1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መጋቢት 24 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ መጋቢት 24 2010

የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ረቡዕ ካይሮ ውስጥ ከሊቢያ አቻው ጋር ይጋጠማል። በከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ አንቶኒ ጆሹዋን የሚያስቆመው አልተገኘም። የፕሬሚየር ሊግ፣ የቡንደስ ሊጋ እና የላሊጋ ጨዋታዎችንም እንቃኛለን።

https://p.dw.com/p/2vNcN
Boxen Anthony Joshua vs Joseph Parker
ምስል Reuters/A. Couldridge

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከሊቢያ አቻው ጋር ረቡዕ ግብጽ ካይሮ ውስጥ ይጋጠማል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ማንቸስተር ሲቲ፣ ተከታዩ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል እና በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም በሣምንቱ መጨረሻ ድል ቀንቷቸዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ ቸልሲ ቀዳሚዎቹም ኾኑ ከኋላው የሚገኘው አርሰናል አሸናፊ ኾነው ነጥብ ሲሰበስቡ ለሽንፈት ተዳርጓል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየርን ሙይንሽን የቀድሞው ተቀናቃኙ ቦሩስያ ዶርትሙንድን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶታል።

ከቡንደስ ሊጋው ላለመውረድ ባለፈው ሳምንት ተስፋው ለምልሞ የነበረው ኮሎኝም የቦሩስያ ዶርትሙንድ አይነት እጣ ገጥሞት፤ በከፍተኛ የግብ ልዩነት ተሸንፏል።  በስፔን ላሊጋ መሪው ባርሴሎና ነጥብ ሲጋራ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ፤ ሪያል ማድሪድ እና በደረጃ ሠንጠረዡ አራተኛ የኾነው ቫለንሺያ አሸንፈዋል። በከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ አንቶኒ ጆሹዋን የሚያስቆመው አልተገኘም። 

እድሜያቸው ከ20 በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት ውድድር ትናንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ከቡሩንዲ አቻው ጋር ባደረገው የማጣሪያ ጨዋታ  የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ውድድሩ ጠንካራ እንደነበር የገለጡት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ቡድኑ ለደረሰበት ሽንፈት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ተናግረዋል። እንደ ምክንያትም ከተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች ጋር የእድሜ አለመመጣጠንን ጠቅሰዋል። 

በእርግጥ በኢትዮጵያ እና በቡሩንዲ ተጨዋቾች መካከል የጎላ የእድሜ ልዩነት ነበር? ምናልባት መረጃዎችን ማረጋገጥ ባይቻል እንኳን በአካል ሲታዩ የጎላ ልዩነትስ ይስተዋል ነበር?። የሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ መራኄ አርታኢ ኦምና ታደለ ገዘፍ ያለ ተክለ ሰውነት ያላቸው የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾችን እድሜ በዐይን ብቻ ተመልክቶ መፍረድ ባይቻልም «አንዳንዶቹ ተጨዋቾች ግን የሚያጠራጥሩ ነበሩ» ብሏል። 

Fußball Bundesliga Borussia Mönchengladbach - Mainz 05
ምስል Imago/T. Frey

ሉሲ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ረቡዕ ከሊቢያ አቻው ጋር ግብጽ ካይሮ ውስጥ ይጋጠማል። ብሔራዊ ቡድኑ ስለተጋጣሚው ቡድን ምንም መረጃ እንዳላገኘ አሠልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ገልጠዋል። 

ሉሲዎቹ ረቡዕ እለት ከሊቢያ ቡድን ጋር የማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርጉት በቶታል አፍሪቃ ሴቶች ዋንጫ ለመሳተፍ ነው። 
ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያን በተመለከተ በዓለም አቀፍ መድረክ ሁለት ሰዎች የኢትዮጵያን ስም አስጠርተዋል።  ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ እና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ። 

በሰኔ ወር ላይ ሩስያ ውስጥ የሚደረገው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ለመዳኘት ከተመረጡ ስድስት አፍሪቃውያን መካከል ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ አንዱ መኾናቸው በርካቶችን አስደስቷል። 

በሌላ ዜና ደግሞ ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በጦርነት የተዳቀቀችው የመን ብሔራዊ ቡድኗ ለእስያ አኅጉር ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያልፍ ማስቻላቸውም በርካቶችን አስደምሟል።   

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለስምንት ጊዜያት በተከታታይ በመሸነፍ የዌስት ብሮሚች አልቢኖ ቡድንን ክብር ወሰን የሰበሩት አሰልጣኝ አላን ፓርዴው ዛሬ ከቡድኑ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰናበታቸው ተገልጧል። የ56 ዓመቱ አሰልጣኝ የቀድሞው አሰልጣኝ ቶኒ ፖሊስ ከተባረሩ በኋላ በዌስት ብሮሚች የቆዩት ለአራት ወራት ብቻ ነበር። ቡድኑን ከገባበት አዘቅት ያወጡታል በሚል ተጠብቀው የነበሩት አሠልጣኝ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ዌስት ብሮሚች ከቀሪ አጠቃላይ ስድስት ግጥሚያዎቹ ሦስቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመኾን ከሚፋለሙት ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል እና ቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ነው። ቅዳሜ እለት በደጋፊዎቹ ፊት በበርንሌይ 2 ለ1 የተሸነፈው ዌስት ብሮሚች በአኹኑ ወቅት 20 ነጥብ ብቻ ይዞ የፕሬሚየር ሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል።

UEFA Champions League Achtelfinale | Manchester United - FC Sevilla
ምስል Getty Images/AFP/O. Scarff

ከትናንት በስትያ ስዋንሲ ሲቲን 2 ለ0 ያሸነፈው እና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ዩናይትድ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ የኾነው ሊቨርፑልን በ2 ነጥብ ይበልጠዋል።  32ኛ የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታውን ከክሪስታል ፓላስ ጋር  ቅዳሜ ዕለት አከናውኖ 2 ለ1 ያሸነፈው ሊቨርፑል 66  ነጥብ አለው። ቶትንሃም ሆትስፐር ቸልሲን ትናንት 3 ለ1 ኩም አድርጓል፤ 64 ነጥብ ይዞ ሊቨርፑልን ይከተላል። ተሸናፊው ቸልሲ በ56 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ስቶክ ሲቲን ትናንት 3 ለ0 ድል ያደረገው አርሰናል 51 ይዞ ስድስተኛ ነው። ከሊቨርፑል በስተቀር ሁሉም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል።  

በሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ከደረሱ ቡድኖች መካከል ሦስቱ በየሀገራቸው የሊግ ፉክክሮች ቀዳሚ በመኾን ዋንጫ ለመሸለም ጫፍ የደረሱ ናቸው። ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እንዲሁም ከጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በሚቀጥለው ሳምንት አለያም በዚያኛው ዋንጫውን በእጃቸው እንደሚያስገቡ ይጠበቃል። ለሻምፒዮንስ ሊጉ ሩብ ፍጻሜ የፊታችን ረቡዕ ወደ ሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ አቅንቶ ሊቨርፑልን የሚገጥመው ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ ተከታዩ ማንቸስተር ዩናይትድን በ16 ነጥብ ርቆታል።  

በቡንደስ ሊጋው አስተማማኝ ነጥብ ያለው የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን ነገ የስፔኑ ሴቪላን ይገጥማል ። ባየር ሙይንሽን በቡንደስሊጋው ከትናንት በስትያ ዶርትሙንድን 6 ለ0 አበራይቷል።  ኮሎኝም በሆፈንሐይም ተመሳሳይ እጣ ደርሶበታልበስፔን ላሊጋ የደረጃ ሰንጠረዡን በ9 ነጥብ ልዩነት የሚመራው ሌላኛው የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ ባርሴሎና የፊታችን ረቡዕ የጣሊያኑ ሮማን ያስተናግዳል። 
ከባርሴሎና በ13 ነጥብ ርቀት ሦስተኛ ደረጃ ይዞ የሚከተለው ሪያል ማድሪድ ነገ የጣሊያኑ ጁቬንቱስን ይፋለማል። ጁቬንቱስ በአውሮጳ ቡድኖች ሌላኛው ኃያል ቡድን ነው። በዚነዲን ዚዳን የሚሠለጥኑት ሪያል ማድሪዶች ነገ የሚፋለሙት በጣሊያን ሴሪ ኣ በ78 ነጥብ መሪ ከኾነው ጁቬንቱስ ጋር ነው። 

Spanien Roberto Carlos 2003
ምስል picture-alliance/dpa/A. Scheidemann

የከባድ ሚዛን ቡጢ

የሆሊውድ ፊልም ከፊል ትእይንት በተቀረጸበት የፕሪንሲፓሊቲ ስታዲየም በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ብሪታንያዊው አንቶኒ ጆሹዋ ድል አድርጓል። አንቶኒ ከትናንት በስትያ ከኒውዚላንዱ ቡጢኛ ጆሴፍ ፓርከር ጋር ባደረገው ግጥሚያ አይበገሬነቱን አስመስክሮ በድል ጎዳና እየገሰገሰ ነው። በዓለማችን የከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ ፈጽሞ የማይረታ ቡጢኛ ለመባልም አንቶኒ የቀረው አንድ ቀበቶ ብቻ ነው። 

አንቶኒ ጆሹዋ እስካሁን ያደረጋቸው 21 ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎችን ከዚህኛው በስተቀር ያሸነፈው በዝረራ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 የኦሎምፒክ ባለድሉ አንቶኒ ቅዳሜ ዕለት ያሸነፈው ሦስቱም ዳኞች በሰጡት ግልጽ የኾነ አጠቃላይ የነጥብ ልዩነት ነው። ሦስቱም ዳኞች  118-110፣ 118-110 እንዲሁም 119-109 ነጥብ በመስጠት ነው አንቶኒ ጆሹዋ አሸናፊ እንዲኾን ያደረጉት።

Boxen Anthony Joshua vs Joseph Parker
ምስል picture-alliance/empics/N. Potts

የዓለማችን የከባድ ሚዛን ኃያል ቡጢኛ አቻ የለሽ ባለድል ለመሰኘት በዴኦንታይ ዊልደር የተያዘው የዓለም የቡጢ ምክር ቤት  (WBC) ቀበቶ ብቻ ይቀረዋል። ከወዲሁ ታዲያ አንቶኒ ጆሹዋ ራሱን «የዓለማችን መጥፎው ሰው» ሲል ሰይሟል።

የአንቶኒ ጆሹዋ እና የጆሴፍ ፓርከር ግጥሚያ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የስታዲየሙ ታዳሚዎች የቡጢ ተፋላሚዎች ስም ሲጠራ በድጋፍ እና በጩኸት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የብሪታንያው ኮከብ አንቶኒ ጆሹዋ፣  የዝነኛው ሹገር ሬይ ሊዮናርድ እና የከባድ ሚዛን ቡጢ የዓለም ባለድሉ ዴኦንታይ ዊልደር ስሞች ሲጠሩ ስሜታቸውን በጋራ እንዲገልጡም ተጠይቀው ነበር።  የተመልካቾች አጸፌታ የተቀረጸው ለcreed 2 ፊልም ሲኾን፤ በእለቱ የከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያውን ለመከታተል  80,000 ተመልካቾች በሥፍራው ተገኝተው እንደነበር ተዘግቧል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ