1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳንና ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱት ተፈናቃይና ስደተኞች ዜጎቿ፧

ማክሰኞ፣ ሰኔ 12 1999

በዳርፉር ሳቢያ፧ ብዙ የሚነገርባትና የሚነገርላት ሱዳን፧ በሌላ በኩል ዜጎቿ ከስደት የሚመለሱበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ መሆኗ ይነገራል። እ ጎ አ በ 1983 ዓ ም ባገረሸው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው ከነበሩት መካከል በአንድ ዓመት ገደማ ውስጥ፧

https://p.dw.com/p/E0at
ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሱዳናውያን
ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሱዳናውያንምስል AP

አሥራ ሰባት ሺው ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፧ በምዕራብ ኢትዮጵያ በ 4 መጠለያ ጣቢያዎች ሠፍረው የሚገኙት 46,000 ያህል ስደተኞችም የሚመለሱበትን ጊዜ በመጠባባቅ ላይ ናቸው። በተለያዩ አገሮች ተበትነው የነበሩት ሱዳናውያን ብቻ ሳይሆኑ በአገር ውስጥ ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ከልታማ ኑሮ ሲገፉ የቆዩት ሱዳናውያንም ወደየትውልድ ሠፈራቸው በመመለስ ላይ ናቸው። ከኑባ ታራራማ አውራጃ ተፈናቅለው የነበሩትን ሱዳናውያን ይዞታ የተከታተለችው የዶቸ ቨለ ባልደረባ Jutta Schwengsbier የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅራለች፧ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ሰብሰብ አድርጎ አቅርቦታል።
ከ Samsam ቤተሰብ መካከል Samsam el Faki Makeen የተባለችውን የአሥራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት፧ በምሳሌነት እንጥቀስ። የተወለደችው ስዑዲ ዐረቢያ ነው። በካርቱም ትምህርቷን በመከታተል ኢንጅኔር መሆን ትፈልጋለች። አባቷ፧ ስዑዲ ዐረቢያ ውስጥ፧ በአንድ ሆቴል በምግብ አብሳይነት ተሠማርተው ማለፊያ ገቢ ነበራቸው። አሁን ለአሥራ አራት ልጆቻቸው የትምህርት ወጪ ለመክፈል አያዳግታቸውም።
የኑባው ባላባት፧ ከ 25 ዓመት በፊት በጦርነት ሳቢያ ኮረብታማውን መንደራቸውን ለቀው መሰደዳቸውን ነው ለልጆቻቸው ታሪክ የሚነግሩት። ሳምሳም፧ ኑባን አይታው አታውቅም። ባህሉንም በትረካ ከሚነገረው ብቻ ነው የምታውቀው። የወላጆቿን ቋንቋ አታውቅም። ዐረብኛ ብቻ ነው የምትናገረው። እናቷ ወይዘሮ አይሻ አባስ ናየል ተገቢ አይደለም ይላሉ።
«እዚህ ካርቱም ውስጥ በዛ ያሉ የተለያዩ ብሔረሰቦች ናቸው የሚገኙት። ልጆቻችን ታዲያ በተሳሳተ አያያዝና ትምህርት ነው ያደጉት። ባህላቸውን አያውቁትም። ወደትውልድ ሠፈራችን መሄድ አለብን የምልበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነው።«
በሱዳን፧ ከደቡብ፧ ከማዕከላዊው አውራጃ ከኑባ ተራሮች ከምሥራቅና ምዕራብ ሱዳን (ዳርፉር) የተፈናቀሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ናቸው። ወደ ውጭ ከተሰደዱት፧ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉት ሥፍር-ቁጥር የላቸውም። ሳምሳምና ቤተሰቦቿ የሚኖሩት፧ ዑም ባድር በተሰኘው የካርቱም መዳረሻ፧ በጭቃ በተለሰነ ቤት ነው። በድንኳንና እንደነገሩ ውሽልሽል ብሎ በተሠራ ዳስ የሚኖሩት እጅግ በዛ ያሉ ናቸው።
ዓለም-አቀፉ የፍልሰት ጉዳይ መሥሪያ ቤት፧ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር፧ ተፈናቃዮቹ ወደ ሠፈራቸው የሚመለሱበትን ወጪ በመክፈል አስተዋጽዖ ያደርጋል። ስለሆነም ወደ ትውልድ ሠፈራቸው መመለስ የሚፈልጉት እየተመዘገቡ፧ ወደ ደቡብ ሱዳንና ወደ ኑባ ተራራማ አውራጃ ይጓዛሉ። ብዙዎቹ፧ ፍራሽ፧ ብስክሌት፧ ወንበሮችና የመሳሰሉትን ብቻ ነው እየያዙ የሚመለሱት። ተፈናቃይና ስደተኛ ሆኖ ብዙ ንብረት ማፍራት ከባድ ነው። ከተመላሾቹ አንዷ፧ ወይዘሮ ቻዲያ ናቸው።
«መንግሥት ነው ወዲህ ያመጣን። ልጆቻችንና በዕድሜ የገፉት አዛውንት እየተራቡ ነው። ከብቶች ይዘረፋሉ፧ የሚበሉትን በማጣት የሞቱት ብዙ ናቸው። በአንድ በኩል የመንግሥት ወታደሮች ይተኩሱብናል። ድንገት ከዱር በፈረስና በግመል አተርትረው እየጋለቡ የሚመጡ ጠብመንጃ አንጋቢ ዐረቦች ጥቃት ይሰነዝሩብናል። ላም፧ በሬ፧ ፍየል፧ ይሠርቃሉ። ሴት ልጆቻችንንም እየነጠቁ ይወስዳሉ። ይህን የሚያደርጉት፧ የምናውቃቸው የሠፈራችን ዐረቦች አይደሉም። «ጸጉረ-ልውጦች« ናቸው።«
ወይዘሮ ቻዲያ መላ ቤተሰባቸውን ይዘው ነው ወደ ትውልድ ሠፈራቸው የተመለሱት። በካርቱም፧ ኑሮ አስቸጋሪ፧ ጸጥታውም አስተማማኝ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጭ ጦር (SPLA) መሪ ጆን ጋራንግ፧ የሰላም ውል ከተፈረመ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ፧ በሄሊኮፕተር አደጋ እንደሞቱ በተቀሰቀሰ ሁከት ሳቢያ ቻዲያ ሁለት ወንዶች ልጆቸውን ማጣታቸውን ይናገራሉ።
የቻዲያ ትውልድ ሠፈር፧ ካዱግሊ ይባላል። በቆሎ፧ ሰሊጥ ለውዝ ዳጉሣ ያበቅላል።
አይሻና ቤተሰባቸው፧ በማዕከላዊው ሱዳን፧ በኑባ ተረሮች፧ ሃጃር ሱልጣን ወደተሰኘው መንደር ነው የተመለሱት። ብዙዎች ገና አልመጡም፧ አንዳንዶች ናቸው ጎጆ ቀልብሰው የሚታዩት። መሠረተ ልማቱ አልተስተካከለም። መንገድ በሚገባ አልተሠራም። ትምህርት ቤት፧ ሀኪም ቤት የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ጣቢያ የለም። ኑቢያውያን ያላቸው እድል፧ ወይዘሮ አይሻ እንደሚሉት፧ ባህላቸውን መልሶ መንከባከብ ነው። ማታ ማታ ከወገኖቻቸው ጋር በመሰባሰብ ተረት መንገሩ፧ ማደመጡ፧ መዝፈን-መጨፈሩ፧ የጥንቱን የኑባ ተራሮች ህዝብ ባህል መተረኩ እንደሚያስደሳቸውም ነው የገለጡት።