1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስርዓት የጠፋባት አይቮሪኮስት

ሐሙስ፣ ሰኔ 23 1997

በአይቮሪኮስት ዓመታት ያስቆጠረዉን ግጭት ለማረጋጋት የሚያስችል ዉይይት በደቡብ አፍሪካ ተካሄደ። በተጨማሪም በመንግስትና በአማፂዉ ቡድን ተወካዮች መካከል የሰላም ዉይይት በፕሪቶሪያ በዚሁ ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/E0jq

በአገሪቱ የሚዋጉት ቡድኖች ምንም እንኳን ከሁለት ዓመታት በፊት ፓሪስ ላይ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም አንዱ አንዱን ምክንያት እያደረገ ተደጋገሚ ግጭቶች ከዚያ ወዲህም ተቀስቅሰዋል። ባለፈዉ ሚያዝያ ወርም ፕሪቶሪያ ላይ ትጥቅ መፍታትን አስመልክቶ የተደረገዉ የስምምነት ሙከራም ከሽፏል።
የሰላም ስምምነቱ በእንጥልጥል በመቆየቱም የመንግስትና የአማፅያኑ ኃይል የሚገኝበት የግጭት ወረዳ በተባበሩት መንግስታት የአይቮሪኮስት የሰላም አስከባሪ ቡድን ተለይቶ ቁጥጥር እየተደረገበት ነዉ። አሁንም ደቡብ አፍሪካ የሽምግልናዉን የኃላፊነት ተግባር ተረክባ ቀጥላለች።
በአይቮሪኮስት የሚገኘዉ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ቡድን በያዝነዉ ወር መጀመሪያ ላይ ያቀረበዉ ዘገባ እንደሚያሳየዉ በአማፅያኑ የተያዘዉ አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚካሄድበት ሆኗል።
ዘገባዉ ለድርጊቱ ተጠያቂ የሚያደርጋቸዉ የተለያዩ ቡድኖችን ሲሆን ግድያ፤ ማሰቃየት፤ አፈናና ህገወጥ እስር በስፍራዉ እንደሚፈፀምም አጋልጧል።
በድሪጊቱም ባለስልጣናት፤ የመንግስት ደጋፊ የፓርላማ ተመራጮች፤ የተለያዩ ጎሳዎችና ወደአማፅያኑ የተቀላቀለዉ አዲስ ኃይል ሁሉ እጃቸዉ እንዳለበት ዘገባዉ ይገልፃል።
በተለይ ባለፈዉ መጋቢትና ሚያዝያ ወር የተፈፀመዉ የተለያዩ ቡድን አባላትን የማደንና የመግደል ድርጊት መንግስት በዓማፅያን ዓማፅያንም በመንግስት የሚያሳብቡበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ።
የዛሬ ሶስት ዓመት በአገሪቱ የተሞከረዉን መፈንቅለ መንግስት ደግፈዋል በመባል ሶስት ሰዎች በመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ አቢጃን ዉስጥ በፓሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።
ከአራት ቀን በኋላም ሁለቱ ተገድለዉ ከአቢጃን ወጣ ብላ በምትገኘዉ አቦ አካባቢ ተጥለዉ ሲገኙ ስቃይ እንደደረሰባቸዉ አካላቸዉን የተመለከተዉ በአይቮሪኮስት የሚንቀሳቀሰዉ የመንግስታቱ የሰላም አስከባሪ ቡድን ዘግቧል።
ሶስተኛዉ እስረኛ የአይቮሪኮስት ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል ሲሆን ከ18 ቀናት በኋላ በቤቱ አካባቢ ተገድሎ ተገኝቷል።
ከዚያ በኋላ ይላል ዘገባዉ ተራዉ የቀድሞዉ የካቢኔት ሚኒስትር ጀሮሚ ሴሪ አሲያ ነበር። እሳቸዉም በገዛ ቤታቸዉ ታስረዉ ከነቤተሰባቸዉ ስቃይ ደርሶባቸዋል።
በያዝነዉ ወር መጀመሪያም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰዉ ተቃዋሚ ቡድን ማለትም የአይቮሪኮስት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ደጋፊ በሆኑት የቀድሞ ሚኒስትሮች ማቲያስ ናጎንና ፓዉል አኮቶ ያዖ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈፅሟል።
የአገሪቱ መንግስት ይህን ድርጊት በአቢጃን ሽብር እየፈጠሩ ናቸዉ ባላቸዉና ታጣቂ ሽፍቶች በሚላቸዉ ነዉ ያሳበበዉ።
ሆኖም የአይቮሪኮስት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ እንዲህ ያለዉ ድርጊት የሚፈፀመዉ የመንግስት ተቆርቋሪ ነን በሚሉ ወገኖች ነዉ በማለት ድርጊቱን ይኮንናል።
በተጨማሪም በሌላ ወገን ህዝቡ እንዲህ አይነቱን የግድያ ተግባር የሚፈፅሙት በፓርላማዉ የተደራጁ ነፍሰ ገዳዮች ናቸዉ በማለት ይከሳል።
አቢጃን የሚገኙ የፓለቲካ ተንታኝ ደግሞ ምንም እንኳን መንግስት ቢያስተባብልም የሚለብሱት የደንብ ልብስ፤ የሚጠቀሙበት መኪናና ተቃዋሚዎቹን የሚያጠቁበትን የተረጋጋ ስልት የተመለከተ በስልጣን ላይ ካለዉ ወገን ጋር ግንኙነት እንዳላቸዉ ያለጥርጥር ያምናል ይላሉ።
በዚያም ላይ ይህን መሰሉ ጥቃትና የግድያ ተግባር ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምሮ እየተፈፀመ መሆኑ ቢታወቅም በተከሳሽነት መዝገብ ሰፍሮ በወንጀሉ የተጠየቀ ማንም የለም ሲሉም ይጠቁማሉ።
በሌላ በኩል ባለፈዉ ዓመት የአማፅያኙ የተጠናከረ ወረዳ በመባል በሚታወቀዉ የኮሮንጎ ሰሜናዊ ግዛት አካባቢ የመንግስታቱ ቡድን ወደ አንድ መቶ የሚደርሱ ሰዎች በአንድነት የተቀበሩበትን መቃብር አግኝቷል።
እነዚህ ወገኖች የተገደሉት በኮንቴነር ዉስጥ ታሽገዉ እንዲቆዩ ተደርጎ ሲሆን መንስኤዉ በአማጽያኑ መካከል በተፈጠረ መከፋፈል ሳቢያ በተቀሰቀሰ ግጭት እንደነበር ዘገባዉ ያሳያል።
በወቅቱ ምንም እንኳን አለም አቀፉ ህብረተሰብ፤ የአገር ዉስጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የሲቪሉ ማህበረሰብ በአይቮሪኮስት ዉስጥ የሚታየዉ ሁኔታ መንስኤ እንዲጣራ ቢወተዉቱም ድርጊቱ ግራ እንዳጋባ ሳይጣራ በእንጥልጥል ቀርቷል።
አይቮሪኮስት ከቅኝ ግዛት ተላቃ ነፃ ከወጣች በኋላ ለ30 ዓመታት ሰላም የሰፈነባት አገር ሆና ብትቆይም ላለፉት ዓስርታት በሃይማኖትና በጎሳ ልዩነት ሰበብ ለእርስ በርስ እልቂት ተዳርጋለች።
ለግጭቱ፤ ለግድያዉና እየተፈፀመ ላለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣዉ አሁን አይቮሪኮስት ተጠያቂ የሌለባት ስርዓት የጠፋባት ሆናለች።