1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ሥነጥበብ ለፍቅርና ለአንድነት በስዊዘርላንድ»

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23 2006

የጥበብ ሰው ስሜቱ ስስ ነው ይባላል። የጥበብ ሰው አብዛኛውን ጊዜ በአጠገቡ የሚከወኑ ነገሮችን እንደዋዛ ተመልክቶ አያልፋቸውም። በርን ስዊዘርላንድ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በእየሦስት ወሩ የሚያሰናዱትን የጥበብ እንቅስቃሴ እንመልከት።

https://p.dw.com/p/1Brn8
ምስል Fotolia/A. Burmakin

የጥበብ ሰው እውስጡ የሚንተገተገውን ስሜት ለጥበብ ታዳሚያን እስኪያካፍል ድረስ ፋታ የለውም። ከእራሱ አልፎ የሌሎችንም ስሜት የመኮርኮር አንዳች አቅም አለው፤ እውነተኛ የጥበብ መክሊት የተቸረው ጥበበኛ። «ሥነጥበብ ለፍቅርና ለአንድነት በስዊዘርላንድ» የተሰኘ የጥበብ ድግስና በዝግጅቱ ላይ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ የስዊዘርላንድ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን «ለም ዕውቀት» የተሰኘው ግጥሙን በእራሱ አንደበት ያስደመጠን ቴዎድሮስ አሽኔ አንዱ ነዉ።

የጻፈዉን ትረካ ያሰማን ደግሞ ጥላሁን ዛጋ። ሁለቱም ነዋሪነታቸው በርን ከተማ ውስጥ ነው። እስኪ የኪነጥበብ ድግሱን ከሚያስተናብሩት የጥበብ አፍቃሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ኤፍሬም ግርማይ ዝግጅቱን ለመጀመር ምን አነሳሳው?

የስዊዘርላንድና ጀርመን ድንበር ምልክት
የስዊዘርላንድና ጀርመን ድንበር ምልክትምስል picture-alliance/dpa

በእየሦስት ወሩ በሚሰናዳው በእዚህ የጥበብ ድግስ ላይ የስዕል አውደ-ርዕይ፣ ግጥሞችና መጣጥፎች፣ ቀርበው የጥበብ አፍቃሪያኑን ማዝናናታቸውን ኤፍሬም ገልጾልናል። መድረኩም ስዊዘርላንድ ነዋሪ በሆኑት «የአርሴማ ዲኮር» ነፃ አገልግሎት በኢትዮጵያ ባህላዊ ቁሳቁሶችና መጋረጃዎች አጊጦ ነበር።

«የምንኖረው በባዕድ ሀገር ነው፤ ባዕዳን ነን» የሚለው ጥላሁን ዛጋ ስዊዘርላንድ መኖር ከጀመረ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል። አሁን በርን የሚባለው ከተማ ነዋሪ ሲሆን፤ ቀደም ሲል ባዝል የሚባል ሌላ ከተማ ውስጥ ደግሞ ለስድስት ወራት ያህል ኖሯል። ስዊዘርላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ እግሩ ሲረግጥ የተሰማውን ስሜት «የግማሽ ቀን ሽራፊ ታሪክ» በሚል ርዕስ በብዕሩ ሸክፎታል።

የስዊዘርላንድ ሠንደቅ-ዓላማ ኮረብታው ላይ ሲውለበለብ
የስዊዘርላንድ ሠንደቅ-ዓላማ ኮረብታው ላይ ሲውለበለብምስል picture-alliance/dpa

ቴዎድሮስ ስዊዘርላንድ ውስጥ መኖር ከጀመረ ስምንት ዓመታት ግድም እንደሆነው ገልጾልናል። በውጭ ሀገር የኑሮ ቆይታው የነዋሪዎቹ የሥራ መንፈስና ጥንካሬ ምንጊዜም እንዳስቀናው ነው።

በሥነጥበብ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብከው ዝግጅት ላይ ከቀረቡ የጥበብ ትሩፋቶች መካከል «ቆማ ቀረች» የተሰኘው የቴዎድሮስ አሽኔ ግጥም ፈገግ ያሰኛል።

የፈጠራ ፅሁፉን በትረካ ያቀረበልን ጥላሁን ዛጋ በሚቀጥለው ሣምንት መጨረሻ ላይ ሊያቀርበው ያሰበውን «ምንድን ነው ነገሩ?» የተሰኘ አዲስ ግጥሙን በእራሱ አንደበት ያሰማናል። ሙሉዉን ቅንብር ከድምፅ ዘገባዉ ያድምጡ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ