1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መዝጋቷ

Merga Yonas Bula
ማክሰኞ፣ ጥር 1 2010

የሱዳን መንግስት በምስራቅ ከኤርትራ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ከባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ዘግቷል። የሀገሪቱ መንግሥት ድንበሩን የዘጋው በአካባቢው ይካሄዳል የሚለውን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር እና የአማፅያን እንቅስቃሴን ለማስቆም ታስቦ መሆኑን እንደ ምክንያት ጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/2qaXM
Karte Sudan Englisch

Border Tension b/n Sudan, Eritrea - MP3-Stereo

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በከሰላና ሰሜን ኮርዶፋን  ግዛቶች  ዉስጥ ባለፈው ታኅሣሥ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የስድስት ወር አስቸኳይ ግዜ ካወጁ ከአንድ ሳምንት በኋላ መንግስት ከኤርትራ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ዘግቷል። የሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር አህመድ ሞሃመድ ኦስማን ለዜና ምንጮች እንዳሉት፣ ርምጃዉ የተወሰደዉ ፕሬዚደንት አልበሽርን ከስልጣን ለማስወገድ በማሰብ በኤርትራ ድንበር አካባቢ ተሰማርተዋል ያሏቸውን የግብፅ የጦር ሃይላት እና የዳርፉር ታጣቂዎችዎች እንቅስቃሴን ለመግታት ነዉ።

ከዚህ በተጨማሪም ሕገ-ወጥ የሰዉ ዝዉውር፣ የመሳሪያ ንግድንና ሌሎች የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር እንደሆነም ተናግረዋል። ይህ ርምጃ ቢወሰድም ግን  በሱዳንና በኤርትራ መካከል ያለዉ የሁለትየሽ ግኑኝነት አለመቋረጡን ሚንስትሩ አህመድ ሞሃመድ ኦስማን ገልፀዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል አሁን ያለውን ግንኙነት ለመተንተን አስቸጋሪ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት በለንደን ዩኒቨርስቲ Institute of Commonwealth Studies ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ማርቲን ፕላዉት ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። በሱዳን መንግስት የተሰጠዉ ምክንያት ግን አሳማኝ አለመሆኑን አክለውበታል። 

«የኤርትራና የሱዳን መንግስት ሁልጊዜም ጥሩ ግንኙነት አላቸዉ። ምክንያቱም ድንበራቸዉ ላይ የሚደረገዉ እንቅስቃሴ ሁለቱንም ስለሚጠቅም። ሁለቱም ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝዉውር እና በሁለቱም አገሮች በኩል በሚካሄዱ ሕገ-ወጥ ሸቀጦች ይጠቀማሉ። የተባበሩት መንግስታት ማስረጃ እንደሚያመለክተዉ አንዱ አገር የሌላውን ድንበር በመሻገር ሰዎችን ሲያስር እንደነበረ ነዉ። ስለዚህ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ አሁን ምን ተቀየረ? የሚል ነዉ። የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ነዉ የሚባለዉን ምክንያት እኔ አልቀበለውም። ኮንትሮባንድ ከሆነ ለረጅም ጊዜ እዚያዉ ነበረ። ስለዚህ ለምን ለሚለዉ ጥያቄ እስካሁን ግልፅ የሆነ መልስ አልተሰጠም» ይላሉ ማርቲን ፕላዉት።

Sudan Omar Hassan Ahmad al-Bashir
ምስል picture-alliance/AA/E. Hamid

ለሱዳን መንግሥት ርምጃ በካርቱም የዳቦ ዋጋ በጣም መጨመሩ አለመረጋጋት መፍጠሩ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባዉ ግድብ በሱዳንና በግብፅ መካከል ግንኙነቱን በማሻከሩ እና በዚህም ዉስጥ ኤርትራ አላት የሚሉት ሚና ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ማርቲን ፕላውት ይናገራሉ።

«በተለምዶ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ችግር ሲፈጠር ሱዳን ኤርትራ ዉስጥ የሆነ ነገር ማድረግ ትፈልጋለች። ይህ ወደ1950ዎቹ መለስ ብለን እንድንመለከት ያደርገናል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በነበረችበት ጊዜ ሌሎቹ አገሮች የኤርትራን ታጣቂ ቡድን ሲረዱ ነበረ። አሁን የኤርትራ ፕሬዚዳንት ከግብፅ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ እስካሁን አናዉቅም። ግን ማለት የምንችለዉ በአሁኑ ጊዜ በአንድ በኩል በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኤርትራና በግብፅ መካከል ያለው ግኑኝነት ጥብቅ ማለቱን ነው። ለዚህም ምክንያት ሊሆን የምችለዉ የሱዳን መንግስት የዓባይን ዉሃን በመጠቀም ረገድ ከግብፅ ጫና እየተደረገበት ይገኛል። በሁለቱም መካከል የድንበር ግጭትም አለ። በኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋቱ እንደቀጠለ ነዉ። ስለዚህ ጊዜዉ በጣም ከባድ ነዉ። ምንም ነገር ለፈጠር ይችላል» ይላሉ ማርቲን ፕላዉት። 

የግብፅ መንግስት በኢትዮጵያ «ህዳሴ» ግድብ ላይ እየተደረገ ካለው የሶስትዬሽ ዉይይት ሱዳን እንድትወጣ ባለፈዉ ሳምንት ጠይቋል ቢባልም ግብፅ  አስተባብላለች።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ