 4 ለባዶ አንኮታክቷል። ቅዳሜ ያገኘውን ሶስት ነጥብ ደምሮ የደረጃ ሠንጠረዡን ቸልሲ በ66 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ሊቨርፑል እና አርሰናል አንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው በተመሳሳይ 59 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ይከታተላሉ።

ሊቨርፑል ሁለተኛ፣ አርሰናል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት። ማንቸስተር ሲቲ ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀረው 57 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቶትንሐም በ53 ነጥብ አምስተኛ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 48 ነጥብ ይዞ መሪው ቸልሲ ላይ ለመድረስ 18 ነጥቦችን መሰብሰብ ይጠበቅበታል።

የሊቨርፑሉ ግብ አዳኝ ሉዊስ ሱዋሬዝ 24 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የፕሬሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነቱን አሁንም እንዳስጠበቀ ነው። ሌላኛው የሊቨርፑል አጥቂ ዳንኤል ስቱሪጅ በ18 ግቦች ይከተለዋል። የማንቸስተር ሲቲው አጉዌሮ በ15 ግቦች ሶስተኛ በመሆን ይከተላል።

ከእዚሁ ከፕሬሚየር ሊግ ሳንወጣ፤ ዛሬ 33ኛ ዓመት የልደት በዓሉን የሚያከብረው የአርሰናሉ አጥቂ ሳሙኤል ኤቶ ዕድሜውን አስመልክቶ አሰልጣኙ ሞርሒኖ ከእዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት ላይ ከትናንት በስትያ ሜዳ ላይ በመቀለድ ታዳሚውን አስፈግጓል። ኤቶ 56ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ወደ ማዕዘን በዝግታ በማቅናት በእድሜ እንደገፋ ሰው ግራ እጁን ጀርባው ላይ አድርጎ አሰልጣኙ ላይ ቀልዷል።

የባየር ሙንሽን እግር ኳስ ቡድን ፕሬዚዳንት ኡሊ ሆኔስ
የባየር ሙንሽን እግር ኳስ ቡድን ፕሬዚዳንት ኡሊ ሆኔስምስል Reuters

የቸልሲው አሰልጣኝ በቅርቡ ስዊዘርላንድ ውስጥ ከአንድ ባለሀብት ጋር ባደረጉት የግል ውይይት ወቅት ተቀርፆ በመገናኛ አውታሮች ይፋ የሆነው ውይይታቸው አነጋጋሪ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ሞሪንሆ ከባለሀብቱ ጋር ሲነጋገሩ «የቸልሲ ችግር ምን መሰሎት፤ የአጥቂ እጥረት አለብን። በእርግጥ አንድ አለኝ» አሉ፤ ሳሙኤል ኤቶን ማለታቸው ነበር። «ግን እሱ» ቀጠሉ «32 ዓመቱ ነው። ማን ያውቃል ምናልባትም 35» ሲሉ በኤቶ ዕድሜ የተሰማቸውን ጥርጣሬ ገለፁ። አፍታም አልቆየ በለፈለፉ ይጠፉ እንዲል ይህ ንግግራቸው መቆሚያ መቀመጫ አሳጣቸው።

እናም ይህ አባባላቸው በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች በስፋት ትንታኔ ሲሰጥበት ለማስተባበል አልሞከሩም። ብቻ ንግግሩ የሚቀዳ መሆኑን ባውቅ እንደዛ ብዬ አልናገርም በማለት የመገናኛ አውታሮችን ስነምግባር የጎደላቸው ሲሉ ተችተው ነበር። ኤቶ ከትናንት በስትያ በእድሜ እንደገፋ ሰው ወገቡን ይዞ ቀስ እያለ በመራመድ መሳለቁን አስመልክቶ አሰልጣኙ ሞሪንሆ ሲናገሩ፥ «ድንቅ ነው። ደግሞም የሆነ ነገር ለማድረግ ሲዘጋጅ ስለነበር እንደዛ አይነት ነገር እንደሚያደርግ አውቀነው ነበር» በማለት በፈገግታ መልስ ሰጥተዋል ። በእዚህም አለ በእዚያ ግን እድሜህ ገፍቷል ተብሎ የተተቸው አጥቂ ብድሩን ሜዳ ላይ የከፈለ ይመስላል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ፍልሚያ፥ የባየር ሙንሽን ፕሬዚዳንት ኡሊ ሆኔስ በግብር ማጭበርበር ክስ ዛሬ ፍርድ ቤት ቢቆሙም፤ ተጨዋቾቹን ግን ሜዳ ላይ የሚገታቸው አልተገኘም። የባየር ሙንሽን የእግር ኳስ ቡድን ፕሬዚዳንት ከ15 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚገመት ገንዘብ ግብር እንዳይቆረጥበት አጭበርብረዋል በሚል ነው ክስ የተመሰረተባቸው። ፕሬዚዳንቱ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ አስር ዓመት ድረስ የሚዘልቅ እስር ይጠብቃቸዋል። ከእዚህ ቀደም ለባየር ሙንሽን በመጫወት ከቡድኑ ጋር የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅተው የነበሩት ኡሊ ሆኔስ እጅግ ከበርቴ እንደሆኑም ይጠቀሳል። ኑረንበርግ ውስጥ የተከሉት ፋብሪካቸው አልዲ ለተሰኘው የዕለታዊ የፍጆታ ዕቃ አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም ለማክዶናልድ ስጋ በማቅረብ ይታወቃል። እኚህ ግለሰብ ላይ የተጀመረው የክስ ሂደት ውሳኔ በእዚሁ ሳምንት ላይ እንደሚሰጥ ተጠቁሞዋል።

የሪያል ማድሪድ ሳንቲያጎ በርናቦ ስታዲየም
የሪያል ማድሪድ ሳንቲያጎ በርናቦ ስታዲየምምስል Getty Images

ፕሬዚዳንቱ የሚመሩት የባየር ሙንሽን ቡድን ግን ከትናንት በስትያ ባለተራው ቮልፍስቡርግን በሰፊ የግብ ልዩነት 6 ለ 1 አሸንፏል። የደረጃ ሠንጠረዡን ከባየር ሙንሽን በሃያ ነጥቦች ዝቅ ብሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ፍራይቡርግን 1 ለምንም አሸንፏል። ማይንስ እና ሔርታ በርሊን ትናንት ባየር ሌቨርኩሰንና ሐኖቨር እንዲሁም ሐምቡርግ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ከትናንት በስትያ አንድ እኩል ተለያይተዋል። ሻልካ በሆፈንሀይም 4 ለባዶ ተቀጥቷል። ብሬመን ኑረንበርግን 2 ለዜሮ ረትቷል። ሽቱትጋርት ከአይንትራኅት ብራውንሽቫይግ አንድ እኩል ወጥቷል።

የደረጃ ሰንጠረዡን ባየር ሙንሽን በ68 ነጥቦች በመምራት ለብቻው እየገሰገሰ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ 48 ነጥብ ይዞ በርቀት ይከተለዋል። ባየር ሌቨርኩሰን በ44 ነጥብ ሶስተና ደረጃ ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ተበልጦ ሻልካ አራተኛ ደረጃ ላይ ነው። በስፔን ላሊጋ ትናንት ኤስፓኞላ ኤልሼን 3 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ሪያል ማድሪድ ሌቫንቴን 3 ለባዶ ቀጥቷል። ቫሌንሺያ ከአትሌቲኮ ቢልባዎ አንድ እኩል ተለያይቷል። ሴቪላ አልሜሪያን 3 ለ 1 አሸንፏል። ከትናንት በስትያ በተደረጉ ግጥሚያዎች አትሌቲኮ ማድሪድ ሴልታ ቪጎን፤ ሪያል ቤቲስ ጌታፌን እንዲሁም ግራናዳ ቪላሪያልን 2 ለዜሮ ድል በማድረግ ነጥብ ሰብስበዋል። ጠንካራው ባርሴሎና ግን ድል ሳይቀናው አምሽቷል። በቫላዶሊድ 1 ለ ባዶ ሽንፈትን ቀምሷል።

በእዚህም መሰረት ሪያል ማድሪድ 67 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሠንጠረዡን ሲመራ፤ ባርሴሎና በ64 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ዝቅ ብሎ እንዲቀመጥ ግድ ሆኖበታል። አትሌቲኮ ቢልባዎ በ63 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

በጣሊያን ሴሪኣ ደግሞ የደረጃ ሠንጠረዡን በ72 ነጥብ የሚመራው ጁቬንቱስ ፊዮሬንቲናን 1 ለ ባዶ አሸንፏል። በ58 ነጥብ ተከታይ የሆነው ሮማ 55 ነጥብ ይዞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ናፖሊ 1 ለ ዜሮ ተሸንፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ