1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳይንስ በ2015

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20 2008

በ2015 በሳይንሱ ዓለም በርካታ እመርታዎች ተመዝግበዋል። ናሳ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ሮኬት ወደ ኅዋ አምጥቆ ወደ ምድር መመለሱ ተሳክቶለታል። ቀደም ሲል ወደ ኅዋ የሚወነጨፉ ሮኬቶች ግባቸውን ከፈጸሙ በኋላ እዛው ኅዋ ላይ ተበታትነው እንዲከስሙ ይደረግ ነበር። በፀሐይ ኃይል የሚሠራ አውሮፕላን በረራ ማድረጉም ተሰምቷል በ2015።

https://p.dw.com/p/1HVra
Space X's Falcon 9 Rakete
ምስል Getty Images/AFP/B. Weaver

ሳይንስ በ2015

የሥነ-ፈለክ እና የጠፈር ተመራማሪዎች ኬፕለር የተሰኘች ፕላኔት ማግኘታቸውን አውጀዋል። ኬፕለር ከምድር ጋር ተመሳሳይ ስትሆን በውስጧ የውኃ ክምችት ይዛለችም ተብሏል። ጥንታዊ የሰው ዘር እንደሆነ የተነገረለት ሆሞ ናሌዲ የተሰኘ ቅሪት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የመገኘቱ ዜና ብዙዎችን አነጋግሯል። በሕክምናው ዘርፍ የዘንድሮ የኖቤል ሽልማት እንዲሁም ሌሎች በ2015 የተከናወኑ ዐበይት ክስተቶችን ዳሰሳ ያደረግንበት የሳይንስ እና ኅብረተሰብ ዝግጅታችንን ነው የምትከታተሉት።

የጎርጎሪዮሱ 2015 የናሳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ሐዘንም ስኬትም ያስተናገደበት ዓመት ነበር። ለናሳ የሚሠራው ስፔስ ኤክስ (SpaceX)የተሰኘው ተቋም በሁለተኛ ሙከራው ወደ ኅዋ ያስወነጨፋት ሮኬት ስኬታማ ጉዞ ያደረገችው በ2015 መገባደጃ ላይ ነበር። ልዩ ስሟ Falcon 9 የተሰኘችው ይኽች ሮኬት የተወነጨፈችው ከፍሎሪዳ ዩናይትድ ስቴትስ የናሳ ኬኔዲ የኅዋ ምርምር ማዕከል ነበር። ሮኬቷ ኅዋ ላይ ተንሳፎ ወደ ሚገኘው ዓለም አቀፍ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ተልካ በተሳካ መልኩ ማረፏ ለኅዋ የምርምር ዘርፍ ታላቅ እመርታ ተብሎ ተመዝግቧል።

ስፔስ ኤክስ ከስድስት ወራት በፊት ወደ ኅዋ ሊያመጥቃት የነበረችው ሌላ ሮኬት ገና ከመነሻው ሁለት ደቂቃ ያህል እንደተወነጨፈች ነበር አየር ላይ የፈነዳችው። ሮኬቷ ጭነቷን ወደ ኅዋ ለማጓጓዝ ነበር ግቧ፤ አየር ላይ መክና ቀረች እንጂ። ስፔስ ኤክስ ከናሳ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ጋር በገባው የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ውል መሠረት ነበር የመጀመሪያውን ያልተሳካ ሙከራ ያከናወነው። በሁለተኛው ሙከራ ግን ሮኬቷ የጫነቻቸውን 11 ሳተላይቶች ኦርብኮም ለተሰኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኩባንያ ማድረሱ ተሳክቶላታል። ስፔስ ኤክስ የላካት ሮኬት ሳተላይቶቹን ኅዋ ላይ ወደሚገኘው ጣቢያ አድርሳ ወደ ምድር መመለሷም ሌላኛው ታልቅ እመርታ ነው ተብሏል። ከዚህ ቀደም ወደ ኅዋ የሚላኩ ሳተላይቶች ግባቸውን ከመቱ በኋላ እዛው ኅዋ ላይ እንዲከስሙ ይደረግ ነበር።

በሌላ ዜና ደግሞ ኅዋ ላይ ተንሳፎ ለሚገኘው ለዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ 6 ጠፈርተኞች ዩናይትድ ስቴትስ የገና ስጦታ መላኳም ተደምጧል። ዓለም አቀፍ ጣቢያው ኅዋ ላይ ተንሳፎ በመሬት ዙሪያ ሲሽከረከር 15 አመታትን አስቆጥሯል። ጣቢያው በኅዋ ሳይንስ ላይ ምርምር ለሚያከናውኑ ጠፈርተኞች መኖሪያ እና ቤተ-ሙከራ ሆኖም ያገለግላል። ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ወይም ናሳ ተመራማሪው ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ «ዓለም አቀፍ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ካለው ቅርበት የተነሳ በረራ ሲያደርግ በዐይናችን ማየት እንችላለ» ብለዋል። ይኽ ግዙፉ መንኵራኵር የሩስያ እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታትን ያጣመረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጣቢያው የተገነባው በዩናይትድ ስቴትስ፤ሩሲያ፤አውሮጳ፤ጃፓን እና ካናዳ የኅዋ ማዕከላት ትብብር ነው። ጣቢያው እያንዳንዱ አካሉ በተናጠል ከተጓጓዘ በኋላ በጠፈርተኞቹ እጅ እዛው ሕዋ ላይ እንደተገነባ ይነገርለታል።
ኅዋ ላይ እየተንሳፈፈች ቅኝት የምታደርገው «አዲስ አድማሶች» (New Horizons) የሚል ስያሜ ያላት እናት መንኵራኵር ደግሞ ፕሉቶ የተሰኘችው ፕላኔት ላይ በ2015 አስገራሚ ነገሮችን በምስል አንስታ ወደ ምድር ልካለች። የናሳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ንብረት የሆነችው «አዲስ አድማሶች» እናት መንኵራኵር በፕሉቱ በኩል አድርጋ መብረር የቻለችው ከአምስት ወራት በፊት ነበር።

ፕሉቶ የተሰኘችው ፕላኔት በናሳ እይታ
ፕሉቶ የተሰኘችው ፕላኔት በናሳ እይታምስል picture-alliance/dpa/NASA/JHUAPL/SwRI
የስፔስ ኤክስ (SpaceX)ሮኬት ስትወነጨፍ
የስፔስ ኤክስ (SpaceX)ሮኬት ስትወነጨፍምስል picture-alliance/AP Photo

ከሰሞኑ ግን መንኵራኵሯ በፕሉቶ በኩል ማለፍ ብቻ ሳይሆን አስደማሚ ምስሎችንም በፎቶግራፍ አንስታ ወደ ምድር ልካለች። ምስሎቹ የፕሉቶን ከርሰ-ምድራዊ ገጽታ እና የፕላኔቷን አወቃቀር እንደሚያሳዩ ተገልጧል። ከዚያም ባሻገር በፕሉቱ ከባቢ አየር ያልተጠበቀ ጭጋግ መከሰቱን በፕላኔቷ ቀደም ሲል እና በአሁኑ ወቅት የበረዶ ግግር እንቅስቃሴ እንደሚገኝ አመላክተዋል። የተቦረቦሩ የመሬት ገጽታዎች እና ሸለቆዎች በፕላኔቷ መገኘታቸውም አስደምሟል።

ከዚሁ ከበረራ ዜና ሳንወጣ፤ ከወደ ጃፓን በጸሐይ ኃይል የሚሠራ አውሮፕላን በ2015 የበረራ ሙከራ ማድረጉ ተሰምቷል። 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የስዊዘርላንድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን በገጠመው የባትሪ ችግር ግን ቢያንስ ለ9 ወራት ሃዋዪ አየር ማረፊያ ውስጥ እንዳረፈ መቆየቱ የግድ ነው ተብሏል። አውሮፕላኑ ዓለምን ለመዞር ከጃፓን ኦሃሁ ከተማ በመነሳት የጀመረው ጉዞ ግማሽ በግማሽ መገባደዱም ተጠቅሷል። አውሮፕላኑ በ2016 ሚያዝያ አለያም ግንቦት ወር ላይ ወደ አሪዞና ግዛት የአራት መዓልት-ወሌሊት ጉዞ ለማድረግ ቀጠሮ እንደተያዘለት ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።

ከኅዋ ዜና ሳንወጣ፤ የሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪዎች አንድ አዲስ ፕላኔት ማግኘታቸውን በ2015 ይፋ አድርገዋል። ፕላኔቷ ከመሬት ጋር ተመሳሳይነት አላት ተብሏል። ይኽች ፕላኔት ኬፕለር -452b ትሰኛለች። ስያሜውን ኬፕለር ከተሰኘው አጉልቶ መመልከቻ ግዙፍ መነጽር (ቴሌስኮፕ) ያገኘችው ይኽች ፕላኔት ለሕይወት ተስማሚ የሆኑ ነገሮችን አቅፋ እንደያዘችም ትንታኔ ተሰጥቷል። ይኽም በመሆኑ ኬፕለር 452b፤ የመሬት ዘመድ አዲሷ ፕላኔት የሚል ስያሜ አግኝታለች።

በጸሐይ ኃይል የሚሠራ አውሮፕላን፤ አድማስ ስታዘቀዝቅ
በጸሐይ ኃይል የሚሠራ አውሮፕላን፤ አድማስ ስታዘቀዝቅምስል picture-alliance/Solar Impulse/Jean Revillard

እንደ ሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪዎች ከሆነ ፕላኔቷ የተገኘችው ምድር ከምትገኝበት ፀሐያዊ ጭፍሮች(ጋላክሲ) ውጪ እጅግ በጣም በርቀት ነው። ኢትዮጵያዊው የሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪ ዶክተር ጌታቸው መኮንን ደቡብ አፍሪቃ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፊዚክስ ያስተምራሉ። አዲሷ ፕላኔት ከመሬት እጅግ ከመራቋ የተነሳ በብርሃን ፍጥነት ጉዞ ቢደርግ እንkኳን ፕላኔቷ ላይ ለመድረስ ሦስት ሺህ ዓመት ይፈጃል ብለዋል።

የኬፕለር 452b ውጪያዊ አካል ምናባዊ ገጽታ ምንነት ገና ሙሉ ለሙሉ አልተብራራም። ሆኖም ጠቢባኑ ብርሃንን በመተንተን ፕላ ኔቷ ምናልባትም ከእሳተ-ጎመራ የተገኘ አለታማ ቋጥኞች ሳይኖራት አይቀርም ብለዋል። ፕላኔቷ ዘንድ በዘመኑ የሰው ልጅ ስልጣኔ ታግዞ ለመድረስ የማይሞከር ነው። አንድ ቀን መሆኑ አይቀርም የሚል ተስፋ ግን መሰነቃቸው አልቀረም ሳይንቲስቱ።

ኢትዮጵያ ከሦስት እስከ አምስት አመታት ውስጥ ሳተላይት የማምጠቅ እቅድ እንዳላት የተገለጠው በ2015 ነው። ኢትዮጵያ በእንጦጦ ተራራ ላይ በሁለት ቴሌስኮፖች የመጀመሪያውን የኅዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል ከፍታ ሥራ ከጀመረች ጥቂት ወራት መቆጠሩም ተዘግቧል። ከጀርመን እንደተገዙ በተነገረላቸው ቴሌስኮፖች የምርምር ሥራ መጀመሩን የእንጦጦ ኦብሰርቫቶሪ ወይም እንጦጦ ኅዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ኋላፊ ዶ/ር ሰለሞን በላይ ተናግረዋል።

ወደ ቅሪተ አካል ጥናት ዘገባ ደግሞ እንሻገር። የጥንታዊው ሰውም ሆነ ቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ 2,8 ሚሊዮን ዓመት ገደማ ዕድሜ ያለው መንገጭላ ከ5 ጥርስ ጋር መገኘቱን በ2015 የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ በይፋ ማሳወቃቸውም ይታወሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአፋር ምድር፤ ሌዲ-ገራሩ በተሰኘው የምርምር አካባቢ የተገኘው ቅሪተ አካል LD 350-1 የሚል ሳይንሳዊ መለያ ስም ተሰጥቶታል። ይኽ ቅሪተ አካል የተገኘው በአሪዞና ፌደራል ክፍለ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ትምህርቱን በመከታታል ላይ በሚገኘው ኢትዮጵያዊው ወጣት ሳይንቲስት ቻላቸው መሥፍን ሥዩም ነው። ቅሪተ አካሉ በጥቂት መቶ ሺ ዓመታት ልዩነት ቀደም ሲል ከተገኘችው ማለትም የ 3,2 ሚሊዮን ዓመታት ዕድሜ ካላት ይበልጥ ጦጣ መሰሏ ቅሪተ አካል Australopithecus afarensis ድንቅነሽ (ሉሲ) ይበልጥ ወደ ዘመናዊው ሰው ቅድመ ምስል ይጠጋል ተብሎለታል።

ኬፕለር -452b የተሰኘችው ፕላኔት ከመሬት አንፃር
ኬፕለር -452b የተሰኘችው ፕላኔት ከመሬት አንፃርምስል NASA/Ames/JPL-Caltech/T. Pyle via AP

ይኸው የመጀመሪያው የHomo ቤተሰብ አባል ሳይሆን እንዳልቀረ የተነገረለትን ቅሪተ አካል፤ የዛሬው ዘመን ሰው (Homo Sapiens) እንዲሁም በሂደት የጠፉት ዘመዶቹ፣ Homo Habilis, Homo Erectus እና Neanderthals የጋራ የዘር ሐረግ ግንድ ሳያደርገው አልቀረም ተብሏል።

ሆሞ ናሌዲ (Homo naledi)ቅሪተ አካል
ሆሞ ናሌዲ (Homo naledi)ቅሪተ አካልምስል picture-alliance/ National Geographic/ Mark Thiessen

በሂደት ከጠፉት የዛሬ ዘመን ሰው ዘመዶች ጋር ይደመራል የተባለለት ቅሪተ አካል ከሦስት ወራት በፊት ከወደ ደቡብ አፍሪቃ የመገኘቱ ሌላ ዜና ብዙዎችን አስገርሟል። ከዛሬው ዘመን ዘመናዊ ሰው ጋር ቅርበት አለው የተባለለት ይኽ ቅሪተ አካል ሆሞ ናሌዲ (Homo naledi)የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚገኝ አንድ ዋሻ እንደ ከዋክብት ተበትነው ከተገኙት 1,500አጥንቶች ስብስብ በመነሳት ነው የሆሞ ናሌዲ ገጽታ ናሙና የተበጀው። ሆሞ ናሌዲ በደቡብ አፍሪቃ የሶቶ ጽዋና (Sotho-Tswana-)ቋንቋ ብቅ የሚሉ ከዋክብት የሚል ስያሜ ይይዛል። ሆሞ ናሌዲ ሚጢጢ አዕምሮ እና የራስ ቅል መዋቅር አለው። እንደ ደጋን የተቆለመሙ የእጅ እና የእግር ጣቶቹ መዋቅሮች ከጦጣ ጋር ያመሳስለዋል ተብሏል። ሆሞ ናሌዲ ከዚህ ቀደም በጥናት እና ምርምር ያልተገኘ የጦጣ እና የዘመናዊ ሰው ቅይጥ ነውም ተብሎለታል። የቅሪተ-አካል አጥኚዎች ከወደ ቻይና ደረስንበት ባሉት ምርምር መሠረት ደግሞ ጥንታዊው ብልሁ ሰው ከ80 ሺህ ዓመታት በፊት ወደ ቻይና ያቀናው ከኢትዮጵያ ተነስቶ ነው ብለዋል።

በስዊድን መዲና ስቶክ ሆልም የሚገኘው የካሮሊንስካ ተቋም በሕክምና የዘንድሮዎቹ የኖቤል አሸናፊዎችን ለቻይና፣ ለጃፓን እና አየርላንድ ሳይንቲስቶች በጋራ ሰጥቷል። ተሸላሚዎቹ በጥገኛ ትሎች የሚከሰት ምርቀዛን በአዲስ ዘዴ ማከም እንደሚቻል ያስተዋወቁ እንዲሁም የወባ በሽታን ለመከላከል መድሐኒት ያገኙ ሣይንቲስቶች ናቸው። የአየርላንድ ተወላጁ ዊልያም ሲካምፕቤል፣ ጃፓናዊው ሳቶሺ ኦሙራ እና ቻይናዊቷ ዩዩ ቱ ናቸው ሳይንቲስቶቹ። ቻይናዊቷ የወባ በሽታን ለመታገል መድሐኒት በማግኘታቸው፤ ሁለቱ ሳይንቲስቶች ምርቀዛን ለመከላከል ስኬታማ በመሆናቸው ነው የተሸለሙት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ