1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምግብና መጠለያ በመማፀን ላይ የሚገኙት ተፈናቃዮች

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 26 2013

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ቻግኒ ልዩ ስሙ «ራንች» አካባቢ የሰፈሩ ተፈናቃዮች፣ ለመጠለያና ለምግብ እጦት መጋለጣቸውን ተናገሩ፣ የአማራ ክልል በበኩሉ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ይላል፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበኩሉ ወሰን ተሸግሬ መርዳት አልችልም ባይ ነዉ፡፡

https://p.dw.com/p/3nUsI
Äthiopien Bahardar | Katastrophenprävention
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ድጋፍ እየተደረገ ነው ይላል፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበኩሉ ወሰን ተሸግሬ መርዳት አልችልም ባይ ነዉ 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ቻግኒ ልዩ ስሙ «ራንች» አካባቢ የሰፈሩ ተፈናቃዮች፣ ለመጠለያና ለምግብ እጦት መጋለጣቸውን ተናገሩ፣ የአማራ ክልል አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ይላል፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበኩሉ ወሰን ተሸግሬ መርዳት አልችልም ባይ ነዉ፡፡

ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ተከስቶ በነበረው ግድያና ወከባ ምክንያት ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቻግኒ አካባቢ በተለይም “ራንች” በተባለ ስፋራ የሰፈሩ ተፈናቃዮች፣ የደህንነት ስጋት፣ የመጠለያና የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Bahardar | Katastrophenprävention
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የቻግኒና የአካባቢው ኅብረተሰብ ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ውጪ ምንም ነገር እንደሌላቸው ነው ተፈናቃዮቹ የሚናገሩት፡፡  የተሰጠው ድንኳን 11 ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ ከህብረተሰቡ ብዛት አንፃር አቅርቦቱ በጣም አነስተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡አስቸካይ የምግብና የመጠለያ ችግሮቻቸው እንዲፈታላቸው ነው እነዚሁ ተፈናቃዮች የጠየቁት፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ እንዳሉት የተረጂው ቁጥር ሰፊ መሆኑና የእርዳታ ማዕከሉ አንድ ብቻ በመሆኑ እርዳታ ያልደረሰው ተረጂ እንደሚኖር ጠቁመው መንግስት ያን ማስተካከል አለበት ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ማስተባበሪያና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለዓለም ልጃልም ቻግኒ አካባቢ 41 ሺህ ተፈናቃይ እንደሚኖር ጠቁመው የርሳቸውን ምክትል ጨምሮ ሌሎችም ባለሙያዎች በታው ተሰማርተው እገዛ እደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ በበኩላቸው ድጋፉ በፌደራል በኩል ወደ አማራ ክልል ስለተላከ ወሰን ተሸግረን እርዳታ አናቀርብም ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል 258ሺህ ተፈናቃዮች ሲኖሩ በወር 46 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ወጪ እየተደረገ እንደሆነ ኮሚሽነር ዘለዓለም አመልክተዋል፡፡

ዓለምነዉ መኮንን

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ