1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥቅምት 24 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥቅምት 24 2012

በዓለም አቀፍ የማራቶን ሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን ለድል በቅተዋል። የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዘንድሮ ፉክክር ሊጠናቀቅ 2 ዙር ይቀረዋል፤ ብሪታንያው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ግን ከወዲሁ የአሸናፊነት ዘውዱን ጭኗል። ደቡብ አፍሪቃ በዓለም የራግቢ ስፖርት የፍጻሜ ፍልሚያ ብሪታንያን በአስደናቂ ኹኔታ ረትታ የዘንድሮ አሸናፊ ኾናለች።

https://p.dw.com/p/3SS0f
Formel 1 | Grand Prix USA
ምስል Getty Images/AFP/C. Mason

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሳዲዮ ማኔ በአለቀ ሰአት ሊቨርፑልን ለድል አብቅቶ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ነግሶ ቆይቷል። በጣሊያን ሴሪኣ ባሎቴሊ በዘረኝነት ስድብ ትእግስቱ ተሟጦ ከሜዳ ሊወጣ ሲል ተጨዋቾች ተማጽነው አስመልሰውታል፤ ዘግየት ብሎም ግብ አስቆጥሯል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በአይንትራኅት ፍራንክፉርት የ5 ለ1 ሽንፈት ተሸማቋል፤ አሰልጣኙም ከሥራቸው ተባረዋል። በዓለም አቀፍ የማራቶን የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን ለድል በቅተዋል። የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዘንድሮ ፉክክር ሊጠናቀቅ ሁለት ዙር ይቀረዋል፤ ብሪታንያው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ግን ከወዲሁ የአሸናፊነት ዘውዱን ጭኗል።  ደቡብ አፍሪቃ በዓለም የራግቢ ስፖርት የፍጻሜ ፍልሚያ ብሪታንያን በአስደናቂ ኹኔታ ረትታ የዘንድሮ አሸናፊ ኾናለች፤ ዋንጫ ስታነሳ ለሦስተኛ ጊዜ መኾኑ ነው።

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ ማሳረጊያ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሳዲዮ ማኔ የዓመቱ የአፍሪቃ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ የመመረጥ ዕድሉን አስፍቷል። የአፍሪቃ ምርጥ ተጨዋች ክብርን የተጎናጸፈው ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላኅ በተቀየረበት የቅዳሜው ግጥሚያ ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ ገኖ አምሽቷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሳዲዮ ማኔ ከሞሐመድ ሣላኅ ጋር
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሳዲዮ ማኔ ከሞሐመድ ሣላኅ ጋርምስል AFP/F. Walschaerts

እንደ አጀማመሩ ቢኾን መሪው ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ዳግም ነጥብ ሊጥል ጫፍ ተቃርቦ ነበር። የሴኔጋሉ ምርጥ ሳዲዮ ማኔ ግን መደበኛ ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪው አራተኛ ደቂቃ ላይ አስቶን ቪላ ላይ ባስቆጠራት ግብ ሊቨርፑልን ለድል አብቅቷል። 15ኛው ደቂቃ ላይ በጭንቅላት መትቶ ወደ ውጪ የወጣችው ኳስ፤ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ለፊርሚኖ በማቀበል ባይጸድቅም እንዲያገባ ማስቻሉ ሳዲዮ ማኔ ብቃቱን ያሳየበት እንቅስቃሴ ነበር። የፊርሚኖ ትከሻ ከጨዋታ ውጪ በመባል ነው ግቧ የተሻረችው።  በዕለቱ ድንቅ ውለታ የዋለው ይኸው ሳዲዮ ማኔ ሲመራ ለቆየው ቡድኑ ሊቨርፑል አቻ የምታደርገውን ግብ 87ኛው ደቂቃ ላይ ለአንድሪው ሮበርትሰን በማቀበል አመቻችቷል። በአሌክሳንደር አርኖልድ ከማዕዘን የተላከችውን ኳስ ደግሞ በድንቅ ኹኔታ በጭንቅላት ሸርፎ ገጭቶ ከመረብ በማሳረፍ ሊቨርፑል የማታ ማታ ለ2 ለ1 ድል እንዲበቃ አስችሏል።

ይኽም በዕለቱ ሳውዝሐምፕተንን በተመሳሳይ ውጤት 2 ለ1 ድል ላደረገው ማንቸስተር ሲቲ አናዳጅ ክስተት ኾኗል። 31 ነጥብ የሰበሰበው ሊቨርፑል ከተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ በ6 ነጥብ የበላይነቱን እንዳስጠበቀ ነው።

ትናንት ክሪስታል ፓላስን 2 ለ0 ያሸነፈው ላይስተር ሲቲ በ23 ነጥብ ማንቸስተር ሲቲን ተከትሎ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ቸልሲ ትናንት ዋትፎርድን 2 ለ1 ማሸነፍ ችሎ ተመሳሳይ 23 ነጥብ ቢሰበስብም በግብ ክፍያ ተበልጦ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አርሰናል  ቅዳሜ ዕለት ከዎልቨርሐምፕተን ጋር አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል። 17 ነጥብ ያለው አርሰናል በደረጃ ሰንጠረዡ አምስተኛ ነው። ትናንት ኤቨርተን እና አንድ ተጨዋቾ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ቶትንሀም አንድ እኩል ተለያይተዋል። ቅዳሜ ዕለት በቦርመስ 1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ዩናይትድ 13 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። 18 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት በአይንትራኅት ፍራንክፉርት 5 ለ1 በኾነ ከባድ ሽንፈት መረታቱ መነጋገሪያ ከመኾን አልፎ አሰልጣኙ እንዲባረሩ ሰበብ ኾኗል።

Fussball Bundesliga l  Eintracht Frankfurt vs Bayern München l Enttäuschung - Robert Lewandowski
ምስል picture alliance/Fotostand/Racocha

ባየር ሙይንሽንም ኾነ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ረቡዕ ዕለት በጀርመን ዋንጫ ውድድር ተጋጣሚዎቻቸው ቦኹም እና ሳንክት ፓውሊን 2 ለ1 አሸንፈው የነበረ በመኾኑ በቡንደስሊጋው ሲገናኙ ውጤቱ ምን ሊኾን ይችል በሚል አጓጉቶ ነበር። እንዲያም በመኾኑ ፍራንክፉርት አም ማይን የሚገኘው ኮሜርስ ባንክ አሬና ስታዲየም ጢም ብሎ ሞልቶ ታይቷል። የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ደጋፊዎች ቡድናቸው ከባየርን ግዛት የሚመጣው ኃያሉ ባየር ሙይንሽንን ሊገጥም ነውና መደንገጣቸው አልቀረም ግን በወኔ ተሞልተው ድጋፋቸውን ሲሰጡ ነበር።

የቡንደስሊጋውን ዋንጫ በተደጋጋሚ ከፍ ያደረገው ባየር ሙይንሽን ቡድንን ማስተናገድ ቀላል አይመስልም፤ እስከ 9ኛው ደቂቃ ድረስ። ከዚያ በኋላ ግን አይንትራኅት ፍራንክፉርቶች ምሽቱን ሙሉ ያስፈነደቃቸው ክስተት ተፈጥሯል። 9ኛው ደቂቃ ላይ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የመሀል ተከላካይ ጄሮም ቦኣቴንግ ኳሷን በተረከዝ መቆጣጠር አቅቶት ታልፋለች። እናም ኳሷን ከፖርቹጋሉ ጎንቻሎ ፓሴንሲያ ለማስጣል ቢሮጥም አልቻለም። የፍጹም ቅጣት ክልል ጠርዝ ላይ ጎንቻሎን በመጥለፉም የመሀል ዳኛው ማርኩስ ሽሚድት ለቦአቴንግ ቢጫ ካርድ ለአይንትራኅት ፍራንክፉርት ደግሞ ፍጹም ቅጣት ምት ይሰጣሉ። በቴሌቪዥን ምስል እገዛ ወዲያው ጨዋታው ከተገመገመ በኋላ ግን ዳኛው ለቦአቴንግ ቀይ ካርድ ሰጥተው ፍጹም ቅጣት ምቱን ወደ ቅጣት ምት ይቀይራሉ። የቅጣት ምቱ ቢከሽፍም አይንትራኅት ፍራንክፉርቶች ግን በተከታታይ ባየር ሙይንሽን ላይ 5 ግቦችን አከታትለው ማግባት ችለዋል።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር አምስት ግቦችን ሲያስተናግድ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮአሒም ሎይቭ ተመልካች መሀል ኾነው ታዝበዋል። የባየር ሙይንሽን ፕሬዚደንት ኡሊ ሆኔስ እና የቡድኑ ሊቀመንበር ካርል ሃይንትስ ሩሜኒገ ንዴታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉ መመልከት ይቻል ነበር። ወዲያውም ነበር የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች የተሰናበቱት።

 የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ የነበሩት ተሰናባቹ ኒኮ ኮቫች
የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ የነበሩት ተሰናባቹ ኒኮ ኮቫችምስል Reuters/M. Dalder

ኒኮ ኮቫች ባየር ሙይንሽንን ለተደጋጋሚ ድል ቢያበቁትም በቀድሞ ቡድናቸው ጉድ በመኾናቸው ግን ተሰናብተዋል። በሻምፒዮንስ ሊጉ የእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስፐርን 7 ለ2 የግብ ጎተራ ማድረግ ቢችሉም ከመሰናበት አልዳኑም። በቅዳሜ ሽንፈት አሰልጣኙ ብቻ ሳይኾኑ ቶማስ ሙይለርም ከቡድኑ ሊለይ መኾኑን የቀድሞው የባየር ሙይንሽን ተጨዋች ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ለጀርመን ጋዜጣ ተናግሯል።

ራግቢ

የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ቡድን የብሪታንያ አቻውን ልቆ የዘንድሮ የዓለማችን የራግቢ ዋንጫን ማንሳት ችሏል
የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ቡድን የብሪታንያ አቻውን ልቆ የዘንድሮ የዓለማችን የራግቢ ዋንጫን ማንሳት ችሏልምስል Getty Images/C. Spencer

በዓለም የራግቢ ውድድር የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ቡድን የብሪታንያ አቻውን ልቆ የዘንድሮ የዓለማችን የራግቢ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። የደቡብ አፍሪቃ ቡድን በራግቢ ውድድር ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ለድል ሲበቃ የጆሐንስበርግ ጎዳናዎች በፌሽታ ደምቀዋል።

የደቡብ አፍሪቃ ቡድን ዘንድሮ በአስደናቂ ኹኔታ ለድል የበቃው የብሪታንያ ቡድንን 32 ለ12 በማሸነፍ ነው። የደቡብ አፍሪቃ ቡድን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1995 እና 2007ም ማሸነፍ የቻለ ጠንካራ የራግቢ ቡድን ነው።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቱርክ ኢስታንቡል ማራቶን እና ቻይና ውስጥ በተከናወነው የቤጂንግ ማራቶን በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ ድል ተቀዳጅተዋል። በ41ኛው የኢስታንቡል ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ኂሩት ጥበቡ ስታሸንፍ 35 ሰከንድ ቆየት ብላም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ትእግስት ባይቸው ኹለተኛ መውጣት ችላለች።

ኂሩት አሸናፊ የኾነችው 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ በመሮጥ ነው። በቤጂንግ ማራቶን ደግሞ አትሌት ሱቱሜ አሰፋ በሴቶች ፉክክር አሸናፊ ኾናለች። ሱቱሜ ያሸነፈችው2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ በመሮጥ ነው። አትሌት ዳንኤል ፒፕኮሬ ኪቤት ባሸነፈበት የኢስታንቡል ማራቶን የወንዶች ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ይታያል አጥናፉ ዘሪሁን 2ሰአት፤ ከ9 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ በመሮጥ የኹለተኛ ደረጃን አግኝቷል።

የመኪና ሽቅድምድም

Formel 1 Großer Preis von Mexiko | Lewis Hamilton
ምስል REUTERS

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት ለስድስተኛ ጊዜ የዓለማችን ምርጡ አሽከርካሪ በመኾን አሸናፊ ኾኗል። በትናንቱ የአውስቲን ውድድር ድል የተቀዳጀው ሌዊስ ሐሚልተን በጀርመናዊው የቀድሞ ባለድል ሚሻኤል ሹማኸር የተያዘውን የሰባት ጊዜያት የዓለማችን ምርጥ አሽከርካሪነት ክብረ-ወሰን ለመስበር ተቃርቧል።

ሌዊስ ለስድስተኛ ጊዜ የዓለም ምርጥ የመኪና አሽከርካሪነት ክብርን የተቀዳጀው የዘንድሮ አጠቃላይ ውድድር ሊጠናቀቅ ገና ኹለት ዙር ውድድሮች እየቀሩ ነው። ዘንድሮ ከአውስትራሊያ ግራንድ ፕሪ አንስቶ ትናንት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እስከተከናወኑት 19 ዙር ፉክክሮች ሌዊስ ሐሚልተን 381 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል።  በትናንቱ ነጠላ ፉክክር በእርግጥ ሌዊስ ሀሚልተን ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫልተሪ ቦታስን ተከትሎ የኹለተኛነት ደረጃን ነው ያገኘው። እንዲያም ኾኖ በቀሪዎቹ ኹለት ውድድሮች ቫልተሪ ቢያሸንፍ እና ሌዊስ ባይወዳደር እንኳን ቫልተሪ በ17 ነጥብ አንሶ ነው የዘንድሮ ውድድር የሚጠናቀቀው። እስከትናንቱ ውጤት ብቻ የሌዊስ ሐሚልተን አጠቃላይ ነጥቡ ከቫልተሪ በ67 ነጥብ ይልቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ