1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን ላይ ማዕቀብ ለመጣል የአሜሪካ አማራጭ

ማክሰኞ፣ የካቲት 8 1997

በትናንትናዉ ዕለት ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግስታት በርከት ያለ የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ደቡብ ሱዳን ስለመላክ የወሰነበትን ረቂቅ ሰነድ አከፋፍላለች። ሆኖም እስከዛሬ ዕልባት ያላገኘዉን የዳርፉር የጦር ወንጀለኞች በየትኛዉ ችሎት ይዳኙ የሚለዉን ጥያቄ ሆን ብላ እንደዘለለችዉ ታዛቢዎች እየተናገሩ ነዉ።

https://p.dw.com/p/E0kO

ዩናይትድ ስቴትስ ሰራሹ የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ በምዕራብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በጣሰዉ ወገን ላይ ከቦታ ወደ ቦታ መጓጓዝንና ያለዉን ሃብት ማንቀሳቀስን ያግዳል።
በዚህ መነሻነትም በፀጥታዉ ምክር ቤት ስር የተቋቋመዉ ኮሚቴ እገዳዉ እነማንን እንደሚመለከት ለይቶ የማዉጣቱን ተግባር ያከናዉናል።
የዩናይትድ ስቴትስ አቋም በሱዳን ሰላም እንዲኖር ከተፈለገ ዳርፉር ዉስጥ ሰላም መስፈን ይኖርበታል የሚል መሆኑንም ባለስልጣናቷ እየገለፁ ነዉ።
ባለስምንት ገፁ የዉሳኔ ረቂቅ እንደሚያትተዉ አለም አቀፍ ተቀባይነት ባለዉ መንገድ ኢሰብአዊ ተግባር የፈፀሙት ወገኖች ሁሉ መጠየቅ አለባቸዉ ሆኖም የትና እንዴት ይዳኙ የሚለዉን አይገልፅም።
ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ የጦር ወንጀለኞቹ በአሩሻ ታንዛንያ ይዳኙ በማለት ያቀረበችዉ ሃሳብ ከምክር ቤቱ በቂ ድጋፍ አላገኘም።
እንደዉም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በታንዛኒያ ለሚካሄደዉ የፍርድ ሂደት አብዛኛዉን ወጪ ዋሽንግተን ለመሸፈን ፈቃደኛ መሆንዋን ገልፀዉ ነበር።
ሆኖም ከ15 የምክር ቤቱ አባላት መካከል ዘጠኙ እስከዛሬ የጦር ወንጀለኞች፤ በሰዉ ዘር ማጥፋት የተከሰሱ ግለሰቦችና የሰብአዊ መብት መድፈር ተግባራት በአለም አቀፍ የወንጀል ችሎት ይዳኙ እንደነበረዉ የዳርፉር ጉዳይም የተለየ ስላልሆነ በሄግ ችሎት ይታይ ነዉ ያሉት።
የቡሽ አስተዳደር ግን ሁኔታዉ እግረመንገዱን በተለያዩ አገራቱ ያሰማራዉን ጦርና ባለስልጣናቱን ለመወንጀል ሊዉል ይችላል በሚል ስጋት ይህን ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃዉሟል።
በሌላ ወገን ያለዉ ስጋት ደግሞ በዳርፉር ያለዉ ግጭት ከቀጠለ እገዳዉ የነዳጅ ዘይትንም ይጨምራል የሚለዉ ሲሆን እንደ ዲፕሎማቶች አገላለፅ ተግባራዊነቱ አጠያያቂ ነዉ።
ረቂቅ ዉሳኔዉ በተጨማሪ ዋና ፀኃፊዉ ኮፊ አናን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ጦር በዳርፉር የሚገኘዉን የአፍሪካ ህብረት ጦር ቁጥሩን በመጨመር የሚረዳበትን መንገድ ያላቸዉን ዘገባ በማቅረብ እንዲያሳዩ ይጠይቃል።
በዳርፉር የሚገኘዉ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አከባሪ ጦር 1,000 ብቻ ሲሆን ባለፈዉ ጥር ወር የሰላም ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ሲቪሉን ህዝብ ከጥቃት ለመከላከል 10,000 የተጠናከረ ኃይል እንዲታዘዝ ተጠይቆ ነበር።
ዲፕሎማቶች ግን ምንም እንኳን የተባበሩት መንግስታት በሱዳን ለማከናወን ያሰበዉን አዲስ ተልዕኮ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ዉስጥ የዋና ፀኃፊዉን ጥናት ተከትሎ ተግባራዊ ቢያደርግም ሰማያዊ መለዮ ለባሹን የመንግስታቱን ጦር በዚያ እናያለን ብለዉ አይገምቱም።
ለመጀመሪያ ጊዜም በዉሳኔዉ መሰረት በሰላም አስከባሪዉ ኃይል ዉስጥ የተለየ ክፍል በማቋቋም ጦሩ በኮንጎ እንደተፈፀመዉ ያለ የወሲብ ጥቃትም ሆነ ብዝበዛ እንዳይፈፅም የስነምግባር ተቆጣጣሪ አካል አቋቂሟል።
ከዚህም ሌላ የሱዳን መንግስት ማንኛዉንም የጥቃት እርምጃ እንዳይወስድ በማስጠንቀቅ ባለፈዉ ሰሞን በተፈፀመዉ ጥቃት ዉስጥ እጃቸዉ ያለበትን ሰዎች በተጠያቂነት እንደሚይዝ ይገልፃል።
በዳርፉር የሚገኙት ወገኖችም ማዕቀቡ ኢሰብአዊ ተግባራት የሚፈፅሙትን የታጠቁ የአረብ ሚሊሻዎች ብቻ ሳይሆን የሱዳን መንግስትም መሳሪያ እንዳይጠቀም እገዳ ይደረግበት ባይ ናቸዉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቿ ያቀረቡት ሃሳብ በመንግስታቱ ድርጅት ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ባላቸዉ ቻይናና ሩሲያ አልጀሪያን ጨምሮ ተቃዉሞ እንደሚገጥመዉ እየተጠበቀ ነዉ።
እነዚህ አገራት ከዚህ በፊት የሱዳን መንግስት እንዳስታጠቃቸዉ የሚነገረዉንና በህዝቡ ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙ ሚሊሻዎች ሁኔታ እስኪያስተካክል ድረስ ሊጣል የነበረዉን እገዳ ባደባባይ የተቃወሙ ነበሩ።
በቀረበዉ ዉሳኔ ላይ የሚደገረዉ ድርድር ሳምንቱን ሙሉ የሚዘልቅ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት መጨረሻ በሚደረገዉ የድምፅ ብልጫ ተስፋቸዉን ጥለዉ በመጠበቅ ላይ ናቸዉ።