1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰዎች በሙሉ ነፃና እኩል ናቸዉ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 14 2003

አብዛኛዉ ዓለም ደንቡ የዜግነትና የፖለቲካዊ መብቶችን የሚያስከብር መሆኑን የመገንዘቡን ያክል ለምጣኔ ሐብታዊ፥ ለማሕበራዊና ለባሕላዊ መብቶች መከበር የሚሰጠዉን ዋስትና ብዙም አላጤነዉም።

https://p.dw.com/p/RSNO
ዓለም አቀፋዊነትምስል it2net.org


ዓለም አቀፋዊነት (Globalisation):-ለብዙዎችን ኑሮ የማሻሻል ቃል፥ ተስፋም ነበር።ሰብአዊ መብቶች ግን አሁንም አደጋ እንደተጋረጠባቸዉ ናቸዉ።

ብልፅግና፥ የቴክኖሎጂ ዕድገት፥ ኢንተርኔትና የገበያ መጠናካር በሁሉም ክፍለ-ዓለም ለመላዉ የዓለም ሕዝብ የተሻለ ዘመን ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀዉን ዕዉን ማድረግ ይገባቸዉ ነበር።የሰብአዊ መብት ሁለንተናዊ ደንብ እንደሚደነግገዉ «ሁሉም ሰዉ በተፈጥሮዉ እኩል፥ ነፃ፥ ክቡር መብት አለዉ።»

ያም ሆኖ ዓለም አያሌ ቀዉሶች ገጥሟታል።የገንዘብ ገበያ ኪሳራ፥ የአየር ንብረት ለዉጥ፥ የዉሐ፥ የእርሻ መሬትና ሌሎች የአዳጊዎቹ ሐገራት መሠረታዊ ሐብቶች እየተመናመኑ ነዉ።ሁኔታዉ በተለይ ለድሆቹ ሐገራት ሕዝብ ከመሻሻል ይልቅ ይበልጥ እየተበላሸ፥ እያሽቆለቆለ ነዉ።የአለም ባንክና የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ድርጅት (OECD)ን የመሳሰሉ ተቋማት በበኩላቸዉ የንግድና የመዋለ ንዋይ ፍሰት የተፈጥሮ ሐብትን እና ማሕበራዊ ደሕንነትን በሚያስጠብቁበት ሁኔታ እንዲከናወኑ ምክሮችና መመሪያዎችን መስጠታቸዉ አልቀረም።

Simbabwe Menschenrechte Flash-Galerie
የመብት ጥያቄምስል AP

ችግሩ ግን አልተቃለለም።በብዙ አካባቢዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በተለይ ደካሞቹ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀዉሱ ክፉኛ እየተጎዱ ነዉ።ይገለላሉ፥ይጨቆናሉ፥ግፍ ይዋልባቸዋልም።ተበዳዮቹ ኑሯቸዉ እንዲሻሻል እገዛ ይፈልጋሉ። ትብብር ያሻቸዋል።ከሁሉም በላይ በየአካባቢያቸዉ ሰብአዊ መብታቸዉ እንዲከበር፥ ወይም መብታቸዉ ተጠብቆ መስራት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠርላቸዉ ሊረዱ ይገባል።

በ1948 (እ.ጎ.አ.) የተደነገገዉ ሁለንተናዊ የሠብአዊ መብት መርሕ የሰጠዉ ዋስትና እና ተስፋ ሁሉንም መብቶች የሚያካትት ነዉ።ይሁንና አብዛኛዉ ዓለም ደንቡ የዜግነትና የፖለቲካዊ መብቶችን የሚያስከብር መሆኑን የመገንዘቡን ያክል ለምጣኔ ሐብታዊ፥ ለማሕበራዊና ለባሕላዊ መብቶች መከበር የሚሰጠዉን ዋስትና ብዙም አላጤነዉም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በ1966 ያፀደቀዉና በ1976 (እ.ጎ.አ) ገቢራዊ የሆነዉ የምጣኔ ሐብት፥ የማሕበራዊና የባሕል መብቶች ድንጋጌ ካካተታቸዉ መርሆች (ደንቦች) መካካል፥ ለፈሰሰ ጉልበትና እዉቀት ተመጣጣች ክፍያ ያለዉና እና አድሎ የማይፈፀምበት ሥራ የማግኘት መብት እና ለሁሉም እኩል የመሰልጠንና የመማር መብትን የሚበይነዉ አንቀፅ ይገኝበታል።ይሕን መብት ለዜጎቻቸዉ ሁሉ እኩል ለማስከበርም 160 ሐገሮች በፊርማቸዉ አፅድቀዉታል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ