1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሪያል ማድሪድ የአውሮጳ ሻምፒዮን

ሰኞ፣ ግንቦት 18 2006

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም የውድድር መድረክ አሸናፊ ሆነዋል። ዝርዝር ይኖረናል። የዓለም ዋንጫ ዝግጅትን እንዲሁም የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ጨዋታን በተመለከተ ዳሰሳ እናደርጋለን። የሚኪና ሽቅድምድምና ሌሎች ስፖርት ነክ ዜናዎችንም አካተናል።

https://p.dw.com/p/1C7Gl
ምስል Reuters

ባሐማስ ውስጥ በተካሄደው የ1500 ሜትር የወንዶች የዱላ ቅብብል ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሆነዋል። በካናዳ የማራቶን ሩጫ ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል። የአውሮጳ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ዝውውር ዜና፣ የዓለም ዋንጫ ዝግጅት በብራዚል፣ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ውጤትና ውዝግብ እንዲሁም ሌሎች አጫጭር ስፖርት ነክ ዜናዎችንም አሰናድተናል።

በተጫፈሩት የባሐማስ ደሴቶች ግዛት ሮቢንሰን ስታዲየም ውስጥ ትናንት በተከናወነው የ1500 ሜትር የወንዶች የዱላ ቅብብል ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአውስትራሊያ ተፎካካሪዎችን ቀድመው በ14:41.22 ሦስተኛ ወጥተዋል። በእዚህ ውድድር የኬንያ ቡድን 14:22.22 በመግባት የዓለም ክብረወሰን ሰብሮእንደተጠበቀው በአንደኛነት ወርቅ ሲያጠልቅ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ሯጮች 14:40.80 ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳይ ተሸላሚ ሆነዋል።

Tirunesh Dibaba Paris Stade de France
ምስል DW/H. Tiruneh

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አማን ወቴ፣ መኮንን ገ/መድኅን፣ ሶሬሳ ፊዳ እና ዘነበ አለማየሁ በድንቅ አጨራረስ ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳይ አስገኝተዋል። በውድድሩ ቀደም ሲል ልምድ ያካበቱት አማን ወቴ እና መኮንን ገ/መድኅን የሩጫ ፍጥነታቸው ከአሜሪካኖቹ የተሻለ እንደነበር ተዘግቧል።

ካናዳ ዖታዋ ውስጥ ትናንት እና ከትናንት በስትያ በተከናወነው የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበር ፌዴሬሽን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል። በወንዶች የማራቶን ሩጫ አትሌት የማነ ፀጋዬ በ2:06:54 በመግባት ወርቅ አጥልቋል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት ቱፉም የማራቶን ሩጫውን በ2:24:31 በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ ሆናለች። 12 ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት ተፈትልኮ የወጣው የማነ ፀጋዬ አንደኛ በመውጣቱ 20000ዶላር ተሸላሚ ሲሆን፤ የቦታውን ክብርወሰን በመስበሩ 10000 ዶላር ተጨማሪ አሸንፏል።

በሀገሩ ልጅ ድሪሳ ጪምሳ ባለፈው ዓመት እዛው ካናዳ ውስጥ የተመዘገበውን የ2 :07:05 በማሻሻሉ ደግሞ 10000 ዶላር ጭማሪ ሲኖረው፤ በጥቅሉ የ40000 ዶላር ተሸላሚ ሆኗል። በእዚህ ውድድር እጎአ በ1999 የአትሌቲክስ ማኅበር ፌዴሬሽን የዓለም ሻምፒዮንስ የወርቅ ተሸላሚ የነበረችው የጌጤ ዋሚ ወንድም ሙሉጌታ ዋሚ በ2:08:18 ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳይ ተሸላሚ ሆኗል። ኬንያዊው እስማኤል ቼምታ ከሙሉጌታ በ17 ሠከንዶች ዘግይቶ ሦስተኛ ወጥቷል።

Russland Leichtathletik WM in Moskau Tirunesh Dibaba und Belaynesh Oljira
ምስል Haimanot Tiruneh

እስከ 21ኛው ኪሎ ሜትር ተመጣጣኝ ፉክክር በነበረው የሴቶች የማራቶን ሩጫ ትዕግስት ቱፋ ፍጥነቷን በመጨመር ነው ለድል የበቃችው። ኬንያዊቷ አግኔስ ኪፕሮፕ ትዕግስትን በመከተል ሁለተኛ ለመውጣት ብትሞክርም በስተመጨረሻ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሠረት ቶልዋቅ ቀድማት የሁለተኛነቱን ቦታ ነጥቃታለች። መሠረት በ2:27:26 በማጠናቀቅ የብር ሜዳይ ተሸላሚ ሆናለች። ኬንያዊቷ አግኔስ ከመሠረት በ39 ሠከንድ ዘግይታ ሦስተኛ ወጥታለች።

የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ውጤትን ከመቃኘታችን በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተከናወነውን የሴቶች የእግር ኳስ ጨዋታ አጠር አድርገን እንዳስ። ትናንት አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ በኢትዮጵያ ሉሲ እና በጋና ጥቁር ንግሥት ቡድን መካከል በተደረገው ግጥሚያ ጋና 2 ለዜሮ አሸናፊ ሆናለች።

የጋና የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊ
የጋና የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊምስል FAG

ለአፍሪቃ ዋንጫ የሴቶች እግር ኳስ ጨዋታ የመጨረሻ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ በተካሄደው የትናንቱ ፍልሚያ ከሜዳቸው ውጪ የተጫወቱት የጋና ተጨዋቾች ማጣሪያውን ለማለፍ ሰፊ ዕድል ይኖራቸዋል። ጋናዎች በሜዳቸው በሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ አለመሸነፍ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው። ለጋና ጥቁር ንግሥት የመጀመሪያውን ግብ ሣሚራ ሱሌይማን ስታስቆጥር የማሳረጊያውን ሁለተኛ ግብ ደግሞ ኤልሳቤጥ ኮጆ ከመረብ አሳርፋለች።

የፊታችን አርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ በሚደረጉት ጨዋታዎች አሸናፊ የሆኑ 7 ቡድኖች እንደሚለዩ የጋና እግር ኳስ ማኅበር በድረ-ገጹ ዘግቧል። ሰባቱ አሸናፊዎችም ከጥቅምት 1 ቀን፣ 2007 ዓም እስከ ዓርብ ጥቅምት 14 ቀን፣ 2007 ዓም ድረስ በናሚቢያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ድረ-ገፁ አትቷል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ሪያል ማድሪድ አትሌቲኮ ማድሪድን ከትናንት በስትያ ባለቀ ሠዓት 4 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። ሁለቱ የስፔን ኃላያላን ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ መደበኛው 90 ደቂቃ የተጠናቀቀው የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዲዬጎ ጎዲን ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ መሪነት ነበር። ሆኖም በባከነ ሠዓት በተጨመረው ሦስተኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተላከለትን ኳስ የሪያል ማድሪዱ ሰርጂዮ ራሞስ ከተከላካዮች መሀከል ዘሎ በጭንቅላት በመግጨት በድንቅ ሁናቴ ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑን ታድጓል። ሪያል ማድሪድ የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድል ከሆነ በኋላ ZDF የተሰኘው የጀርመኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረገለት ቃለ-መጠይቅ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ሳሚ ከዲራ ደስታውን እንዲህ ነበር የገለፀው።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው የሪያል ማድሪዱ ሳሚ ኬዲራ
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው የሪያል ማድሪዱ ሳሚ ኬዲራምስል Lars Baron/Getty Images

«እንደእዛ ይሆናል ብሎ ማንም አላሰበም። እጅግ በጣም ነው የተደሰትኩት። ራሞስ ከጉድ ባያወጣን ኖሮ አክትሞልን ነበር። ድንቅ ቡድን ነው ያለን፤ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ምንም ተስፋ ሳንቆርጥ ነው የተጫወትነው። በቃ ደስታዬ ወሰን የለውም። ምንም መናገር እንዳለብኝ እንኳን አላውቅም።»

ሁለተኛዋን ግብ ጋሬት ባሌ በ 109ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል። ከ9 ደቂቃ በኋላ ሦስተኛዋን ግብ ማርሴሎ ለማስቆጠር ችሏል። መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ የተጨመረው 30 ደቂቃ አብቅቶ በባከነው የመጨረሻ ደቂቃ ማለትም 121ኛው ደቂቃ ላይ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ በመጠለፉ የተሰጠውን ዕድል በሚገባ ተጠቅሞ አራተኛውን ግብ በድንቅ ሁናቴ ከመረብ አሳርፏል። በእዚህም ሪያል ማድሪድ 60000 ተመልካቾች በታደሙበት የሊዛቦኑ ኤስታዲዮ ደ ሉስ ስታዲየም ተፎካካሪው አትሌቲኮ ማድሪድን 4 ለ1 አሸንፏል።

የመኪና ሽቅድምድም። በሞናኮው ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲስ አሽከርካሪዎችቹ ኒኮ ሮዘንበርግ እና ሉዊስ ሐሚልተን አንደኛ እና ሁለተኛ ወጥተዋል። አንድ ቡድን ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ አሽከርካሪዎች ባገኙት የትናንትናው ውጤት ሉዊስ ሐሚልተን ቅሬታ እንዳደረበት ገልጿል። ኒኮ አንደኛ ለመውጣት ከመነሻው አንስቶ ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ ፍጥነነቴን እንዳልጨምር የመንገዱን ጠርዝ በመያዝ ሲከላከለኝ ነበር ሲል ሐሚልተን በቡድን አባሉ የተሰማውን ቅሬታ ገልጿል።

የ2014 የዓለም ዋንጫ ተሰላፊ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አባላት
የ2014 የዓለም ዋንጫ ተሰላፊ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አባላትምስል picture-alliance/ZB

ከስድስት ወራት በኋላ ሞሮኮ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም የእግር ኳስ ቡድን ሻምፒዮኖች ውድድር ላይ የሞሮኮው ማግሬብ ቴቶን ቡድን ማለፉ ታወቀ። ማግሬብ ለዓለም ሻምፒዮን ያለፈው ትናንት ተፎካካሪው ራጃ ካዛብላንካን አሸንፎ የሞሮኮ ሊግ ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ በእጁ በማስገባቱ ነው።

የሞሮኮው ማግሬብ ቡድን ከትናንት በስትያ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ከሆነው ሪያል ማድሪድ ጋር ከወራት በኋላ እዛው ሞሮኮ ውስጥ ይገናኛል።

ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን፣ 2006 ዓም የሚጀምረው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታን ለመታደም ወደ 300 000 የሚገመቱ የውጭ ሀገር ሰዎች ብራዚል እንደሚገቡ ተጠቀሰ። የመክፈቻው ጨዋታ በአስተናጋጇ ብራዚል እና ክሮሺያ መካከል ሳዎ ፖሎ ከተማ ውስጥ ነው የሚካሄደው። ጨዋታዎቹ በሚካሄዱባቸው የብራዚል ከተሞች ውስጥ ችግር እንዳይፈጠር በሚል 157 000 ወታደሮች እና ፖሊሶች ለጥበቃ እንደሚሰማሩም ተገልጿል።

በእዚህ የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ወደ ብራዚል የሚያቀናው ከ24 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለአራተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለመጨበጥ ተስፋ በማድረግ እንደሆነ ተጠቅሷል። ያለፉት ሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ለግማሽ ፍፃሜ ደርሶ የነሐስ ዋንጫ ያሸነፈው የጀርመን ቡድን ውስጥ ተሰላፊ የነበረው የቡድኑ አምበል ፊሊፕ ላም ቡድናቸው ሦስተኛ መውጣቱ እንዳታከተው ተናግሯል። ጀርመን በጃፓኑ የዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ደርሳ በብራዚል የተሸነፈችው ከ12 ዓመታት በፊት ነበር።

የ35 ዓመቱ ፍራንክ ላምፓርድ
የ35 ዓመቱ ፍራንክ ላምፓርድምስል picture-alliance/dpa

የእግር ኳስ ተጨዋቾች የዝውውር ዜናዎችን እናሰማችኋለን። የQPRአሠልጣኝ ሐሪ ሬድክናፕ የማንቸስተሩ ተከላካይ ሪዮ ፈርዲናንድ እና የቸልሲው አማካይ ፍራንክ ላምፓርድን ወደ ቡድናቸው ለማምጣት እርግጠኛ መሆናቸውን ገለጡ ሲል The Sun የተባለው ጋዜጣ ዛሬ ዘግቧል። ፈርዲናንድም ሆነ ላምፓርድ ዕድሜያቸው 35 ዓመት ነው።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የአርሰናሉ አጥቂ ሉቃስ ፖዶልስኪን በደህና ዋጋ የሚወስድ ቡድን ከተገኘ አርሰናል ዝውውር ለመፈፀም አይኑን እንደማያሽ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አስታውቋል። ለዓለም ዋንጫዝግጅት እያደረገ የሚገኘው ሉቃስ ፖዶልስኪ በለንደን ቆይታውም ሆነ በቡድኑ ደስተኛ እንደሆነ ለንደን ውስጥም ተደላድሎ እንደተቀመጠ ገልጿል።

የሊቨርፑል እና የአርሰናል ዓይን ያረፈበት የስዋንሲ አጥቂ ዊልፍሬድ ቦኒን ለመውሰድ ቡድኖቹ 25 ሚሊዮን ፓውንድ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ስዋንሲ ዛሬ አስታውቋል። ሊቨርፑል ከዊልፍሬድ በተጨማሪ የሳውዝ ሐምፕተኑ አማካይ አዳም ላላናን ለመውሰድ ያቀረበው 25 ሚሊዮን ፓውንድ በቂ አይደለም መጨመር አለበት ሲል ሳውዝ ሐምተን አሳውቋል። ሊቨርፑሎች የሳውዝ ሐምተኑ የቀኝ ክንፍ ተመላላሽ ናትናኤል ክሌንን ጨምሮ ሁለቱን ተጫዋቾች ለመውሰድ በጥቅሉ የ40 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ አቅርበል።

የሊቨርፑሉ አሠልጣን በርንዳን ሮጀርስ በሊቨርፑል ለመቆየት እና ለቡድኑ የተቻላቸውን ለማድረግ አዲስ የረዥም ጊዜ ውል ዛሬ መፈረማቸው ተዘግቧል። ሊቨርፑል ከ24 ዓመታት ቆይታ በኋላ ዘንድሮ ዋንጫ የመጨበጥ ዕድሉ የተጨናገፈው ለጥቂት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

የፈረንሣዩ ሞናኮ ቡድን የማንቸስተር ሲቲው ተከላካይ ሠርቢያዊው አሌክሳንደር ኮላሮቭን በዝውውር ለመውሰድ ንግግር እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ከታች የሚገኘውን የድምፅ ማጫወቻ ይጫኑ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ