1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማቻር በአዲስ አበባ ለአጭር ጊዜ ታስረው ነበር ተብሏል

ማክሰኞ፣ ኅዳር 13 2009

የደቡብ ሱዳን አማጽያን መሪ ሪየክ ማቻር ኢትዮጵያን አቋርጠው ወደ ሌላ ቦታ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ በክልከላ ምክንያት ተደናቀፈ፡፡ የአማጽያኑ ቃል አቃባይ ማቻር በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለአጭር ጊዜ ታስረው እንደነበር ለዜና ወኪሎች ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የቀድሞ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንትን መታሰር አስተባብላለች፡፡

https://p.dw.com/p/2T5HO
Südsudan Riek Machar Rebellenführer SPLM
ምስል picture-alliance/dpa/Stringer

Reik Machar briefly detained in Ethiopia - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ መንግስት የቀድሞውን የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት በአዲስ አበባ እንዳይተላለፉ ያገደው ባለፈው እሁድ ነበር፡፡ በዕለቱ ሪየክ ማቻር ላለፈው አንድ ወር ገደማ ከቆዩበት ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረው አዲስ አበባ ይደርሳሉ፡፡ አዲስ አበባን በመሸጋገሪያነት ተጠቅመው ወደ ሌላ ቦታ ለመጓዝ አቅደው የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ የኢሜግሬሽን ወደመጡበት እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡

ማቻር የሚመሩት የአማጽያን ቡድን ቃል አቃባይ ዲክሰን ጋትሉክ ለጀርመን ዜና አገልግሎት «dpa» እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ማቻርን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለአጭር ጊዜ አስረዋቸው ነበር፡፡ ባለስልጣናቱ ማቻርን ያሰሯቸው በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ድንበር ወደሚገኘው የአማጽያኑ መቀመጫ ለመጓዝ እንደመጡ በመጠርጠራቸው እንደሆነ ቃል አቀባዩ ይናገራሉ፡፡

የማቻር ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ ወደ ድንበር ከተማይቱ ፓጋክ ለመጓዝ እንዳልነበረ ጋትሉክ ቢገልጹም ወደየት ለመጓዝ አቅደው እንደነበር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ግን ማቻር ወደ ናይጀሪያ ለመጓዝ አዲስ አበባን በመሸጋገሪያነት እንደተጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ከናይጄሪያ መንግስት የመግቢያ ቪዛ በመነፈጋቸው ኢትዮጵያ ወደ መጡበት ለመመለስ መገደዷን ያስረዳሉ፡፡

“መጀመሪያ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ናይጄሪያ ለመሄድ ነበር በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጣው፡፡ ነገር ግን በመንገድ ላይ እያለ የናይጄሪያ መንግስት የሰጠውን ቪዛ መልሶ ከለከለው፡፡ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ህግ መሰረት ደግሞ ተቀባዩ ሀገር ቪዛውን ከከለከለ ያመጣው አየር መንገድ ወዳመጠበት መመለስ ነበረበት፡፡ ያ ነው የተደረገው፡፡ ስለዚህ ደቡብ አፍሪካ ተመልሷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አልታሰረም ማለት ነው” ሲሉ ዶ/ር ነገሪ ያስተባብላሉ፡፡

Südsudan Opposition Soldaten
ምስል picture-alliance/dpa/P. Dhil

ሪየክ ማቻር ወደ ደቡብ አፍሪካ መጀመሪያ ያቀኑት ከስድስት ሳምንት በፊት ህክምና ለማግኘት በሚል ነበር፡፡ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጋር የነበራቸው አለመስማማት እንደገና አገርሽቶ መዲናይቱ ጁባን ባለፈው ሐምሌ ጥለው ከወጡ በኋላ በጫካ ቆይተዋል፡፡ በነሐሴ ወር ከሀገራቸው ጋር ድንበር ወደምትጋራው ዲሞክራቲክ ሪፕብሊክ ኮንጎ ተሻግረዋል፡፡ በሱዳን ካርቱም እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ቆይታ ካደረጉ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘዋል፡፡  

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማቻር በኢትዮጵያ ቤተኛ ነበሩ፡፡ በደቡብ ሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ካለፈው ሶስት ዓመት ወዲህ እንኳ  ለፖለቲካ ድርድር ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለሱ ቆይተዋል፡፡ ደቡብ ሱዳንን የተመለከቱ ሶስት መጽሐፍት ያሳተሙት ጄምስ ሺማኙላ ኢትዮጵያ ለማቻር “ሲበዛ ቸር” ነበረች ያላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ማቻርን በድርድር ወቅት ከማስተናገድ አልፎ የደህንነት ዋስትና እስከ መስጠት ድረስ ወዳጅነት ሲያሳይ መቆየቱን ያስረዳሉ፡፡ አሁን ግን በማቻር ጉዳይ “ጥንቃቄን” መርጧል ይላሉ፡፡

“አሁን በደቡብ ሱዳን ባለው ሁኔታ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት በጣም ጠንቃቃ ሆኗል፡፡ ጥንቃቄው እንደቀድሞው ሪየክ ማቻርን ሲቀበል በደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ዘንድ አለመታየት ድረስ የሄደ ነው፡፡ ቀድሞ ማቻር ኤስ.ፒ.ኤል.ኤ ተቃዋሚ ስለነበር ነው፡፡ አሁን ግን በጁባ መንግስት ላይ ጦርነት አውጇል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በጣሙኑ ጠንቃቃ የሆነው የጁባ መንግስት የሪየክ ማቻርን መገኘት ይፋዊ አድርጎ እንዳይተረጉመው ነው፡፡ ይልቁኑም የጁባን መንግስት ለመጣል የሚደረግ ማንኛውንም የአማጽያን ንቅንቄን እንደማይደግፍ እንዲታይለት ይፈልጋል” ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ሺማኙላ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ወደ ደቡብ ሱዳን ለመሻገር ነው የሚለው አስተሳሰብ አይዋጥላቸውም፡፡ የአማጽያኑ መሪ በሶስት የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች ጦራቸውን ማስፈራቸውን የሚናገሩት ሺማኙላ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የማቻር በቦታው መገኘት ፋይዳ የለውም ባይ ናቸው፡፡ “የትም ቦታ ሆነው ጦራቸውን ማዘዝ እየቻሉ ለምን ወደ ደቡብ ሱዳን ይጓዛሉ” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ