1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ግንቦት  7  ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ግንቦት 7 2009

የአርሰናሉ አሰልጣኝ ጫናው በርትቶባቸዋል። ቡድናቸው ስቶክ ሲቲን ቅዳሜ እለት በአስተማማኝ ኹናቴ ድል ቢያደርግም፤ ሊቨርፑል ግን ተስፋቸውን አደብዝዟል። የዘንድሮ ውድድር የዋንጫ ባለቤት ቸልሲ ከዋትፎርድ ጋር ይጋጠማል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች የደጋፊዎች ጠብ ተደጋግሟል።

https://p.dw.com/p/2d0uv
Fußball Liverpool vs Sevilla Europa League
ምስል Getty Images/F.Coffrini

Sport, 15.05.2017 - MP3-Stereo

የአርሰናሉ አሰልጣኝ ጫናው በርትቶባቸዋል። አርሰን ቬንገር ቡድናቸው ስቶክ ሲቲን ቅዳሜ እለት በአስተማማኝ ኹናቴ ድል ቢያደርግም፤ ሊቨርፑል ግን ተስፋቸውን አደብዝዟል። የዘንድሮ ውድድር የዋንጫ ባለቤት ቸልሲ ከዋትፎርድ ጋር ይጋጠማል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች የደጋፊዎች ጠብ ተደጋግሟል። በሳምንቱ ማሳረጊያ የተከሰተው የመቀሌ እና የባሕር ዳር ከተማ ቡድኖች ግጭት የጠቡ ድግግሞሽ አንዱ አካል ኾኖ ተመዝግቧል። በመኪና ሽቅድምድም የትናንቱ  ውድድር አሸናፊው ሌዊስ ሐሚልተን ከመሪው ሠባስቲያን ፌትል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችሏል። 

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል። ገና ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቸልሲ ግን የዘንድሮ ዋንጫ ባለቤት መኾኑን አረጋግጧል።  ባለድሉ ቸልሲ ዛሬ ማታ ዋትፎርድን በስታምፎርድ ብሪጅ ያስተናግዳል። በእርግጥ ዛሬ ማታ የሚደርገው ጨዋታ ለቸልሲም ኾነ ለዋትፎርድ የሚቀይረው ነገር የለም።  40 ነጥብ ይዞ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዋትፎርድ ከፕሬሚየር ሊጉ የመውረድ ስጋት የለበትም፤ ከወራጅ ቃጣና ውጪ ነው የሚገኘው። 80 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው ቶትንሀም ሆትስፐርን  በ7 ነጥብ የሚበልጠው ቸልሲ ደግሞ  የዛሬውን ጨዋታ የሚያከናውነው ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ለማሟላት  ሲል ብቻ ነው። 

West Ham United
ምስል Getty Images/D. Istitene

ይልቅ በፕሬሚየር ሊጉ በአጓጊነታቸው እጅግ የሚጠበቁ ጨዋታዎች ሊቨርፑል፣  ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ናቸው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀሩት ሊቨርፑል 73 ነጥብ ይዞ ደረጃው ሦስተኛ ነው። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሯቸው ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። 

በፕሬሚየር ሊጉ 69 ነጥብ ይዞ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል  ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል። አርሰናል በፕሬሚየር ሊጉ አራተኛ ደረጃ ይዞ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ የግድ ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ማሸነፍ ብቻም አይደለም ወይ ሊቨርፑል አለያም ማንቸስተር ሲቲ ቀሪ ጨዋታዎቻቸውን እንዲሸነፉ አጥብቆ መጸለይ ይጠበቅበታል። ለዚያውም ጸሎቱ ከሰመረ ነው። ሁለቱ ቡድኖች እንደ አያያዛቸው ከኾነ በቀላሉ የሚበገሩ አይነት አይመስሉም። 

ሊቨርፑል ትናንት ዌስትሐምን ያንኮታኮተው በሰፋ ልዩነት 4 ለ0 ነው። ለዚያውም በጨዋታ ብልጫ አሳይቶ። ትናንት ለሊቨርፑል በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ 35ኛ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው ዳንኤል ስቱሪጅ ነው። ፊሊፕ ኮቲንሆ ሁለት ግቦችን በተከታታይ፤ እንዲሁም የማሳረጊያዋን ደግሞ ኦሪጂ አስቆጥሯል። ፊሊፕ ኮቲንሆ በ57ኛው እና 61ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ካሳረፋቸው ሁለት ግቦች በተጨማሪ የመጀመሪያዋን ግብ ለዳንኤል ስቱሪጅ አመቻችቷል።  

Premierleague - FC Liverpool - FC Watford
ምስል picture-alliance/Office Sports Photography/S. Stacpoole

በእሁዱ ጨዋታ ወሳኝ የነበረው የሊቨርፑሉ ፊሊፕ ኮቲንሆ ግን በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን ወደ ስፔን ላሊጋ ሊያቀና ይችል ይኾናል እየተባለ ነው። የስፔኑ ኃያል ቡድን ባርሴሎና ፊሊፕ ኮቲንሆ ላይ ዐይኑን አሳርፏል። ፊሊፕ በበኩሉ ለዚያ፦«ደስተኛ ነን» ብሏል፤ ከምንም በላይ ግን አሁን ሊቨርፑል ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ እንዲያልፍ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ እንደሚጠመድ ተናግሯል። 

ሊቨርፑል ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን ለማረጋገጥ አሰልጣኙ ዬርገን ክሎፕ የሚጠብቁት የመጨረሻ ጨዋታቸውን ማሸነፍ ብቻ ነው። የመጨረሻ ጨዋታቸውን ደግሞ የፊታችን እሁድ የሚያከናውኑት ወራጅ ቃጣና ውስጥ ከሚገኘው ሚድልስቦሮው ጋር ነው። 

ማንቸስተር ሲቲ በአንፃሩ ነገ የሚገጥመው ዌስት ብሮሚችን ነው። 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስት ብሮሚች ቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍም ቢሸነፍም ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።  ለማንቸስተር ሲቲ ግን የነገው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነው። ያም በመኾኑ አርሰናል ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍ እንኳን እንዲሸነፉ እና ነጥብ እንዲጥሉ ተስፋ የጣለባቸው ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ የዋዛ አይደሉም።  የኳስ ነገር ግን የሚኾነው አይታወቅም። በዚህም አለ በዚያ አርሰናል ነገ ከሰንደርላንድ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ አሸንፎ በተሰፋ መጠባበቅ ይኖርበታል። 

የአርሰናልን ተስፋ ትናንት ያደበዘዘው የ24 ዓመቱ የሊቨርፑል ወሳኝ ተጨዋች ፊሊፕ ኮቲንሆ በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን 12 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 7 ግቦችን ማመቻቸት ችሏል። ብራዚሊያዊው የሀገሩ ልጅ ኔይማር የሚገኝበት ባርሴሎና ፊሊፕ ኮቲንሆን ይፈልገዋል መባሉን አስመልክቶ ሲናገር፦ «ባርሴሎና ከዓለማችን ምርጥ ቡድኖች አንዱ ነው። እስካሁን ለእኔ የመጣ ነገር የለም፤ ከመጣም በማናጀሬ በኩል ነው፤ አሁን ትኩረቴ ሜዳ ላይ ነው» ብሏል። 

«ከሊቨርፑል ጋር ውል አለን» ያለው ፊሊፕ «ትልቅ ቡድን ለእኔ ፍላጎት እንዳለው በማወቄ ደስተኛ ነኝ። ለሥራዬ ዕውቅና በመኾኑ ደስ የሚል ነገር ነው። ከእኔ የሚጠበቀው ጠንክሮ መሥራት ነው» ሲል የተናገረው ፊሊፕ ኮቲንሆ ታላቅ ቡድን ያለው ሊቨርፑልን «ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ መመለስ አለብን» ሲል ቁርጠኛ አቋሙን አሳውቋል። 

RB Leipzig v Bayern Muenchen - Bundesliga
ምስል Getty Images/AFP/B. Streubel

ፊሊፕ ኮቲንሆ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን ሊቨርፑልን እንደሚሰናበት በተነገረበት ወቅት ሌላኛው ብራዚሊያዊ አጥቂ ሉዋን በ23 ሚሊዮን ፓውንድ ከግሬሚዮ ቡድን ሊመጣ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ብራዚሊያዊው አጥቂ ከግሬሚዎ ቡድን ጋር ያደረገው ውል የሚጠናቀቀው ገና ከ12 ወራት በኋላ ነው። ቡድኑ ብራዚሊያዊውን አጥቂ በኋላ ላይ ከሚያጣው ለሊቨርፑል በደህና ዋጋ ለመሸጥ ሳይገደድ እንዳልቀረ ተገልጧል።  

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ  መሪው ባየር ሙይንሽን  ቅዳሜ እለት ከላይፕትሲሽ ጋር ያደረገው ግጥሚያ እጅግ አጓጊ ነበር። 60ኛው ደቂቃ ላይ ከአሎንሶ በጭንቅላት የተገጨለትን ኳስ ቲያጎ በተመሳሳይ በግንባር ገጭቶ ከመረብ እስኪያሳርፍ ድረስ ባየር ሙይንሽን 3 ለ1 እየተመራ  ነበር።  ባየር ሙይንሽንን አራት እኩል ያደረገችው፤ አላባ የመታት ቅጣት ምት በእለቱ ድንቅ ግብ ኾና ተመዝግባለች። በ95ኛው ደቂቃ ላይ አሪየን ሮበን አምስተኛዋን እና የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሮ በመቦረቅ ከባየር ሙይንሽንን አስጨፍሯል። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ አሁን በባየር ሙይንሽን በ13 ነጥብ ለመራቅ ተገዷል።    

እንደ ሆፈንሀይም ተመሳሳይ 61 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ከአውስቡርግ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ባየርን ሌቨርኩሰን ከኮሎኝ ጋር ሁለት እኩል ሲለያይ፤ ሔርታ ቤርሊን ዳርምሽታትድትን 2 ለ0 ድል አድርጓል። 

ከዚሁ ከእግር ኳስ ግጥሚያዎች ዘገባ ሳንወጣ፦ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች እና ክፍለ ሃገራት የሚከናወኑ የብሔራዊ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች  በተደጋጋሚ የግጭቶች መንስኤ ሲሆኑ ተስተውለዋል። ቅዳሜ እለት መቀሌ ከተማ ውስጥ የተከናወነው የመቀሌ ከነማ እና የባህርዳር ከነማ ቡድኖች ግጥሚያ በደጋፊዎች ግጭት አንድ እኩል የነበረው ጨዋታ ተቋርጧል።  

እስካሁን ድረስ በተደረጉ የብሔራዊ ሊግ ግጥሚያዎች በየሳምንቱ ግጭቶች የመስተዋላቸው ነገር አሳሳቢ ኾኗል። የቅዳሜውን ጨዋታ ግጭትን የዐይን ምስክር ኾኖ እንደታዘበ የገለጠው ነጋ ዘርዑ በእግር ኳስ ጨዋታዎች ወቅት ግጭቶችን ለመከላከል የታጠቁ ፌደራል ፖሊሶችን መመልከት እየተለመደ መምጣቱን ተናግሯል።

Fußball Champions League Bayern München - FC Arsenal
ምስል picture-alliance/sampics/C. Pahnke

የመቀሌ እና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ግጥሚያ ወቅት የነበረው ግጭት ከእግር ኳስ ቡድን ፍቅር ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘት ይንጸባረቅባቸው እንደነበር ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።  ከዚህ ቀደምም ሐዲያ ሆሳዕና ከስልጤ ወራቦ እና ጂንካ ከተሞች ጋር በነበረው ግጥሚያ ተመሳሳይ ግጭቶች መስተዋላቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ለአብነት ያኽል ጠቅሰዋል። በብሔራዊ ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ወቅት የሚከሰቱ ግጭቶች በብሔር ላይ ያተኮሩ መኾናቸው እልባት ሊገኝለት እንደሚገባም አስጠንቅቀዋል።

በፎርሙላ አንድ የባርሴሎና የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተን አሸናፊ በመኾን ከመሪው ሴባስቲያን ፌትል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችሏል።  የፌራሪ እና የመርሴዲስ አሽከርካሪዎቹ ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል እና ሌዊስ ሐሚልተን አሁን የነጥብ ልዩነታቸው  ስድስት ብቻ ኾኗል። ሰባስቲያን ፌትል 104 ነጥብ ሲኖረው፤ ሌዊስ ሐሚልተን 98 ነጥብ ላይ ደርሷል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ፊንላንዳዊው ቫልተሪ ቦታስ በ63 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ይከተላል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ