1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥጋት የተጫነው የደቡብ ሱዳን የሰላም ፍለጋ ድርድር

ዓርብ፣ ግንቦት 3 2010

አዲስ አበባ ግንቦት 17 የሚጀመረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ውይይት ስጋት አንዣቦበታል፡፡ አሜሪካ ለደቡብ ሱዳን ስትሰጠው የቆየችውን ዕርዳታ በመከለስ ልታቋርጥ እንደምትችል ያስታወቀች ሲሆን ውጥረት ውስጥ የገባው የደቡብ ሱዳን መንግስትም “የዕርዳታው መቋረጥ ተቃዋሚ ወገኖች ሰላም ስምምነት ለመድረስ ያላቸውን ፍላጎት ያዳክመዋል” ሲል አስጠንቅቋል

https://p.dw.com/p/2xYPs
Südsudan Vereidigung Taban Deng Gai als neuer Vizepräsident
ምስል Reuters/J. Solomun

የደቡብ ሱዳን ድርድር ሐሙስ በአዲስ አበባ ይጀመራል

የአሜሪካ መንግስት ውሳኔውን በገለጸበት መግለጫ “በደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ለመድረስ የሚታየው መጓተት በእጅጉ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ እናም የምንሰጠውን ዕርዳታ በጥልቀት መከለስ እንጀምራለን” ብሏል፡፡ “ዕርዳታችን ለጦርነቱ አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ወይም ጦርነቱን እንዲያራዝም እና ምዝበራን እንዲያበረታታ አንፈቅድም” ያለው መግለጫው “የሀገሪቱ ብሄራዊ አንድነት መንግሥትም ሁሉን አካታች አይደለም፤ ቅቡልነቱንም አጥቷል” ሲል ነው ጠንከር ባሉ ቃላት የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን መንግስት የወቀስው፡፡

የዕርዳታ ክለሳው እንደ ጎርጎሳዊያን አቆጣጠር በ2015ቱ የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ስር Joint Monitoring and Evaluation Mechanism ለተባለው የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም መከታተያ መርሃ ግብር አሜሪካ ስትሰጥ የቆየችውን ዕርዳታ እንደሚያካትት መረዳት የተቻለ ሲሆን ዝርዝር ይዘቱና ሰብዓዊ ዕርዳታን ሰለማካተቱ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ ላለፉት ዐመታት ለመንግስትም ሆነ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ግዙፍ ሰብዓዊ ድጋፍ የምትለግሰው አሜሪካ ስትሆን የርስበርስ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ብቻ 3.2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጥታለች፡፡

የዕርዳታው መቋረጥ የሰላም ሂደቱን ያስተጓጉለው እንደሆነ SUDD Institute በመባል በሚታወቀው የደቡብ ሱዳን ገለልተኛ የጥናትና ምርምር ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑትን ሚስተር ዘካሪያ አኮልን ወደ ጁባ ስልክ ደውዬ ጠይቄያቸው ነበር፤

"በርግጠኝት ይህ ነው ማለት አልችልም፤ ሰብዓዊ ዕርዳታው በተወሰነ መልኩ ከተስተጓጎለ ወይም ከተቋረጠ ግን በትክክልም ዕርዳታ ፈላጊው ተራው ሕዝብ ላይ አሉታዊ ጉዳት ያመጣል፡፡ የአሜሪካ መንግስት በሰላም ሂደቱ መጓተት መበሳጨቱን መረዳት ይቻላል፡፡ ባሁኑ ሰዓት ዕርዳታውን ማቋረጥ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ሊያከራክር ይችል ይሆናል፡፡ ውሳኔው ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ሰላም ስምምነት የማምጣት ዕድሉን ግን በጣም ነው የምጠራጠረው፡፡ "

Südsudan Salva Kiir und Paul Malong Awan
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Patinkin

አሜሪካ የዕርዳታ ክለሳ ውሳኔዋን ያሳለፈችው ተመድ፣ አውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ አፍሪካ ኅብረት፣ ቻይና እና ተቃዋሚ ሃይሎች የተካተቱበት Joint Monitoring and Evaluation Commission የተባለው የሰላም ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ሰላም ስምምነቱ በቅርቡ የሚፈረም ከሆነ ለተቃዋሚ ወገኖች ደኅንነት ዋስትና የሚሰጥ ሁኔታ በሀገሪቱ የለም በማለት ባስጠነቀቀ ማግስት ነው፡፡ ኮሚሽኑ እንደሚለው የተወጊነት ሃላፊነት የተሰጠውና በጁባ ከተማ ብቻ ተወስኖ ያለው Regional Protection Force የተሰኘው ልዩ ሰላም አስከባሪ ሃይል በመላ ሀገሪቱ ጥበቃ ማድረግ የመቻል አለበት፡፡

የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በበኩሉ በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ባሉ አንዳንድ ግለሰቦች ላይ የጣለውን የጉዞ እና ገንዘብ እገዳ ማዕቀብ ለአንድ ዐመት ያራዘመ ሲሆን ተጨማሪ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ለመጣልም እያጤነ መሆኑን በያዝነው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡ ባለፈው የካቲት ደሞ አሜሪካ በተናጥል ጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ዝውውር ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል፡፡ ተመራማሪው ሚስተር ዘካሪያ ግን ማዕቀብ ለውጥ እንዳላመጣ ካሁን በፊት በተደጋጋሚ ታይቷል ባይ ናቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ አማፂያን እንደ አሸን መፍላታቸው የሰላም ድርድሩን አወሳስቦታል፡፡ የቀድሞው የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ፖል ማሎንግ በቅርቡ የመሠረቱት አማጺ ሃይልም አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ሰላም ውይይት ለመታቀፍ ኢጋድን እየጎተጎተ ይገኛል፡፡ ሚስተር ዘካሪያ ግንቦት አጋማሽ ሊካሄድ ከታቀደው የአዲስ አበባው ውይይት ምን እንደሚጠብቁ ጠይቄያቸው ነበር፤

"አሁን ጸጥታው ምክር ቤት እያደረገ ያለው ነገር አለ፡፡ አሜሪካም ሰላም ውይይቱ ሊጀመር ሳምንት ሲቀረው ሰሞኑን ዕርዳታ የመከለስ ውሳኔ አሳልፋለች፡፡ መንግስት ደሞ እነዚህ ወገኖች ለሰላም ሂደቱ አጋዥ እንዳልሆኑ አምኗል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ሲል ከነበሩበት በእጅጉ የተዳከሙት ተቃዋሚዎች የአሜሪካ ውሳኔ እና ጸጥታው ምክር ቤት በመንግስት ላይ የሚፈጥሩት ጫና መንግስትን ያዳክምልናል ብለው ያስባሉ፡፡ እንዲህ ከሆነ ትርጉም ያለው የሰላም ሃሳብ ይዘው ስለማይቀርቡ ምንም ስምምነት እንደማይደረስ ልንጠብቅ አንችላለን፡፡" 

Südsudan Waffenstillstand 01.02.2014 Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

የሳልቫ ኪር መንግስት በበኩሉ “የሰላም ውይይቱ ከከሸፈ አጠቃላይ ምርጫ አካሂዳለሁ” እያለ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ምዕራባዊያን መንግስታት ግን ዕቅዱን አልተቀበሉትም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በምህጻረ ቃሉ ኤስፒኤልኤም ተብሎ የሚታወቀውን ገዥውን ድርጅት መልሶ ለማዋሃድ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ በተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር ከሚመራው አማጺ ሃይል የተገነጠለውን አንጃ የሚመሩት ተቀዳሚ ምትል ፕሬዝዳንቱ ታባን ደንግ አንጃቸውን ከገዥው ፓርቲ ጋር ማዋሃዳቸውን በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ አድርገዋል፡፡ የገዥው ፓርቲ ውህደት በፕሬዝዳንቱ የሚመራውን ብሄራዊ አንድነት መንግስት በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተንታኞች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ሚስተር ዘካሪያም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው፤

"መጀመሪያ የደቡብ ሱዳን ችግር መነሻ ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የሀገሪቱ ቀውስ እኮ በኤፒኤልኤም መከፋፈል ሳቢያ የተፈጠረ ነው፡፡ የድርጅቱ ውስጣዊ ቀውስ ሳይነሳ ስለ አጠቃላይ ሰላም ስምምነት ማውራት አይቻልም፡፡ ከኤስፒኤልኤም ውጭ ያሉት ተቀናቃኝ ወገኖች እኮ ጠንካራ የሚባሉ አይደሉም፡፡ …ስለዚህ ድርጅቱን መልሶ ማዋሃድ ለሰላም ሂደቱ ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን ችግር የሆነው መልሶ መዋሃዱን የሚቃወሙ ወገኖች ንቅናቄው ከመጠን በላይ ስለገዘፈ በሀገሪቱ ዲሞክራሲን ለማስፈን አስቸጋሪ ይሆናል የሚል እምነት መያዛቸው ነው፡፡" 

አዲስ አበባ ላይ ባለፈው ታህሳስ የተፈረመው ተኩስ አቁም ተጥሶ ጦርነቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ከቀናት በኋላ የሚጀመረው ሰላም ውይይትም ለጦርነቱ መቋጫ ስለማስገኘቱ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡

ቻላቸው ታደሠ

ኂሩት መለሰ