1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥለ ወባ የተደረጉ ጥናቶች

ማክሰኞ፣ መጋቢት 2 2006

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ በተለይ ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት የወባ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ገንዘብ መድቧል። በዚህ አማካኝነት የተከናወኑ የተቀናጁ ጥረቶችም ለዉጥ ማሳየታቸዉ እየተነገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1BNUR
Moskitonetz
ምስል Edlena Barros

አፍሪቃ ዉስጥ የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመግታት ለዓመታት ሳይቋረጥ በሚካሄደዉ ዘመቻ በአንድ ወገን ተስፋ ሲታይ በአንዱ ደግሞ ዛሬም ወደ10 የሚሆኑ ሀገራት ከፍተኛ ስጋት እንዳጠላባቸዉ ተነግሯል። በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚለዉ ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት ካለባቸዉ አካባቢዎች ናይጀሪያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ዩጋንዳ፣ አይቮሪኮስት፣ ሞዛምቢክ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጋና፣ ማሊ፣ ጊኒ እና ቶጎ በጋራ 87 በመቶ የሚሆነዉን ይይዛሉ። ጥናቱ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም አንስቶ 44ሃገራት ላይ በማተኮር በሽታዉን ለመቆጣጠር የተደረገዉን ጥረት ለመመዘን ሞክሯል። እናም በወባ የመያዝ ከፍተኛ ስጋት ባለባቸዉ አካባቢዎች ለአስር ዓመታት በተካሄደዉ ቅኝት ይታመሙ የነበሩ ሰዎች ቁጥር በ16 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በተቃራኒዉ በወባ መያዝ እጅግ አያሳስብም በሚባልባቸዉ አካባቢዎች ቁጥሩ በ57 በመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል። ያም ሆኖ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም ብቻ በዓለም ዙሪያ በወባ የ620 ሺ ሰዎች ህይወት አልፏል።

በአንድ ወገን ወባ ጉዳት ያደርስባቸዉ የነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች የሚካሄደዉ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ በሽታዉን ፈፅሞ የማጥፋት ተስፋ አሳይቷል። ይህ ሊሳካላቸዉ ይችላል የተባሉት ዐራት ሃገራትም ኬፕቨርዲ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ አፍሪቃና ኢትዮጵያ ናቸዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ወባ የምታደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም ለመቆጣጠር በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደዉን ጥረት በየጊዜዉ መቃኘታችን ይታወስ ይሆናል። ለስኬት ዉጤቱ አስተዋፅኦ ያደረገዉም የተቀናጀዉ የመድኀኒት ርጭት፣ አጎበር የመጠቀም እድሉ መስፋፋት፣ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮጀክት ቤት ለቤት የሚሰጠዉ ምርመራና ምክር መሆኑን ተረድተናል። ኢትዮጵያ ወባን ፈፅማ የማጥፋት ተስፋዋ የለመለመ ነዉ የሚለዉን ዘገባ ተንተርሰን ያነጋገርናቸዉ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወባን ቁጥጥር የሚመለከተዉ ዘርፍ ባልደረባ አቶ ደረጀ ድሉ ብርሃን በሽታዉን ፈጽሞ የማጥፋት ሂደቱ ደረጃ በደረጃ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ፤

Anopheles Mücke schlägt zu
ምስል picture-alliance/dpa/ Birgit Betzelt/actionmedeor

በተቃራኒዉ ከዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ጋ በተገናኘም የወባ በሽታ ከቆላማ አካባቢ ወደደጋዉ በመዛመት እዚያም የሰዎችን ጤና ማወኩን ሊያስፋፋ እንደሚችል እየተነገረ ነዉ። በዚህ መሠረትም ምዝን የአየር እርጥበቱ ከፍተኛ በሆነባቸዉ የአፍሪቃ፣ እስያ፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ አሜሪካ ሃገራት ዉስጥ የሚገኙ ደጋማ አካባቢ ኗሪዎች ለወባ ሊጋለጡ እንደሚሉ አንድ ጥናት ያመለክታል። ጥናቱ በምሳሌነት በጠቀሳት ኢትዮጵያ የአንድ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት መጨመር ዉስጥ በከፍተኛ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን ለወባ በሽታ የማጋለጥ እድል እንደሚኖር ይዘረዝራል።

ላለፉት 25 ዓመታት በተለያዩ ሃገራት በወባ ላይ ጥናታቸዉን ሲያካሂዱ እንደቆዩ የገለፁልን የጥናቱ ተባባሪ በለንደን የንፅህና ጥበቃና የሞቃት አካባቢ በሽታዎች ተመራማሪ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ መምህር እና የህክምና ዶክተር የሆኑት ሜኖ ባዉማ፤ ስለጥናቱ እንዲህ ያስረዳሉ፤

Teaser 2 Global Ideas / Malaria

«በዚህ የጥናት ጽሑፍ ለማሳየት የሞከርነዉ በሞቃት ዓመታት ወባ በከፍተኛ አካባቢዎች ይከሠታል የሚል ነዉ። እናም በጣም ከፍተኛ የሚባሉትን ሁሉንም አካባቢዎች ብቻ አልተመለከትንም፤ ደብረዘይት አቅራቢያ የሚገኙ ከፍተኛ ስፍራዎችን ነዉ፤ እናም በእነዚህ አካባቢዎች በሞቃት ወቅቶች በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ይላል።»

ጥናቱ በዉስን አካባቢ የተሠራበት ምክንያትም የተሳሳተ ግንዛቤ ላለመፍጠር እንደሆነም ዶክተር ባዉማ ጨምረዉ አስረድተዋል። የጥናታቸዉ ዉጤት ለማመልከት ያለመዉም ሞቃት በሆኑ ዓመታት ወባ በከፍተኛ አካባቢዎች የሚከሰት ከሆነ የዓለም የሙቀት መጨመር በኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራዎች የበሽታዉ ስርጭት መጠን ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ነዉ። በዚህም ይላሉ፤

«ወባ ወትሮም በሚከሰትባቸዉ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ቀድሞ በአየር ንብረቱ ቀዝቃዛነት ምክንያት ወባ በማያሰጋቸዉ ስፍራዎች ምን ያህል ሰዎች ሊጎዱ እንደሚችሉ ሊገመት የሚችል ነዉ።»

ጥናቱ የተካሄደዉ ከአሜሪካኑ ሚቺገን ዩኒቨርሲቲ ጋ እንደሆነ እሳቸዉም ተባባሪ አጥኚ እንደሆኑ የገለፁልን ዶክተር ባዉማ ከዓመታት በፊት ጥናቱ አሁን በሕይወት የሌሉት ኢትዮጵያዊ የዘርፉ ባለሙያ አሰፋ ነጋ ቱሉ በለንደን የንፅህና ጥበቃና የሞቃት አካባቢ በሽታዎች ተመራማሪ ዩኒቨርሲቲ ለዶክትሬት ዲግሪ ሥራ የተጀመረ እንደሆነም ገልጸዋል። በህይወት የሌሉት ኢትዮጵያዊ ምሁር የራሳቸዉ አባት በወባ ህይወታቸዉን ማጣታቸዉን በመጥቀስም፣ ጥናቱ ለወደፊት በሽታዉ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ሊደረግ የሚገባዉን ማመልከቱን ዘርዝረዋል።

«ይህ ጥናት ስንት ሰዎች ለወባ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፤ ምን መደረግ እንደሚኖርበት፤ ችግሩን ለመከላከልና ሰዎቹን ከመታመም ለማዳንም ምን ያህል ገንዘብ ስራ ላይ መዋል እንደሚገባዉ ሳይንሳዊ መሠረት ሰጥቶናል። እናም ጥናቱ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የሚጎዱ ሰዎችን ህይወት በምን መልኩ አስቀድመን መከላከልን እንደሚገባን ያመላከተ ነዉ።»

Malaria in Tansania
ምስል Mirjam Gehrke

ሁለቱ የጥናት ዉጤቶች ያቀረቡት ግኝት የሚጋጭ ይመስላል። አንደኛዉ ስለስኬት ሌላኛዉ የሙቀት መጨመር ተከትሎ ይመጣል ስላለዉ የወባ በሽታ መስፋፋት ስጋት ይተነትናል። እናም ዶክተር ባዉማን ኢትዮጵያን ጨምሮ ዐራት የአፍሪቃ ሃገራት ወባን የማጥፋት ተስፋ እንደሚኖራቸዉ የገለጸዉን ዘገባ በመጥቀስ ሁኔታዉን በቅርበት ለዓመታት አጥንተዉታልና እንዴት ይመዝኑታል ብያቸዉ ነበር። ይሄ እኮ ቀድሞ ተሞክሮ ነበር አሉኝ፤ ቀጠሉ

«አዎ በ1960ዎቹ ተሞክሮ ነበር ደቡብ አፍሪቃና ኢትዮጵያ የወባ ማጥፊያ መርኀ ግብር ነበራቸዉ። ምክንያቱም ከሌላዉ የአፍሪቃ አካል ይልቅ ባላቸዉ ዝቅተኛ የአየር ንብረት ሳቢያ በሽታዉ በጣም የተባባሰባቸዉ ሃገራት አይደሉም። እናም ያ አዲስ ተነሳሽነት ነበር። እናም እኔ በግሌ ለ25ዓመታት በወባ ላይ እንደሠራ ባለሙያ ይህን ለመሞከር እንደዛሬ 50ዓመቱ ቀላል ይሆናል ብዬ ማመን ይከብደኛል። ያኔም ተሞክሮ አልተሳካም። ክትባት ሳይኖር፣ የመከላከያዉ ስልት ሳይረጋገጥ የተሳካ ዉጊያ ማካሄድ አይቻልም።»

ይህ ጥናት የዓለም የሙቀት መጠን ሲጨምር ወትሮ ያልነበሩ ነገሮች ባልተለመዱበት አካባቢ ይከሰታሉ የሚለዉን የተመራማሪዎች መላ ምት የሚያጠናክር ይመስላል። እናም ዶክተር ባዉማን ምናልባት ዓላማችሁ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራትን የሚያስተዳድሩ የዓለም ፖለቲከኞችና መሪዎች ለአየር ንብረት ለዉጥ ትኩረት በመስጠት የብክለት መጠን ቀንሱ የሚለዉ ጥሪ ትኩረት እንዲያገኝ ይሆን አልኳቸዉ፤

«ይህ የሚያመላክተዉ ነገር ይሁን እንጂ የምርመራችን ትኩረት አይደለም። ያም ሆኖ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች መነሻን የጠቆመ ነዉ። አዎ እዉነት ነዉ፤ ግን ያ የእኛ ሥራ አይደለም የሌሎች ኃላፊነት ነዉ። ሙሉ በሙሉ ትክክል ነሽ ግን የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ያን ያድርጉ እኛ ተመራማሪዎች ነን እንደዛዉ ሆነን ነዉ መቀጠል የምንሻዉ በተቻለን መጠን። ሆኖም አንዳንዴ ፖለቲካዊ ማመላከቻዎች ሊከሰቱ ይችላሉ አንቺ ያልሺዉ ያዉ ትክክል ነዉ።»

Forschungszentrum für Gesundheit von Manhica
ምስል Nadia Issufo

የተለያዩ ጥናቶች በየዘርፉ ባሉ ተመራማሪዎች መቅረባቸዉ የተለመደ ነዉ። አንዳንዴ ታዲያ ልክ ዛሬ እንደተመለከትነዉ የወባ ማጥፋት ተስፋ እና በተቃራኒ በቀረበዉ የወባ ከቆላ ወደደጋ የመዛመት ሁኔታ የሚጣረስ የሚመስልበት ጊዜ ያጋጥማል። ያም ቢሆን እንደዛሬዉ የወባ መከላከያ ሳይባል በ1960ዎቹ የወባ ማጥፋት ዘመቻዋን ስታጠናክር ወባ ማጥፊያ በሚል መንቀሳቀሷን በማስታወስ፤ እንደዉ ኢትዮጵያ ወባን ፈፅማ ማጥፋት የምትችልበት አጋጣሚ እንዴት ይታያል። አልኳቸዉ ባለሙያዉን፤

«እዉነት ነዉ የዚህ ችግሩ ምንድነዉ ኢትዮጵያ ይህን ማድረግ ብትችል እንኳን፤ ማለቴ ኢትዮጵያ አፍሪቃ ዉስጥ ለየት ያለች ሀገር ናት እናም በቴክኒክ ደረጃ ይህን ማድረግ ትችላለች፤ ችግሩ ግን በዙሪያዋ የሚገኙ ሃገራት ታዉቂያለሽ ሱዳን አለች፣ ኬንያ፤ ሶማሊያ አሉ፤ እነዚህ ወባ የተስፋፋባቸዉ ቦታዎች ናቸዉ። በተለይ ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ዝናብ የምታገኝ ሀገር ናት። እናም እዚያም ተመሳሳይ ስራ ካልተሰራ ተመልሳ ትወረራለች። ከኢትዮጵያ በሽታዉን ብታጠፉ ያለማቋረጥ የመከላከል ተግባሩ መቀጠል ይኖርበታል ከዉጭ እንዳይገባ። ይህ ዋና ጉዳይ ነዉ። ይህ ለማድረግ ደግሞ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፤ አለበለዚያ ትዋጊያለሽ ድል ታደርጊያለች መልሰሽ ትወረሪያለሽ እንደዚያ ነዉ የሚሆነዉ። አዎ በሽታዉን ማስወገድ ይቻላል ግን ተከታታይ የመከላከል ሥራዉ መቀጠል አለበት ከሌላ እንዳይመጣ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ