1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰሜን ኢራቅና የዩኤስ አሜሪካ ጦር ርምጃ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 7 2006

በሃይማኖት ተጨቁነው እና በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ወደሚገኝ ተራራ ተሰደው የሚገኙ 20 000 የሚደርሱ የያዚዲ እምነት ተከታዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ እንደሆነ ነው የሚሰማው። ይህም አንዳንድ ጠበብት እንደሚሉት አሜሪካ ጣልቃ ከገባች በኋላ የተገኘ ለውጥ ነው።

https://p.dw.com/p/1Cseg
Irak Jesiden Flucht 9.8.2014
ምስል picture-alliance/AP Photo

ሰሜን ኢራቅ ውስጥ አክራሪው እስላማዊ ታጣቂ የሱኒ ቡድን ሲንጃር የተባለችውን ከተማ ሲቆጣጠር፤ ከዚህ አማፂ ኃይል ጥቃት የሸሹ በሺ የሚቆጠሩ ያዚዲዎች አንድ ሳምንት ያህል ያለ ምግብ እና ውሃ ሲንጃር ተራራ ቆይተዋል። ትናንት ግን ራስ ገዙ የኩርድ መንግሥት እንዳስታወቀው 20 ሺ የሚጠጉ ኢራቃዉያን የሲንጃር ተራራን በሰላም ለመልቀቅ ችለዋል።

ስደተኞቹ ወደ የሶርያ ድንበር በመሸሽ በኩርድ ኃይሎች ታጅበው በሰላም ወደ ኢራቅ መግባታቸዉ ተገልጿል። ይሁንና ትናንት ብቻ በርካቶች በውሃ ጥም እና በድካም የተነሳ ሞተዋል። ከነዚህ ውስጥ 50ዎቹ ህፃናት እንደነበሩ ተገልጿል። 500 የሚሆኑ ያዚዲዎች በእስላማዊ ታጣቂዉ ቡድን ሲገደሉ፤ አንዳንዶች ከነነፍሳቸው እንደተቀበሩ እና በርካታ ሴቶች ወደማይታወቅ ቦታ እንደተወሰዱ ይነገራል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማብራሪያ እስካሁን 600 000 የሚሆኑ ሰዎች ከሶርያ እና ከኢራቅ ወደ ራስ ገዙ የኩርድ አካባቢ በመሰደድ ከለላ አግኝተዋል። ኢራቅ ውስጥ ከታጣቂ ቡድኑ የሚሸሹት ያዚዲዎች ብቻ አይደሉም። በርካታ የክርስትና እምነት ተከታዮችም በአክራሪ ኃይሉ ክፉኛ ተጨቁነው ይገኛሉ። « ይህ ሁሉ የተከሰተው አሜሪካ እኢአ በ2003 ዓም ኢራቅ ውስጥ ጣልቃ በመግባቷ ነው ብለዋል የመካከለኛው ምስራቅ ምሁር ሚካኤል ሉደርስ ለዶይቸ ቬለ ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ። እንደ ሉደርስ አገላለፅ «የኢራቅ መሪ ሳዳም ሁሴን ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በርካታ ሱኒዎች ከፖለቲካ እና ሌሎች ስራዎች ተወግደዋል። ይህም የተበሳጩት ሱኒዎች የአማፂ ቡድን እንዲያደራጁ የጀርባ አጥንት ሆኗቸዋል ይላሉ ሉደርስ።

Irak Jesiden Flucht 9.8.2014
ምስል REUTERS

ምንም እንኳን የዮናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የምርጫ ዘመቻ መፈክር ጦራቸውን ከኢራቅ ማስወጣት የነበረ ቢሆንም፤ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ካለፈው አርብ ጀምረው ጦራቸው ዳግም በኢራቅ ጣልቃ በመግባት የኃይል ርምጃ እንዲወስድ ፈቅደዋል። « አማፂያኑን እስከተፋለሙ ድረስ ለኢራቅ መንግሥት እና ለኩርድ ኃይላት የጦር ድጋፍ እና ምክር መስጠታችንን እንቀጥላለን። በዚህ ሁኔታም አማፂያኑ አስተማማኝ የሆነ መጠጊያ እንዳይኖራቸው ማድረግ ይቻላል።»

USA - PK Präsident Obama vor dem weißen Haus
ምስል Getty Images

የዮናይትድ ስቴትስ አብራሪ የለሽ አይሮፕላኖች እና የጦር አይሮፕላኖችን በከፊል ለውጊያ የተሰማሩ ሲሆን በሌላ በኩል ሌሎች የጦር አይሮፕላኖች 40 000 ሊትር ውኃ እና 52 000 የታሸጉ ምግቦች የሰብዓዊ ርዳታ ለሚሹት ስደተኞች ከአይሮፕላን ወርውረዋል። የአሜሪካ ጣልቃ መግባት እስከመቼ ይዘልቅ ይሆን? «ችግሩን በሳምንታት የምንፈታው አይሆንም፤ እንደሚመስለኝ የተወሰነ ጊዜ ይፈጃል።»

ይላሉ ኦባማ። በርግጥ ኦባማ ፈታኝ ጊዜ ነው የገጠማቸው። ቢሆንም የአሜሪካን የሰሙኑን ጣልቃ ገብነት የሚያወድሱት ይበልጣሉ፤ በተለይ ተጨቋኝ ኢራቃውያን። « የቦንብ ድብደባዎቹ ለውጥ አሳይተዋል» ይላሉ ከያዚዳን ማዕከላዊ ምክር ቤት ቴሊም ቶላን። በዶይቸ ቬለ ቴሌቪዥን የቀረቡ የኩርድ ወታደሮች ደግሞ « ምንም እንኳን ሁሉም ነገር ይፋ ባይወጣም የአይ ኤስ ቡድን በርካታ ሰዎች ቆስለው እና ሞተውበታል። እንዲሁም ተሽከርካሪዎቻቸው ወድመዋል።» ብለዋል።

በአንድ በኩል የሀይማኖት ተወካዮች እና ጠበብት ለዮናይትድ ስቴትስ የሞራል ድጋፍ ሲሰጡ በሌላ በኩል ሀብታም ሳውዲአረቢያን እና ሱኒዎች የአይ ኤስ ቡድንን በገንዘብ ይደግፋሉ።

ኢራቅ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ሰላም ማስፈን ህልም ነው የሚመስለው። ትናንት የኢራቅ ፓርላማ እንዴት አዲስ መንግሥት ሊመሰርት እንደሚችል ዳግም ሲመክር ቢውልም ውጤቱ ግን ተስፋ ሰጪ አልነበረም።

ሽቴፈኒ ሆፐር/ልደት አበበ

ተክሌ የኃላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ