1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰላም የራቃቸው ናይጀሪያና ጊኒ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14 2013

ምዕራብ አፍሪቃውያኑ ናይጀሪያ እና ጊኒ ሰላም ርቋጠዋል። ናይጀሪያ ውስጥ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ተቃውሞና ሰልፍ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ቢያንስ ለ56 ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል። በጊኒም ባለፈው እሁድ የተካሄደው ምርጫ ውጤት ብጥብጥ ቀስቅሷል።

https://p.dw.com/p/3kMh1
Nigeria Lagos | Proteste gegen Polizeigewalt
ምስል Benson Ibeabuchi/AFP

«ትኩረት በአፍሪቃ»

ተቃውሞና ጥቃት በናይጀሪያ

ናይጀሪያ ውስጥ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ተቃውሞና ሰልፍ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ቢያንስ ለ56 ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል። ተቃውሞውን  የቀሰቀሰው  በማኅበራዊ  መገናኛ  ዘዴዎች የተሰራጨው የፀረ ዝርፊያ ልዩ ቡድን የተሰኘው የናይጀሪያ ፖሊስ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ SARS አባል ደቡባዊ ዴልታ ግዛት ውስጥ አንድ ዜጋን ሲገድል የሚያሳየው ቪዲዮ ነው። ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት የፀረ ዝርፊያ ልዩ ቡድን የተሰኘው የናይጀሪያ ፖሊስ ዘርፍ የተሰጠውን ሥልጣን ያለአግባብ በመጠቀም እና ያስቆማል የተባለው እንደዝርፊያ እና እገታ በመፈጸም ከኅብረተሰቡ ክስ ይቀርብበታል። የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይህን የፖሊስ ዘርፍ ለማሻሻል ከጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም ቃል ቢገቡም ለተቃውሞ የወጣው ሕዝብ ምን የተደረገ ለውጥ የለም ነው የሚለው።

በመሠረቱ መንግሥት የፀረ ዝርፊያ ልዩ ቡድን ይባል የነበረው የፖሊስ ዘርፍ የጦር መሣሪያ እና ስልት ልዩ ቡድን በምህጻሩ SWAT በሚል ተክቷል። የፖሊስ አዛዥ ጀነራል መሀመድ አዳሙም ይህ የፖሊስ ኃይል የተሰጠውን ኃላፊነት ለሌላ እንዳይጠቀምበት እንዲሰለጥን ይደረጋል ብለው ነበር። የዚህ የፖሊስ ዘርፍ ተግባር የሚቃወሙት ዜጎች ግን የለም SWAT ያው የቀድሞውን የፀረ ዝርፊያ ልዩ ቡድን አስከፊ ድርጊት ከመቀጠል የዘለለ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው በመግለጽ በተቃውሟቸው ገፍተዋል።

በዚህ ሰሞን የተቀሰቀሰው የወጣቶች ንቅናቄም በፖሊስ የጭካኔ ተግባር ላይ ዘላቂ ለውጥ ካልተደረገ ከአደባባይ  ተቃውሟችን አንመለስም በሚል ነው። ተቃውሞ በተለያዩ የናይጀሪያ ከተሞች የተቀጣጠለ ሲሆን ማዕከሉን ሌጎስ ላይ አድርጓል። የተቃውሞው ደጋፊዎች ቁጣቸውን ለመግለፅ በማኅበራዊ መገናኛው SARS ይቁም የሚል ልዩ ጥሪ ወይም ሃሽታግ ተጠቅመው ድምጻቸውን ያሰማሉ።

ተቃውሞ በናይጀሪያ
ምስል Reuters TV

እንዲያም ሆኖ ናይጀሪያ በጎሳ እና በሃይማኖት እጅግ የተከፋፈለች ሀገር በመሆኗ ፀረ ዝርፊያ የተባለውን ልዩ የፖሊስ ቡድን በመቃወም የሚካሄደው እንቅስቃሴም ሆነ ተቃውሞ በሁሉም ዘንድ ድጋፍ ያለው አይመስልም። ቦኮ ሃራም በስፋት በሚንቀሳቀስበት በሰሜናዊ ናይጀሪያ ኑሯቸው በስጋት የተከበበው ዜጎች ሃሳብ ከተቃዋሚዎቹ ይለያል። በተጠቀሰው ስፍራ  የሚገኙት ወገኖች SARS እንዲፈርስ ከተደረገ  የአካባቢያቸው የፀጥታ ይዞታ የባሰ አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ስጋት አላቸው። በዚህም ምክንያት ይህን የፖሊስ ኃይል የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የተዘጋጁ ነበሩ ሆኖም ባለሥልጣናት በማይዱጉሪ ማንኛውም ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድ አግደዋል።  

ተቃውሞ በተቀጣጠለባት ሌጎስ ከተማም  በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ሊካሄድ ከታቀደው የተቃውሞ ሰልፍ አስቀድሞ የሰዓት እላፊ ተነደገገ። የሌጎስ ግዛት፤ ሀገረ ገዢም ተቃዋሚዎቹን ጨምሮ ነዋሪዎች ደንቡን እንዲያከብሩና ከየቤታቸው እንዳይወጡ  አስጠነቀቁ።  በድንጋጌው መሠረትም መንገድ ላይ የተገኘ ማናቸውም ሰው ሕገ ወጥ ነው በሚል የፀጥታ ኃይሎች በሺህዎች በሚገመቱ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ ከፈቱ። በዚህም ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውን የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽል አስታውቋል።

በዚህ ድርጊት የተደናገጡትና የተቆጡት ሌጎስ ከተማ ላይ የፖሊስ ጣቢያን እና ሌሎች መንግሥታዊ ሕንጻዎችን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉት ላይ ጥቃት አደረሱ በእሳትም አቃጠሉ። በማኅበራዊ መገናኛውም በናይጀሪያ ጥቁሩ ማክሰኞ እንዲሁም የሌኪ ጭፍጨፋ የሚሉ ልዩ ጥሪዎችን ተጠቅመው ቁጣቸውን ገለጹ። በሌጎስም በሌሎች መሰል ተቃውሞ በተቀሰቀሰባቸው ከተሞች የተደነገገው የሰዓት እላፊ እንዳለ ሲሆን፤ ለቀጣይ ጥቂት ቀናትም እንደሚቆይ ይጠበቃል። ሆኖም ተቃውሞው አልሰከነም፤ አሁንም ሕይወታቸውን ላጡ ፍትህ በመጠየቅ ቀጥሏል።

ለሳምንታት ሕዝቡ ተቃውሞውን እያሰማ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ሲላተም እና ሕይወት ሲጠፋ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ማሀማዱ ቡሃሪ ዝምታን በመምረጣቸው ሲተቹ ነበር። ከብዙ ወቀሳ በኋላ ፕሬዝደንቱ ሐሙስ ማምሻውን አመጹን ለማስከን በሚል ለሕዝብ ንግግር ቢያደርጉም ሰላማዊ ሰልፈኞች በፀጥታ ኃይሎች ስለመገደላቸው አላነሱም።  

«እናም ወጣቶቻችን የጎዳና ላይ ተቃውሟቸውን በማቆም መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ በገንቢ መንገድ እንዲሞግቱ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ድምጻችሁ በግልፅ እና ከፍ ብሎ ተሰምቷል፤ እናም ምላሽ እየሰጠን ነው።»

Nigeria l Proteste in Lagos, Rauch über der Stadt
ምስል Jacob Parakilas/Reuters

ሆኖም ይህ ጥሪያቸው አዎንታዊ ምላሽ ያገኘ አይመስልም። በማግስቱ ዓርብ ዕለት ስለትና ዱላ የያዙ በርካቶች የሌጎስን አውራ ጎዳናዎች ዘግተዋል። ሮይተርስ በእማኝነት እንደዘገበው ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የሚወስደውን  መንገድ የዘጉት ተሽከርካሪዎች ገንዘብ ካልከፈሉ አናሳልፍም በማለት ለመክፈል ያንገራገሩትን ሲያወድሙ ታይተዋል። በከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል ሊቡጁ እና ሌኪ በተባሉት አካባቢዎች የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ፖሊስን በማባረር በርካታ የፖሊስ ጣቢዎችን አቃጥለዋል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተረሽ የፀጥታ ኃይሎች ከኃይል ርምጃ እንዲጠበቁ ተማጽነዋል። ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል ያሏቸው የተቃውሞ ሰልፈኞች ጉዳይ ባስቸኳይ እንዲጣራ እየጠየቁ ነው። በናይጀሪያ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ኦሳይ ኦጂጎሆ የፀጥታ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግን አላከበሩም ሲሉ ይወቅሳሉ።

«በስፍራው ተገኝተን በግልፅ እንዳስተዋልነው የፀጥታ ኃይሎች የሰዎችን ሕይወትና የሕዝቡን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግንም ሆነ የናይጀሪያን ሕገ መንግሥት አያከብሩም።»

ይህም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ውግዘት ነው ያስከተለው። ፕሬዝደንት ቡሃሪ ግን ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጉዳዩን ሳያጣራ አቋም እንዳይወስድ አሳስበዋል።

«ናይጀሪያ ውስጥ በሚካሄደው ምክንያት ስጋታቸውን ለገለፁ በተለይ ለጎረቤቶቻችን እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት፤ እያመሰገንን አቋም ከመውሰድ ወይም ፈጣን ፍርድ ከመስጠታችሁና ይፋዊ መግለጫ ከማውጣታችሁ በፊት ያሉትን እውነታዎች ሁሉ እንድታጣሩ እንጠይቃችኋለን።»

በናይጀሪያ የዜጎች ቁጣ ንሯል፤ በሀገሪቱ የታየው አመጽ እና ጥቃት ናይጀሪያ ወደ ሲቪል አስተዳደር ከተመለሰች ከጎርጎሪዮሳዊው 1999 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተና ለፕሬዝደንት መሃማዱ ቡሃሪም እጅግ ፈታኝ የፖለቲካ ቀውስ መሆኑንም ተጠቁሟል።  

 

የጊኒ ምርጫና ውዝግቡ

አልፋ ኮንዴ
ምስል Sadak Souici/Le Pictorium Agency/ZUMA Press/picture-alliance

 ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ጊኒ ባለፈው ሳምንት እሁድ ምርጫ ካካሄደች በኋላ ውጤቱ ውዝግብ ውስጥ ከቷታል።  በመጀመሪያ የምርጫ ውጤት መሠረት ሥልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት ማሸነፋቸው እየተነገረ ነው። የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የመጨረሻውን ውጤት ዛሬ ቅዳሜ እንደሚያሳውቅ ቢገልፅም ምርጫው ከተካሄደበት ቀን ማግሥት ጀምሮ ውጤቱ ይጭበረበራል የሚለው ስጋት የተቃዋሚውን ጎራ ደጋፊዎች ለተቃውሞ አነሳስቷል። ማክሰኞ ማምሻውን ጀምሮ የወጡ የተወሰኑ የምርጫ ውጤቶች ኮንዴ እየመሩ መሆኑን ቢያሳዩም የድምፅ ቆጠራው ይጭበረበራል ብለው ሲከሱ የነበሩት ዋነኛ ተቀናቃኛቸው  ሴሉ ደላን ዲያሎ  ደጋፊዎቻቸው የጀመሩትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዲገፉበት ጥሪ አድርገዋል።

«ውድ ጓዶች ለድላችን ትታገላላችሁ ብዬ እተማመንባችኋለሁ። በዚህ መሀል እኔ እስር ላይ ነኝ። መልእክቴን የማስተላልፈው ከቤቴ ነው፤ ማለትም ከታገትኩበት ማለት ነው። መውጫዬ ሁሉ በፀጥታ ኃይሉ አባላት ተዘግቷል። ማንም ወደ እኔ ቤት መግባትም ሆነ መውጣት አይችልም። ይህን ያዘዙት አልፋ ኮንዴ ናቸው። ይህ ደግሞ ሕገወጥ ነው። ዓይን ያወጣ ነፃነቴን መጣስ ነው።»

ረቡዕ ዕለት የፀጥታ ኃይሎች ጎዳና ላይ በወጡ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ። በተለያዩ ነገሮች መንገድ የዘጉትን ሰልፈኞች ለመበተንም አስለቃሽ ጋዝ ተኮሱ። ተቃውሞው እሳቸው እንደተመኙት ተቀጣጥሏል። የመንግሥት ኃይሎችም ለተቃውሞ ጎዳና ከወጡት ጋር ፍልሚያ ላይ ናቸው። የፀጥታ  መደፍረስ ያሳሰባቸው የጊኒ የሀገር ውስጥ ግዛት አስተዳደር ሚኒስትር ጀነራል ቤሪማ ኮንዴ ትናንት ሁኔታው እንዲህ ነው የገለፁት። «ላለፉት ጥቂት ቀናት ኮናክሪ ከተማ እና ሌሎች የሀገሪቱ ግዛቶች ዜጎችና እና አጠቃላይ ቤተሰቦችን እርዳታ አልባ ስሜት ውስጥ ያስገባ በጣም አስጊና ከፍተኛ አመጽ እያስተናገዱ ነው።» በዚህም ከሰው ሕይወት ሕልፈት በተጨማሪ የመንግሥትና የግል ንብረት እየወደመ መሆኑንም አመልክተዋል። ቤሪማ ኮንዴ መንግሥታቸው ለሰላም እና ለማኅበራዊ መረጋጋት መርሆዎቹ በታማኝነት ስለሚሠራም እንዲህ ያለው አመጽ እንዲቀጥል እንደማይፈቅድም አፅንኦት ሰጥተዋል።

በጊኒ የተባባሰው አመፅ
ምስል John Wessels/AFP

ጊኒ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛትነት በጎርጎሪዮሳዊው 1958 ዓ,ም ነጻ ስትወጣ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩት አህመድ ሴኩ ቱሬ ናቸው። ሴኩ ቱሬ ወደ ሥልጣን ወጡት ፓርቲያቸው የጊኒ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከአንድ ዓመት በፊት በተካሄደው የግዛቶች ጠቅላላ ምርጫ ከምክር ቤቱ 60 መቀመጫዎች 56ቱን አሸንፎ እንደሆነ ታሪክ መዝግቦታል። ፕሬዝደንት ሴኩ ቱሬ ታዲያ ከተመረጡ ከሁለት ዓመት በኋላ ፓርቲያቸውን ብቸኛው የሀገሪቱ ሕጋዊ ፓርቲ መሆኑን በማወጅ ለቀጣይ 24 ዓመታት መራጮች ለዚህ ፓርቲ ብቻ ድምጽ እንዲሰጡ ማድረጉ ተሳክቶላቸው ሦስት የሥልጣን ዘመን ያለተቀናቃኝ ዘልቀዋል። በጎርጎሪዮሳዊው 1984 ሴኩ ቱሬ ሲሞቱ ላንሳና ኮንቴ እና ዲያራ ትራዎሬ በደም አፋሳሽ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣኑን ያዙ እና ላንሳና ኮንቴ ፕሬዝደንት ሆኑ። በኮንቴ ዘመነ ሥልጣን ነው ጊኒ ወደሲቪል አስተዳደር ተቀይራ የመጀመሪያው መድበለ ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተካሄደው። እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2002 ድረስ በተካሄዱ ምርጫዎችም የፕሬዝደንትነት መንበሩ ከእጃቸው አልወጣም። እሳቸውም እንደቀዳሚያቸው የዛሬ 12 ዓመት በሞት ሲለዩ ሙሳ ዳዲስ ካማራ በእግራቸው ተተኩ። ወደ ሥልጣን በወጡ በዓመቱ በተደረገባቸው የመግደል ሙከራ ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመቱ። ከሀገር ውጭ ከታከሙ በኋላ ዳግሞ የሲቪል አስተዳደር በጊኒ እንዲቀጥል ተስማሙ። በጎርጎሪዮሳዊው 2010 በተካሄደው ምርጫ የዘንድሮዎቹ ግንባር ቀደም ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ዲያሎ እና ኮንቴ ለምርጫ ቀርበው አብላጫ ድምፅ ባለማግኘታቸው ሁለተኛ ዙር ድምፅ ተሰጠ። በዚህም አልፋ ኮንዴ 52,54 በመቶ በማግኘት አሸናፊ ሆኑ። በጎርጎሪዮሳዊው 2013 በተካሄደው ምርጫም ፓርቲያቸው የጊኒ ሕዝቦች ምክር ቤት ከፓርላማው 114 መቀመጫ 53ቱን ያዘ። ዘንድሮ በተካሄደው ምርጫም የሚወጡት  የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ውጤቶች የ82 ዓመቱ ኮንዴ ለሦስተኛ ጊዜ ድል እንደቀናቸው እያሳዩ ነው። ተቀናቃኛቸው ሴሉ ዲያሎ ተጭበርብሯል የሚሉትን ውጤት ባለመቀበል ፀንተዋል። ደጋፊዎቻቸውም በተቃውሞው እየሞቱም ገፍተዋል። የጊኒ የምርጫ ኮሚሽን የመጨረሻውን ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ትረጋጋ ይሆን? ውሎ አድሮ የምናየው ይሆናል። 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ