1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰጥቶ የሚነሳዉ የዚምባቡዌ መገናኛ ብዙሃን

ሐሙስ፣ መጋቢት 8 1997

የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመጪዉ መጋቢት 22 ለሚካሄደዉ ምርጫ ቅስቀሳ በመንግስት ቁጥጥር ስር በሚገኙት መገናኛ ብዙሃን እንዲጠቀሙ ተፈቀደ። ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ሁኔታዉ እንዳያማህ ጥራዉ እንዳይበላ ግፋዉ አይነት ነዉ። ለምን ቢባል በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙት የዜና አዉታሮች ከተፅዕኖ የጸዱ አይደሉም።

https://p.dw.com/p/E0kB

ሌላዉ ቀርቶ በስራቸዉ የሚገኙት የሙያዉ ሰዎችም ሳይቀሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያስተናግዱበት መንገድ አግባብ እንዳልሆነ ትችቶች እየተሰነዘሩ ነዉ።
ከላይ ሲያዩት ባለፈዉ ወር የወጣዉ የዚምባቡዌ የመረጃ ስርጭት መመሪያ ስርነቀል ይመስላል። በአገሪቱ ታሪክ ተቃዋሚዎች ድምፃቸዉ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንዲሰማ ሲፈቀድ ይህ የመጀመሪያ መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ።
ሆኖም በዚምባቡዌ የሚገኙት አራት ሬዲዮና ብቸኛዉ ቴሌቭዥን በስልጣን ላይ የሚገኘዉን የዛኑ ፒኤፍን ገድል በመተረክ ከሚወስዱት ረጅም ጊዜ መካከል ለተቃዋሚዎች የሚሰጡት ዕድል ከሁለትና ሶስት የዜና ደቂቃ አልበለጠም።
በዋና ከተማዋ ሃራሬ የሚገኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ የመገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪ ድርጅት እንደሚለዉ የእነዚህ የዜና አዉታሮች ዜናና ሌሎች ዝግጅቶች የፓለቲካ ተቃዋሚዎቹን የመተቸትና የማዳላት አቀራረብ ይታይባቸዋል።
ዋናዉ ስራቸዉ ደግሞ የዛኑ ፒኤፍን ተግባራት ማወደስና አማራጭ የሌለዉ ብቸኛ አገር ወዳድ ፓርቲ አድርገዉ ማቅረብ ነዉ።
ራዲዮና ቴሌቪዥኑን ለማስታወቂያ ለመጠቀምም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠየቁት ገንዘብ እጅግ ከፍተኛና ከአቅማቸዉ በላይ መሆኑን ይናገራሉ።
የዲሞክራሲ ለዉጥ እንቅስቃሴ የተሰኘዉ ፓርቲ ቃል አቀባይ እንደሚሉት ገንዘቡን ወዲያዉ እጅ በጅ ክፈሉ ሲባሉ በአንፃሩ የገዢዉ ፓርቲ ማስታወቂያዎች የአየር ሰዓቱን አጨናንቀዉታል።
ከዚህ በመነሳትም የመገናኛ ብዙሃን ተቺዎች እንደሚሉት የተደረገዉ መሻሻል ቢከፍቱት ለዉጥ የሌለዉ ላዩ ብቻ የተጌጠ ህግ ነዉ።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለምርጫዉና ስለያዙት አማራጭ ፕሮግራም የማስተዋወቅ እድል በሚሰጣቸዉ ጊዜ ለዘመናት የገዢዉ ፓርቲ አስተዋዋቂዎች ሆነዉ ያገለገሉት ጋዜጠኞች በአግባቡ አያስተናግዱንም የሚለዉም ሌላዉ ቅሬታቸዉ ነዉ።
በዚምባቡዌ የምርጫ እንቅስቃሴ አዘጋገብ የሚከታተለዉ ድርጅት እንደሚለዉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የመዘገብ ግዴታ የለብንም የሚሉት የዚምባቡዌ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸዉ ለገዢዉ ፓርቲ እንደሚያደሉ ይፋ አድርጓል።
ለዚህም ማስረጃ ባለፈዉ ወር የዛኑ ፒኤፍ የምርጫ ቅስቀሳ ተካሂዶ ነበር። በቅጥታ በተላለፈዉ ስርጭት የቴሌቪዥን አቅራቢዎቹ ለአራት ሰዓታት የፓርቲዉን መለያ ለብሰዉ መታየታቸዉን ይጠቅሳል።
በመንግስት ስር የሚገኘዉ ሄራልድ ጋዜጣም ከተጓዳኞቹ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የተለየ አቀራረብ የለዉም ሁሉም አድልዎ ይታይባቸዋል።
በግል የመገናኛ ብዙሃን ዉስጥ የሚገኙት ጋዜጠኞች ከመንግስት ፓሊሶች በሚፈፀምባቸዉ ተፅዕኖና ማዋከብ እንደታሰበዉ የሚንቀሳቀሱ አይነት አይደሉም።
ከሶስት አመት በፊት በአገሪቱ የተደነገገዉ መረጃ የማግኘት ነፃነትና መብትን የማክበር ህግ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች የመገናኛ ብዙሃን መረጃ ኮሚሽን ፈቃድ ከሌላቸዉ በሁለት አመት እስራት ይቀጣሉ ይላል።
እስከዛሬም እለታዊዉን ዴይሊ ኒዉስ ጋዜጣ ጨምሮ አራት ጋዜጦች በዚህ ኮሚሽን ትዕዛዝ ታግደዋል።
ከአገሪቱ ለብሪታኒያዉ ዘ ጋርዲያን ይዘግብ የነበረዉ የመጨረሻዉ የዉጪ ዘጋቢ አንድሪዉ ሜልድሩም ከሶስት አመት በፊት ከዚምባቡዌ ተባሯል።
ፓሊሶች የመረጃ ኮሚሺኑን አሰራር ትሰልላላችሁ በሚል በጥያቄ ያዋከቧቸዉ ለአሶሼትድ ፕረስ፤ ለለንደን ታይምስና ለብሉምበርግ ኒዉስ የሚዘግቡት ሶስት የዚምባቡዌ ጋዜጠኞችም ለነፍሳቸዉ በመፍራት ከአገር ተሰደዋል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ሰሞኑን በመጠኑ የተፈጠረዉ የምርጫ ቅስቀሳ ዕድል የዚምባቡዌ ምርጫ የደቡብ አፍሪካ የልማት ህብረተሰብ በምህፃረ ቃል ሳዲክ ባለፈዉ አመት ያወጣዉን አካሄድ የተከተለ ነዉ በሚል አለም አቀፉን ህብረተሰብ ለማሳመን የተሞከረ ነዉ።
ሳዲክ ካወጣቸዉ የምርጫ አካሄዶች ዋነኛዉ ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል የሆነ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ዕድል መስጠት የሚለዉን መጥቀስ ይቻላል።
የሃራሬ ኗሪ የሆኑት ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በዚህ ዉስን ዕድል ተጠቅመዉ በመገናኛ ብዙሃኑ ለአመታት የጠፋ ስማቸዉን ማደስ መቻላቸዉን ይጠራጠራሉ።
በተለያዩ ማስታወቂያዎች የህዝቡና የዚምባቡዌ ጠላት ተደርገዉ የቀረቡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጥቂት ቀናት ቅስቀሳ የህዝቡን እምነት አያገኙም የሚል ነዉ ስጋታቸዉ።