1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥራ አጥነት፣ የፖለቲካ ለውጥ እና ውንብድና

ዓርብ፣ መጋቢት 6 2011

ብዙ የአፍሪካ ከተሞች መንግሥት ያለባቸው አይመስሉም። እኔ ራሴ በሔድኩባቸው አጋጣሚዎች እንዳስተዋልኩት ናይሮቢ መንገድ ላይ ትንሽ ገንዘብ ይዞ መቁጠርና መቀባበል ያስፈራል። የሸቀጥ ሱቆች ሳይቀሩ በፍርግርግ ብረቶች የታጠሩ ናቸው። ካምፓላ መንገድ ላይ ስልክ እያወሩ መሔድ አይደፈርም፤ በወንበዴዎች ይመነተፋል።

https://p.dw.com/p/3F6jp
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu
በፍቃዱ ኃይሉ

የኤትኤም ማሽኖቻቸው ሳይቀሩ በታጣቂዎች ይጠበቃሉ። በጆሃንስበርግ ደግሞ የባሰ ነው። መሐል ከተማ ካልሆነ በቀር ከተሞቹ ዳርቻ በሰላም «ወክ»’ ማድረግም አይደፈርም። ወንበዴዎች በጠራራ ፀሐይ አንገት አንቀው ኪስ እስከመበርበር ይደርሳሉ ይባላል። ይህ አዲስ አበባ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ አይስተዋልም። ነገር ግን አሁን አሁን በተደጋጋሚ የሚስተዋሉትን የውንብድና ድርጊቶች መንግሥት በቸልተኝነት ማለፉ ከቀጠለ የብዙ አፍሪካ ከተሞች ዕጣ ፈንታ የኢትዮጵያ ከተሞችም ይሆናል።

የጉዳዩ አሳሳቢነት

ባለፈው ሳምንት አንድ ልጅ መኪና እየነዳ ወደ ጅማ ደርሶ ሲመጣ ዩኒፎርም የለበሱ ታጣቂዎች ለምን እንደሆነ የማይታወቅ ክፍያ (ጉርሻ) ጠይቀውት ከፍሏል። ሌሎችንም ሲቀበሉ አይቷል። እምቢ ለማለት ደኅንነቱን ማረጋገጫ ዋስትና አልነበረውም። ሐረር ደርሶ መልስ የተጓዙ ጓደኞቼ መንገድ ላይ ደኅንነት እናስከብራለን ባሉ እና መለዮ ባልለበሱ ወጣቶች እንዲቆሙ ተደርገው ተፈትሸዋል። እዚያው ሐረር የሐረሪ ክልል መስተዳድር «የመንጋ አካሔድ» ባለው ድርጊት «መሬቱ የእኛ ነው» ባይ ቡድኖች 16 በሕጋዊ መንገድ የተሠሩ ቤቶችን በቅርቡ አፍርሰዋል። ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች ላይ እህል እና ሸቀጥ ጭነው የሚጓዙ መኪኖች የሕግ አስከባሪ ባልሆኑ ሰዎች ተገደው እየቆሙ ይፈተሻሉ። ንብረታቸውን ሜዳ ላይ እንዲበትኑ እና እንዲከስሩ የተደረጉበት አጋጣሚም በርካታ ነው።

ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን የሕግ አስከባሪ አባላት የወሰዱት ይህ ነው የሚባል እርምጃ የለም።

ለውጥ እና ውንብድና

ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን በተቆጣጠረበት ወቅት በከተሞች ከፍተኛ ውንብድና ተስፋፍቶ ነበር። በአዲስ አበባ የቡድን ፀቦች፣ መንገደኞችን መተናኮስ፣ እንዲሁም በትጥቅ የታገዘ ዝርፊያ ዋነኛ ሥጋቶች ሆነው ነበር። መኪና ላይ የተጫኑ ዕቃዎችን ለማውረድ ሳይቀር በየአካባቢው ያሉ ወንበዴዎች ከሚወስኑት ተመን ያነሰ ዋጋ መክፈል ቀርቶ ዕቃዎቹን በራሴ ሸክም አራግፋለሁ ማለት እንኳን አይቻልም ነበር። ይህ ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ቀጥሎ የኋላ ኋላ ባመዛኙ በመቀረፉ ምክንያት አዲስ አበባ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ የዜጎች የደኅንነት ስሜት ጨምሮ ነበር። ብዙ ሱቆች ሸቀጦቻቸውን በመስታወት ማሳያ ውስጥ ያውላሉ፤ ሰዎች ከባንክ ገንዘብ ተሸክመው መንገድ ላይ በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ። ማታለሎች እና ስርቆቶች እንዲሁም ኃይል የቀላቀሉ ዝርፊያዎች አሁንም ቢኖሩም በቀንና ሰው በተሰበሰበበት አይፈፀሙም ነበር።

አሁን አሁን ግን ነገሩ እየተቀየረ ይመስላል። ሥጋቱ አዲስ አበባን አይርገጥ እንጂ በአዲስ አበባ አጎራባች ከተሞች ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ ቡድኖች ተከስተዋል። በቢሾፍቱ ከመሐል ከተማው በቀር ዳርዳሩን በምሽት መንቀሳቀስ ሳይቀር አስፈሪ ሆኗል።

መንሥኤው ምን ይሆን?

በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚገመተው ሕዝብ ከ35 ዓመት በታች ነው። ከነዚህም በጣም የሚበዛው (የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ‘ሚዲያን’ የዕድሜ ክልል የሚሉት) 17 ዓመት ነው። ይህ እንግዲህ ኢትዮጵያን ወጣቶች የበዙባት (‘Youth bulge’ ያለባት) አገር ሲያደርጋት፥ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሥራ ፈላጊ እየሆነ በየዓመቱ ብቅ እንዲልም ያደርጋል። በገጠር ከወላጆች ወደ ልጆች የሚተላለፈው መሬት እየተሸነሸነ በመምጣቱ እና በቂ ምርት መስጠት ባለመቻሉ፣ እንዲሁም በሌሎች ገፊ እና ጎታች ምክንያቶች ከገጠር ወደ ከተሞች ከፍተኛ ፍልሰት እየታየ ሲሆን፥ ፈላሲያኑ ደግሞ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ተደራርበው በተለይ የከተሞችን የሥራ አጥነት ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርገውታል። የሥራ አጥነቱ ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔ (unemployment rate) 16.8 በመቶ ደርሷል።

ይህ የወጣቶች በከፍተኛ ቁጥር ወደ ሥራ ፈላጊው የሰው ኃይል መቀላቀል እና የሥራ አጥነት መብዛት፣ ከፖለቲካዊ ትኩሳቶች ጋር ተደማምሮ ለውንብድና መንገድ የጠረገ ይመስላል። ሥራ አጥነት፣ ፖለቲካዊ አመፅ እና ውንብድና ግንኙነታቸው በግልጽ ባይስተዋልም፥ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ለአመፅ የሚጠሯቸው እነዚህኑ ሥራ አጥና ብሶተኛ ወጣቶች ነው። በፖለቲካዊ አመፅ ወቅት ተደራጅተው ሲያምፁ እና ከሞላ ጎደል የአርበኝነት ማዕረግ ሲሰጣቸው የነበሩ ወጣቶች የፖለቲካ ለውጥ መጥቷል ሲባል በቴሌቪዥን ቢመለከቱም እውነተኛ ችግራቸው (የሥራ ፍላጎታቸው) ግን አልተቀረፈም።

ለፖለቲካዊ ለውጥ ሲያምፁ የነበሩት ኢ-መደበኛ ቡድኖች ወደ ውንብድና ተግባር አይገቡም ብሎ ማሰብ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል። ዛሬ ዛሬ በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለምን ተግባር የሚውል እንደሆነ የማይታወቅ ቀረጥ (እነሱ «መዋጮ» ነው የሚሉት) የሚሰበስቡት ወጣቶች በዚሁ መንገድ ለተቃውሞ የተደራጁ ወጣቶች ነበሩ። ብዙ ትኩረት ባይሰጠውም ከኅዳር ወር 2011 ጀምሮ በቡሬ ካምፕ እስካሁን ድረስ በሠራተኞቻቸው የታገቱት ሕንዳውያን ቀጣሪዎችም፣ በተመሳሳይ በሕግ እና ፍትሕ ስርዓቱ እምነት በሌላቸው ሠራተኞቻቸው «ደሞዛችን ይከፈለን» ወይም «አልተከፈለንም» በሚል የተፈጠረ ነው።

ሳይቃጠል በቅጠል

መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት ላይ የተወሰነ ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህንን የሚመጥን የሥራ ዕድል የመፍጠር ሙከራ እና የወጣቶችን ችግሮች ከመሠረታዊ ምንጫቸው የማድረቅ ሥራ እየሠራ አይደለም ማለት ይቻላል። የተከፈተው የፖለቲካ ምኅዳር የሥራ ዕድል ያልፈጠረላቸው ወጣቶች፣ በዚያ ላይ ያለውን የሕግ ማስከበር ክፍተት በማስተዋል ወደ ውንብድና እየገቡ ነው። ችግሩ ባስቸኳይ ካልተፈታ የኢትዮጵያ ከተሞችም ውንብድና እንደሚበዛባቸው የሌላ አገር ከተሞች ወደ አስፈሪ ምሽግነት ይለወጣሉ። 

 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።