1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፓኝ፤ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ባለቤት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 6 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በስፓኝ የዋንጫ ድል ተከናውኗል።

https://p.dw.com/p/OHOK
የማድሪድ ፈንጠዝያምስል AP

ስፓኝ የመጀመሪያ ለሆነው የዓለም ዋንጫ ድሏ የበቃችው ኔዘርላንድን በተጨማሪ ሰዓት ውስጥ 1-0 በመርታት ነው። የዝግጅቱ ስኬት የአገሪቱን የመስተንግዶ ብቃት አጠያያቂ ሲያደርጉ የቆዩትን ተጠራጣሪዎች ሁሉ ጸጥ ሲያሰኝ ሂደቱ ደቡብ አፍሪቃን ብቻ ሣይሆን መላውን የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ነው ያኮራው። የ 92 ዓመቱ አንጋፋ የደቡብ አፍሪቃ የነጻነት መሪ ኔልሰን ማንዴላም ባለፈው ምሽት በጆሃንስበርጉ ሶከር-ሢቲይ ስታዲዮም በአካል መገኘታቸው መዝጊያውን ስነ-ስርዓት የበለጠ ክብር አጎናጽፎታል። የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር የእግር ኳስ ጥበብ በጉልበት የአጨዋወት ዘይቤ ላይ፤ የቡድን አጨዋወትም በግለሰብ ተውኔት ላይ አይለው የታዩበት ነበር።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከአንድ ወር በፊት በደመቀ ሁኔታ የተከፈተው 19ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ባለፈው ምሽትም በአስደናቂ ትርዒት ታጅቦ ተፈጽሟል። ደቡብ አፍሪቃ ለውድድሩ ያዘጋጀቻቸው አሥር ስታዲዮሞች በውበታቸው ታላቅ አድናቆትን ሲያተርፉ የአገሪቱ የተፈጥሮ ውበትና የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነትም በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን አገር ጎብኚኛ የስፖርት አፍቃሪ እጅጉን ነው የማረከው። የተፈራው የአደባባይ ወንጀልም ሆነ የጸጥታ አደጋ ቢቀር የታሰበውን ያህል አልታየም። የአገሪቱ የዝግጅት ብቃትም የዓለም አግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር እንዳሉት በጣሙን የሚያኮራ ነው።

“አፍሪቃ ልትኮራ ይገባታል”

ወደ ፍጻሜው ግጥሚያ ሻገር እንበልና እጅግ የደመቀና ያሸበረቀ የመዝጊያ ትርዒትን ተከትሎ በተካሄደው ጨዋታ ስፓኝ ኔዘርላንድን በተጨማሪ ሰዓት 1-0 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ጨዋታውን 84,490 የስፖርት አፍቃሪዎች በጆሃንስበርጉ ሶከር-ሢቲይ ስታዲዮም ተገኝተው ሲመለከቱ በዓለም ዙሪያም ከ 700 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ በቴሌቪዥን አማካይነት በቀጥታ ተከታትሎታል። በነገራችን ላይ ስፓኝ ለፍጻሜ ስትደርስ በዓለም ዋንጫው ውድድር የ 80 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። እንዲህም ነውና ታዲያ የጎል አግቢው የአንድሬስ ኢኒየስታ ደስታ ወሰን አልነበረውም።
“ሊያምኑት ያዳግታል። ሊረዱት የሚከብድ ነው። ጨዋታው ቀላል አልነበረም። ብዙ ጉልበት ፈጅቷል። እንዲህም ሆኖ ግን የዓለም ዋንጫን ማሸነፍ የተለየ ነገር ነው”

ታሪክ ላይ ካተኮርን አንድ የአውሮፓ አገር በዓለም ዋንጫው ውድድር ከአውሮፓ ውጭ የዋንጫ ባለቤት ሲሆን ስፓኝ እንዲሁ የመጀመሪያዋ ትሆናለች። እርግጥ የትናንቱ ፍጻሜ ግጥሚያ በአብዛኛው ግሩም ጨዋታ የታየበት አልነበረም። ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት የሚጠየቁት የስፓኝን የኳስ ጥበብ በሃይል ለማክሽፍ እርግጫን የመረጡት የኔዘርላንድ ተጫዋቾች ናቸው። ሰባት የኔዘርላንድ ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ ሲሰጣቸው አንድ ደግሞ ወደ መጨረሻው ላይ ቀይ አግኝቶ ከሜዳ ወጥቷል።
እንግሊዛዊው ዳኛ ሃዋርድ ዌብ ለአምሥት የስፓኝ ተጫዋቾችም ቢጫ ካርድ ሲሰጥ የስፓኙ ታክቲካዊ ጠለፋ ወይም ግፊያ ግን ከኔዘርላንዱ እርግጫ የሚወዳደር አልነበረም። በጥቅሉ ስፓኝ በመሃል ሜዳ ኮከቧ በአንድሬስ ኢኒየስታ አማካይነት በ 116ኛዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረቻት ግሩም ጎል ለዋንጫ ስትበቃ የእግር ኳስ ጥበብ በጉልበት አጨዋወት ላይ ድል መትቷል። የዚህ የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ውድድር አንዱ ትልቅ ነገርም ይሄው ነው።

“ከባድ ጨዋታ ነበር። ብዙ ትግል የተመላበት። ግን ግሩም ተጫዋቾች ስላሉን ልንወጣው ችለናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ውስጥ ቆጠብ ብለን ነበር የተጫወትነው። እንዲያ ባይሆን አንድ ተጨማሪ ጎልም ልናስገባ በቻልን ነበር። የሆነው ሆኖ ድሉ የሚገባን ነው እላለሁ”

የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቪንሤንቴ-ዴል-ቦስከ! እርግጥ ኔዘርላንድ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደም እ.ጎ.አ. በ 1974 ጀርመን ውስጥ፤ ከዚያም በአራት ዓመቱ በ 1978 አርጄንቲና ውስጥ በተከታታይ ለፍጻሜ ደርሳ ሁለቴም ስትሽነፍ ትናንት ከ 32 ዓመታት በኋላ ያለፈው ታሪክ እንዳይደገም በተጫዋቾቹ ዘንድ የነበረው ጭንቀት የተሰወረ አልነበረም። አለበለዚያ ቡድኑ ከኋላ እስከፊት ለወትሮው ያልተለመደ የተራጋጭነት ባሕርይ ባልታየበትም ነበር።

ለነገሩ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ መድረሱ ራሱ ታላቅ ክብር ሲሆን በጥሩ ጨዋታ ዕድልን መሞከሩ ምናልባት ፍሬ ሊሰጥም በቻለ! የሆነው ሆኖ የአውሮፓው ሻምፒዮን የስፓኝ ቡድን በአጨዋወት ልዕልናው በሚገባ ነው የዓለም ዋንጫን ያገኘው። በረኛ አምበሉ ኢካር ካሢያስ፤ የመሃል ሜዳው የኳስ ጠቢባን ኢኒየስታ፣ ሻቪ፣ አሎንሶና ፋብራጋስ፤ የክንፍ መንኮራኩሮቹ ሴርጆ ራሞስና ካፕዴቪላ፤ ተከላካዩ ካርልስ ፑጆል፤ እንዲሁም አጥቂዎቹ ዴቪድ ቪያና ፌርናንዶ ቶሬስ፤ አጨዋወታቸው ራሱ እንደ ስማቸው ልዩ ጣዕም ያለው ሙዚቃ ነበር።

Flash-Galerie WM 2010 Südafrika Finale Abschlussfeier
የሶከር-ሢቲይ ስታዲዮም ትርዒትምስል AP

የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ድል በአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ቀይና ወርቃማ ቀለማት ባሸበረቀው የማድሪድ ማዕከል በተሰበሰበው ሕዝብ ከተማይቱ አይታው በማታውቀው የደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። የደስታው ጩኸት፣ ጥሩምባው፣ ርችቱና የአውቶሞቢሉ ሰልፍ አቻ አልነበረውም። የስፓኝ ድል ከስፖርቱ አንጻርም በተለይ የኳስ አፍቃሪዎችን ሊያስደስት የሚገባው ነው። ስፓኝ በየጊዜው ያፈራቻቸው ለምሳሌ አንድ እንኳ ለመጥቀስ ራውልን የመሳሰሉ ከዋክብት ለዓለም የእግር ኳስ ተመልካች ብዙ ደስታን አካፍለዋል። የስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ቀደምት ክለቦች ባርሤሎና፣ ሬያል ማድሪድ፣ ሤቪያ፣ ቫሌንሢያ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ወዘተ. ለአውሮፓ እግር ኳስ ውበቱ ናቸው። ቪቫ ኤስፓኛ! እንኳን ደስ ያላችሁ እንላቸዋለን።

19ኛው የዓለም ዋንጫ ውድድር ታላቅ ወይም ሃያል ሲባሉ የኖሩ በተለይም የአውሮፓ ቡድኖች ራሳቸውን ሳይሆን ጥላቸውን መስለው የታዩበትም ነበር። የፈረንሣይ ብሄራዊ ቡድን በውስጣዊ ጭቅጭቅና መነቃቀፍ ተወጥሮ በአሳፋሪ ሁኔታ ከውድድሩ ሲወጣ ያለፈው የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኢጣሊያም በምድቧ ኒውዚላንድን እንኳ ማሸነፍ ተስኗት የደበዘዘ ስንብት ነው ያደረገችው። የእንግሊዝም ዕጣ ቢሆን ብዙም የተሻለ አልነበረም። ቡድኑ ምንም እንኳ የምድቡን ዙር በሁለተኝነት ቢያልፍም በመጀመሪያው ጥሎ ማለፍ ግጥሚያ በጀርመን 4-1 ተቀጥቶ መውጣቱ ሲከነክነው የሚኖር ነው።

ሶሥቱ የአውሮፓ ቀደምት አገሮች ኳስ መጫወቱ ተስኗቸው ከውድድሩ ቀድመው ሲወጡ በሌላ በኩል ለዋንጫ ትልቅ ዕድል ተሰጥቷቸው የነበሩት ብራዚልና አርጄንቲና መሰናበታቸውን ግን እስከ ሩብ ፍጻሜው የተነበየው አልነበረም። በከዋክብት የተመሉት ሁለቱ የላቲን አሜሪካ አገሮች የከሰሩት በችሎታ ማነስ ሣይሆን ብቃትን በሙሉ ልብ ባለመጠቀምና የሚገባውን ያህል ለትግል ዝግጁ ባለመሆን እንደነበር በግልጽ የታየ ጉዳይ ነው። በተለይ እንደ ተጫዋች ማንም የማይስተካከለው የአርጄንቲናው አሠልጣኝ ዲየጎ ማራዶና በድል ስንብት ቢያደርግ ምንኛ ባስደሰተ ነበር። የትግል ስሜትን ካነሣን የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር በተለይ የቡድን እንጂ የግል ተጫዋቾች ተውኔት የጎላበት አልነበረም። ለዚህም ነው ዝነኞቹ ሊዮኔል ሜሢ፣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ ዌይን ሩኒይ ወይም ካካ ወሣኝ ሚና ሊኖራቸው ያልቻለው።

ከአፍሪቃ ቡድኖች መካከል የወጡት ወጥተው ጋና ብቻ በግሩም ጨዋታ ዓለምን ስትማርክ ዕጅ የገባ የመሰለው የግማሽ ፍጻሜ ተሳትፎ ለጥቂት ነበር ያመለጣት። ጋና ለግማሽ ፍጻሜው ደርሳ ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያዋ የአፍሪቃ አገር በመሆን ታሪክ ባስጻፈች ነበር። ግን አልሆነም። ይሁን እንጂ የጋናው ብካክ-ስታር ብሄራዊ ቡድን የመላው አፍሪቃ አለኝታና ኩራት ሆኖ ነው ከውድድሩ የተሰናበተው። ደቡብ አፍሪቃም ቢሆን ፈረንሣይን አሽንፋ ለጥቂት በምድብ ዙሩ ብትወሰንም በዝግጅትና በመስተንግዶዋ ግን የዓለም ሻምፒዮን ልትሆን ለመብቃቷ አንድና ሁለት የለውም።

“አፍሪቃ ይህን የዓለም ዋንጫ ውድድር በማዘጋጀቷ ልትኮራ ትችላለች”

Deutschland Platz 3 WM Südafrika 2010 NO FLASH
ምስል AP

ከስፓኝና ከኔዘርላንድ ሌላ በተለይ ጎልቶ የታየ የአውሮፓ ቡድን ቢኖር ወጣቱ መጤዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰፊው ያሰባሰበው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ነበር። ቡድኑ በግማሽ ፍጻሜው በስፓኝ ከተገታ በኋላ በመጨረሻ ኡሩጉዋይን 3-2 አሸንፎ ሶሥተኛ ሲሆን በጠቅላላው ውድድር አብዛኛውን ጎል በማስቆጠር ተመልካችን መማረኩም አልቀረም። ከሁሉም በላይ የማይረሳው ደግሞ አርጄንቲናን በሩብ ፍጻሜው 4-0 አደንዝዞ የሸኘበት ሁኔታ ነው። አሠልጣኙ የዓሂም ሉቭ ወጣቱን ቡድን ማወደሱን ቀጥላል።

“ይሄ ወጣት ቡድን እንዴት በቁርጠኝነት ይሰራ እንደነበር፣ እንዴት በራሱ ይተማመን እንደነበርና በአጠቃላይ እንዴት ግሩም የማጥቃት አጨዋወት እንዳሳየ ሳስብ በጣም ነው የምደነቀው። በቡድኑ ሙሉ በሙሉ፤ በጣሙን ደስተና ነኝ”

ሌላስ! በየአራት ዓመቱ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር እንደተለመደው ዘንድሮም የውድድሩ ድንቅ ተጫዋቾችና ጎል አግቢም ተመርጧል። ለስፓኙ አትሌቲኮ ማድሪድ የሚጫወተው የኡሩጉዋዩ ኮከብ ዲየጎ ፎርላን የውድድሩ ድንቅ ተጫዋች በመባል ሲሰየም ግሩም በረኛ የሆነው ደግሞ የስፓኙ አምበል ኢካር ካሢያስ ነው። ከሁሉም በላይ ያስደነቀው እስከ አንድ ዓመት ገደማ በፊት ድረስ የሶሥተኛ ዲቪዚዮን ተጫዋች የነበረው የ 21 ዓመቱ ወጣት የጀርመን አጥቂ ቶማስ ሙለር በጎል አግቢነትና ድንቅ ወጣት ተጫዋች በመባል መመረጥ ነው። ሙለር በውድድሩ እንደ ስፓኙ ዴቪድ ቪያ ሁሉ አምሥት ቢያስቆጥርም ቅድሚያ የተሰጠው ብዙ በማቀበል ለሌችንም ለጎል በማብቃቱ ነው።

እንግዲህ ድንቁና በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በአኩሪ ሁኔታ ተጠቃሏል። መጪው የዛሬው አራት ዓመት ብራዚል ውስጥ የሚካሄደው ነው። ፕሬዚደንት ሉላ-ዳ-ሢልቫ ባለፈው ሣምንት የደቡብ አፍሪቃ ጉብኝታቸው አገሪቱን በዝግጅት ብቃቷ በማወደስ ብራዚል ደግሞ የበለጠ እንድታደርግ ትምሕርት መቅሰማቸውን ነው የተናገሩት።

“በመጀመሪያ ደቡብ አፍሪቃን ለዚህ ግሩምና ምን ጊዜም የማይረሣ የዓለም ዋንጫ ዝግጅት እንኳን ደስ ያለሽ እላለሁ። የዓለም ዋንጫው ለመላው የዓለም ሕዝብና ክፍለ-ዓለማት የሚያሳየው አፍሪቃውያን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆኑ፣ የፈጠራ ችሎታና የዝግጅት ብቃት እንዳላቸው ነው። ከዚህም ትምሕርት እየቀሰምን ነው፤ በ 2014 ብራዚል ውስጥ የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ውድድር በሚገባ ለማሳካት”

የዓለም ዋንጫው ውድድር ደቡብ አፍሪቃውያንን በአንድ ለማስተሳሰር የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በቱሪዝምና በኤኮኖሚ ረገድም እንዲሁ የዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጉ እንደማይቀር የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ግሩም! ደቡብ አፍሪቃ! መላው ክፍለ-ዓለም ኮርቶብሻል። መሥፍን መኮንን ተክሌ የኋላ