1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለመድኃኒት ጥራት ተጨንቀዉ ያዉቃሉ?

ሸዋዬ ለገሠ
ማክሰኞ፣ ጥር 8 2010

ድሃ ሃገራት ውስጥ ለሽያጭ ከሚቀርቡ ከ10 መድኃኒቶች 1ዱ እዉነተኛ መድኃኒት እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የጥራት ደረጃቸዉ የወረደ በመሆኑ ፍቱንነታቸዉ መቀነሱ ብቻ ሳይሆን ጨርሶም መድኃኒቶች ያልሆኑ ለገበያ የሚቀርቡት እነዚህ ስመ መድኃኒቶች በሁሉም ሃገራት መገኘታቸዉ እንግዳ ባይሆን በአፍሪቃ ሃገራት ዉስጥ ግን እንደሚበዙም ይነገራል። 

https://p.dw.com/p/2qwQa
Afrika - Medikamente - Markt
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

ስለሀሰት መድኃኒቶች ኅብረተሰቡ በቂ መረጃ ሊኖረዉ ያስፈልጋል

በኢቱሪ ግዛት፤ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ዉስጥ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2014 ታኅሳስ ወር እስከ 2015 ነሐሴ ወር ድረስ 1 ሺህ 29 ሰዎች ምንነቱ በዉል ያልታወቀ በሽታ ስላጋጠማቸዉ በአካባቢዉ በሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የህክምና ጣቢያ ተወሰዱ። ለሰዎቹ የህክም እርዳታዉን ለመስጠት የሞከረዉ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ድርጅት ሲሆን ታማሚዎቹ ላይ ከሚታየዉ ምልክት በመነሳት የሕክምና ባለሙያዎቹ በመጀመሪያ የገመቱት ማጅራት ገትር የሚባለዉን ሕመም ነበር። አንድ ሳምንት ከፈጀ ጥልቅ ምርመራ እና ክትትል በኋላ የችግሩ ምንነት ግልፅ ሆነላቸዉ። ሕመሙን ያስከተለዉ ትክክለኛ ያልሆነ ሰዉነትን የሚያረጋጋ መድኃኒትን በመጠቀም መሆኑም ተረጋገጠ። በዚህ ምክንያትም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ አምስት ልጆችን ጨምሮ 11 ሰዎች ሞቱ።

 የሀሰት መድኃኒቶች ለገበያ መቅረባቸዉን አስመልክቶ የዓለም የጤና ድርጅት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ያካሄደዉ ቅኝት እንደሚያሳየዉ የጥራት ደረጃቸዉ ዝቅተኛ የሆነ ወይም ደግሞ የሀሰት መድኃኒቶችን በገበያ ላይ ማግኘት ለብዙዎች እንግዳ ነገር አይደለም። እንደየዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ይህ ችግር የተወሰኑ ሃገራትን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ነገር ግን በአፍሪቃ ሃገራት ላይ ይጠናል። ድርጅቱ ለዚሁ ጉዳይ መረጃዎችን በሚያሰባስብበት ሂደት 42 በመቶዉን ያገኘዉ ከአፍሪቃ ሃገራት መሆኑን በግልፅ አመልክቷል። በዚህ ምክንያት ማስጠንቀቂያዎችን ካስተላለፈባቸዉ 13 ሃገራትም 11ዱ አፍሪቃ እና አካባቢዋ ያሉ ሃገራት መሆናቸዉንም አስታውቋል። በዓለም የጤና ድርጅት ዉስጥ እንዲህ ያሉ መረጃዎች በቀጥታ የሚመለከታቸዉ ፕሬነተ ቡርዲሎን ስቲቭ የዚህን ምክንያት በሚገባ ያዉቁታል።

«የጥራት ደረጃቸዉ ዝቅተኛ የሆነ እና የሀሰት መድኃኒቶችን የማምረቱ ጉዳይ ባጠቃላይ ትክክለኛ መድኃኒቶችን የማግኘት ዕድል አለመኖር፤ መጥፎ አስተዳደር ወይም ደካማ የቴክኒክ አቅም የሚያመጣዉ ጣጣ ነዉ። ስለደካማ የቴክኒክ አቅም ስናወራ ፤ የቴክኒክ አቅም ድክመት በበርካታ አቅጣጫ መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል። የግድ የብሔራዊ ከመድኃኒት ቁጥጥር አቅምን ብቻ ማለት አይደለም። ስለዚህም እነዚያ ድሃ ሃገራት በዚህ ሁኔታ ዋነኛ ተጎጂ ይሆናሉ። በዚያም ላይ ደረጃዉን ያልጠበቁ እና የሀሰት የመድኃኒት ምርቶች አብዛኛዉን ጊዜ እንዲህ ባሉት አጋጣሚዎች ማለትም በመጥፎ አስተዳደር እና ደካማ የቴክኒክ አቅም እንዲሁም በተዘጉ የአቅርቦት እክል ምክንያት ይገናኛሉ። አንዳንዴም ከዚህ ዉጭ ሊከሰቱ እንደሚችሉም እሙን ነዉ።»

Symbolbild Pillen
ምስል imago/Science Photo Library

እንዲህ ያሉት ነገሮችም በአብዛኛዉ የሚጎዱት ብዙሃኑን የአፍሪቃ ሃገራት ጨምሮ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸዉን ሃገራት መሆኑንም አጽንኦት ይሰጣሉ። አቶ ጳዉሎስ ኃይለ አብ ባይሩ፤ እዚህ ጀርመን ድሬዝደን ከተማ የመድኃኒት መሸጫ ወይም ፋርማሲ ባለቤት ናቸዉ። ሦስተኛዉ ዓለም የሚባሉት ሃገራት እንዲህ ላለዉ የተሳሳተ የመድኃኒት ገበያ የመጋለጣቸዉ መንስኤ በማለት ፕሬነተ ቡርዲሎን ስቲቭ የገለፁትን ያጠናክራሉ።

«በአዉሮጳ እና በአሜሪካን ሃገራት ብዙ ጊዜ አያጋጥምም፤ አልፎ አልፎ ነዉ የሚያጋጥመዉ። ቢያጋጥምም ለትንሽ ጊዜ ነዉ እንጂ ይታወቃል የሀሰት መድኃኒት መሆኑ።  በሦስተኛ ዓለም አገሮች ግን አንደኛ የዋጋ ጉዳይ ነዉ። ሦስተኛ ዓለም አገሮች በተቻለ መጠን ርካሽ መድኃኒት ማስገባት ስለሚፈልጉ ያዉ ነገሩን ማወቁ ችግር ይሆናል ማለት ነው። ሁለተኛ ካፓሲቲም የላቸውም ብዙውን ጊዜ፤ አብዛኞቹ አገሮች መድኃኒቶቹን መርምሮ ትክክለኛ መሆን እና አለመሆናቸውን ለማወቅ ያስቸግራቸዋል። ስለዚህ በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ ይህ ነገር የሚገጥመዉ ወደ ሦስተኛዉ ዓለም አገሮች ነው። ያዉ የገንዘብ ጥያቄ ስለሆነ እሱ ላይ ነው እንጂ በደንብ ላቦራቶሪ ተገብቶ ከሁሉም ሳምፕል እየተወሰደ ቢመረመር ይኸ ነገር ይቀንሳል ወይም በጣም ዝቅ ይላል ማለት ነው። »

«ጀርመን አሁን በቅርብ ጊዜ የዛሬ ሦስት አራት ወር የካንሰር መድኃኒት በጣም ውድ የሆነ የሀሰት መድኃኒት ገበያ ላይ ውሎ ነበር። ግን ከሁለት ሦስት ሳምንት በኋላ ታውቆ በሙሉ መድኃኒቶቹ ተሰብስበው ላቦራቶሪ እንዲገቡ ተደርጎ፤ በትንሽ ጊዜ ውስጥ የሀሰት መድኃኒት መሆኑ ታውቆ ያው ከገባው ወጥቷል ማለት ነው። የዛሬ አንድ ሁለት ዓመትም፤ አንድ የሆነ መድኃኒት እንደዚህ አጋጥሞ ነበር ግን በዚህ አገር ያው ቁጥጥሩም ከበድ ያለ ስለሆነ ይሄን ያህል አያጋጥምም ማለት ይቻላል። አልፎ አልፎ በሦስት አራት ዓመት አንድ ጊዜ ቢገጥም እሱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገኝቶ ወዲያው ርምጃ ስለሚወሰድበት ይሄን ያህል አይገጥምም።»

ያለውን ቁጥጥር ጥንካሬ መሠረት በማድረግ ይህን ይበሉ እንጂ አቶ ጳውሎስ ሰዎች በርካሽ ዋጋ ለማግኘት ሲሉ መድኃኒቶችን በሚገዙባቸው የተለያዩ መንገዶች ምክንያት የተሳሳቱም ሆነ የጥራት ደረጃቸዉ የወረደ ኪኒኖችን አያገኙም ማለት አይደለም። እንዴትነቱን የመድኃኒት ሽያጭ ባለሙያው ያስረዳሉ።

«ጀርመን አገር እንኳን አልፎ አልፎ ይገጥማል፤ አይገጥምም ማለት አይደለም። በተለይ ከፋርማሲ መድኃኒት ከገዛሽ ጥራቱ 99 በመቶ የተረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል። ግን አንዳንድ ሰዉ አሁን መድኃኒት በኢንተርኔት በኩል ያዛል ከሌላም ከሌላም አቅጣጫ ካገኘ ያው ጥራቱ የተጠበቀ ላይሆን ይችላል። እዚህ ላይ ትንሽ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።»

ሰዎችን እንዲህ ያሉ መድኃኒቶች እንዲጠቀሙ የሚገፋፋዉ የዋጋ ውድነት ጉዳይ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ሴራሊዮን ውስጥ የመድኃኒት ተቋም ኃላፊ የሆኑት ዊልትሺር ጆንሰን በበኩላቸዉ ተመሳሳይ ነገር ታዝበዋል። ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት ይላሉ ጆንሰን፤ ድህነቱ ሰዎች በርካሽ ዋጋ የሚገኘውን መድኃኒት እንዲመርጡ ግድ ብሏቸዋል። አምራቾቹም ለገንዘብ ሲሉ የማይሆነውን ይሠራሉ።

Afrika - Medikamente - Markt
መድኃኒት እንደሸቀጥ ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

«ደረጃቸዉ የወረደ እና የሀሰት መድኃኒቶች በዓለም ላይ ሊገኙ የቻሉበት በርካታ ምክንያት አለ። የዚሁ ሁሉ መሠረት ግን በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለሰው ሕይወት ደንታ የሌላቸው ወገኖች መኖራቸው ነዉ። በዚያም ላይ ይህን የሚያባብሱ ሌሎች መንስኤዎችም አሉ፤ ደካማ ሕጎች፤ ደካማ ሕግ አስፈጻሚዎች፤ እንዲሁም መድኃኒት የማግኘት ዕድል መጥበብ ወይም በዋና ደረጃ ድህነት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ምክንያቱም በተለይ ከሰሃራ በስተደቡብ በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ሰዎች ጤናቸውን ለመጠበቅ ርካሽ መድሃኒቶችን የመምረጥ አዝማሚያ አለ።»

ይህንኑ የመድኃኒት ጥራት ጉዳይ መሠረት በማድረግ የዓለም የጤና ድርጅት 100 ግለሰቦችን ጉዳይ ለመመርመር ሞክሯል። ከምርምሩ ያገኘዉ ዉጤት ታዲያ ስጋትን የሚያስከትል ነዉ የሆነዉ። ድርጅቱ ከዚህ ጥናት ተነስቶም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ከሚገኙ መድኃኒቶች በአማካኝ  10,5 በመቶ የሚሆኑት የጥራት ደረጃቸዉ የወረደ ወይም የሀሰት መድኃኒቶች እንደሆኑ አመላክቷል። 

ጥናቱ እንደሚለዉ አብዛኛዉን ጊዜ እንዲህ ያለው ስህተት የሚያጋጥመው የወባ መድኃኒት እና አንቲ ባዮቲክ የሚባሉት መድኃኒቶች ሲሆን የከፋ መዘዝም አላቸው። በመሠረቱ ወባም ሆነ በባክቴሪያ ምክንያት በልጅነት የሚመጣዉ የሳንባ ምች ትክክለኛዉ ህክምና እስከተገኘ ድረስ ሊፈወሱ የሚችሉ የጤና ችግሮች መሆናቸዉ ከተረጋገጠ ረዥም ጊዜያት ተቆጥረዋል። ነገር ግን በእነዚህ የጥራት ደረጃቸዉ ዝቅተኛ በሆነና በሀሰት መድኃኒቶች ምክንያት በየዓመቱ በወባ በሽታ 267 ሺህ እንዲሁም እንደሳምባ ምች ባሉ ልጆችን የሚያጠቁ ህመሞች 20,225 ሕፃናት ከሰሃራ በስተደ ቡብ በሚገኙ ሃገራት እንደዋዛ ህይወታቸዉ ይቀጠፋል።

የዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚቸቁሙት ጥራታቸዉ ዝቅተኛ የሆነና የሀሰት መድኃኒቶች የሚመጡት በአብዛኛው ከቻይና እና ከህንድ ነዉ። የአፍሪቃ ሃገራትን ጨምሮ ብዙዎቹ መንግሥታት ይህን የሚከታተሉበት እና የሚቆጣጠሩበትን መንገድ ዘርግተው እንደሚንቀሳቀሱ ይናገራሉ። ይህን ችግር መከላከል የሚቻልበት ብቸኛው መንገድም ይኸዉ ጠንካራ ቁጥጥር መሆኑ ይታመናል። አቶ ጳዉሎስ እንደሚሉት እዚህ ጀርመን ሀገር በብሔራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በየመድኃኒት መሸጫዉን ቁጥጥሩ ጥብቅ ነዉ።

Produktpiraterie in Deutschland
የሀሰት መድኃኒቶች ስብስብ ናሙናምስል picture-alliance/dpa

«ኖርማሊ ጀርመን ሀገር ጥራት የሌለዉ መድኃኒት ለመሸጥ በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም ቁጥጥሩ ከበድ ያለ ስለሆነ ከሌላ ቦታ አምጥቶ ዝም ብሎ መሸጥ አይቻልም። እኛ ለምሳሌ እዚህ ሥንሰራ እኔ መድኃኒት ሳዝዝ፤ በቀን አትሊስት ከመጣ መድኃኒት ናሙና ወስጄ እያወጣሁ መመርመር አለብኝ። የጅምላ መድኃኒት ሻጩም ቢሆን ሲሸጥ፤ ልክ እንደእኛ ናሙና እያወጣ መመርመር አለበት። አንድ ጥርጣሬ ቢገጥም ሴንትራል ላቦራቶሪ የሚባል አለ የጀርመን ሀገር ፋርማሲስቶች በሙሉ ባለቤትነት የሆነ ድርጅት ፍራንክፈርት አጠገብ አለ፤ ወደዚያ ይላክ እና መድኃኒቶቹ ተመርምረዉ ጥራታቸዉ ይነገራል ማለት ነው።»

የዓለም የጤና ድርጅት ጥራት የሌላቸውን መድኃኒቶች ከገበያ ለማጥፋት ወሳኙ የመንግሥታት ጥንቃቄ ብቻ ሳይሆን ከታች ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ተገቢው መረጃ እንዲኖረዉ ማድረግ መሆኑን ያሳስባል። ከምንም በላይ እንዲህ ያሉ መድኃኒቶችን መጠቀም የሚያስከትለውን የጤና ጠንቅ መረዳቱ ሰዎችን ለርካሽ ዋጋዉ ሲሉ የተሳሳተውን መድኃኒት ከማይሆን ቦታ ከመግዛት እንዲቆጠቡ እንደሚያደርጋቸዉም አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ