1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስጋት ያስከተለው የአንበጣ መንጋ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 26 2012

በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ከአካባቢው ጨርሶ ለማስወገድ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል እርጭት እንዲደረግላቸው አርሶ አደሮች ጠየቁ፣ መንግስት በበኩሉ የኬሚካል እርጭት  ለማድረግ ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም ብሏል፡፡ ኅብረተሰቡ በባህላዊ ዘዴ ለማስወገድ እየታገለ ነው።

https://p.dw.com/p/3SZug
Heuschreckenplage in Äthiopien
ምስል Ali Mekonnen

«አንበጣና ባህላዊ የመከላከል ዘዴ»

 በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች የአንበጣ መንጋ በ6 የገጠር ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ተከስቶ በማሽላ ሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብሎቻቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው አርሶ አደሮች አመልክተዋል። በባህላዊ መንገድ አንበጣውን ለማባረር የተለያዩ ዘዴዎችን ቢጠቀሙም ጨርሶ እንዳልጠፋ ነው አርሶ አደሮች የሚናገሩት። በመሆኑም መንግሥት አውሮፕላን ተጠቅሞ በኬሚካል እርጭት አንበጣውን አንዲስወግድላቸው ጠይቀዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪ ኃላፊ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል እንደገለፁት በዞኑ በ24 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋ መከሰቱን አመልክተው ከፍተኛ የመከላከል ስራ በመሰራቱ አሁን በሁለት ቀበሌዎች ብቻ ተወስኖ እንደሚገኝና የማባረር ስራው በባህላዊ መንገድ እንደቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

Heuschreckenplage in Äthiopien
ምስል Ali Mekonnen

በ11 ሺህ ሄክታር ላይ የአንበጣ መንጋው እንደተከሰተ የተናገሩት ዲያቆን ተስፋሁን በ35 ሄክታር የማሽላ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡ የራያ ቆቦ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ዳኜ ደሳለ በበኩላቸው በአውሮፕላን የታገዘ እርጭት ለማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመው፣ በሁለት ቀበሌዎች ያለውን አንበጣ ለማስወገድ ባህላዊ ስራው ቀጥላል ብለዋል፡፡ ደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰኢድ እንዳሉት ደግሞ አንበጣ በዞኑ 3 ወረዳዎች ተከስቶ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከባህላዊ መከላከል ውጪ ኬሚካል በአውሮፕላን በመጠቀም ለመርጨት ተፈጥሯዊ የአካባቢው አቀማመጥ አስቸጋሪ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ የአንበጣ መንጋ ከጥቅምት ወር መግቢያ ጀምሮ በአፋር፣ በትግራይና በአማራ ክልለሎች አንዳንድ ወረዳዎች ተከስቷል፡፡ የባሕርዳር ዘጋቢያችን ዓለምነው መኮንን አንበጣውን ለመከላከል እየታገሉ የሚገኙ አርሶአደሮችን እና የሚመለከታቸውን ወገኖች በማነጋገር ዝርዝሩን ልኮልናል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ