1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ መጣ፣ ፓርቲ ደግሱ!

ዓርብ፣ ጥር 1 2012

ሰሞኑን የፓርቲ ውሕደቶች፣ ጥምረቶች፣ አዳዲስ ድርጅት ምሥረታዎች ዜናቸው ተበራክቷል። ለመሆኑ የዘንድሮውን ሽር ጉድ ለየት የሚያደርገው ነገር አለ? የዘንድሮውን ምርጫ ስንጠብቅ፣ ምን እንጠብቅ? ብዙዎች “ይራዘማል” የሚል ግምት ነበራቸው።

https://p.dw.com/p/3Vyo8
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

ሰሞኑን የፓርቲ ውሕደቶች፣ ጥምረቶች፣ አዳዲስ ድርጅት ምሥረታዎች ዜናቸው ተበራክቷል። የፖለቲካ ለውጡ ስሜት እምብዛም ስላልደበዘዘ የዜናዎቹ አድማጮች የፖለቲካ ፓርቲዎች ድግሱን ከዚህ ለውጥ ጋር ሊያያይዙት ይችላሉ። ነገር ግን ባለፉት አምስት ምርጫዎችም ስንመለከት የከረምነው ይኼንንኑ ዓይነት ነው። ምርጫው ጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ሲቀሩት የአዳዲስ ፓርቲዎች እና ጥምረቶች ዜና ይጧጧፋል። እንዲያውም አንዳንድ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት እንጂ በምርጫዎች መሐከል ባለው ጊዜ ድምፃቸው ካለመነሳቱ የተነሳ እስከ መኖራቸውም ይዘነጋሉ። ለመሆኑ የዘንድሮውን ሽር ጉድ ለየት የሚያደርገው ነገር አለ? የዘንድሮውን ምርጫ ስንጠብቅ፣ ምን እንጠብቅ?

“ምርጫው ከተካሔደ…”

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የትኛውም የፖለቲካ ውይይት መድረኮች ላይ ስለ ምርጫው ጉዳይ በተነሳ ቁጥር “ከተካሔደ…” የሚል ቅጥያ ማስቀመጥ ፋሽን ሆኖ ነበር። ብዙዎች “ይራዘማል” የሚል ግምት ነበራቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ እያወጣሁ ነው በማለቱ ብዙዎች እንዳዲስ የምርጫውን አጀንዳ እያራገቡት ነው። በርግጥም ካለፉት ምርጫዎች ሁሉ በተለየ ጉጉት እየተጠበቀ ያለ ምርጫ ስለሆነ አጀንዳ መሆን አያንስበትም። አንዳንዶች በፍርሐት እየራዱለት ነው፣ አንዳንዶች ደግሞ እየናፈቁት ነው።

በፍርሐት የሚርዱት ከፖለቲከኞቹ ይልቅ መራጮች ናቸው። የምርጫ ሒደቱን ወይም ውጤቱን ተከትሎ አለመረጋጋት ይኖራል የሚለው ስጋት አሁንም በብዙዎች አዕምሮ እየተጉላላ ነው። እነዚህኞቹ ቀድሞም “ምርጫው ከተካሔደ…” የሚለውን የሚደጋግሙት በተራዘመ እና ሰላማችንን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ባራዘምን በሚል ምኞት ነው። ነገር ግን ተዘጋጅተው ስላልጨረሱ እንዲራዘም ሲወተውቱም የነበሩ አሉበት። እነርሱም ቢሆኑ የሕዝቡን ስጋት ነው እንደ ሰበብ የሚደረድሩት። ምርጫው የመራዘም ዕድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ በተረዱ ማግስት ግን “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” እንደተባለው ዓይነት ድግስ ጀምረዋል። ናፋቂዎቹ ግን ምርጫው በጊዜው ከተካሔደ ከእኛ የተሻለ የማሸነፍ ዕድል ያለው ሌላ ተፎካካሪ የለም ብለው የሚያስቡት ናቸው።

ድጋሚ ምዝገባ…

የ1997ቱ ምርጫ ከሌሎቹ ሁሉ ምርጫዎች የተጧጧፈ እና አጓጊ ነበር። ለዚህ አንዱ ምክንያት የማሸነፍ ዕድል ያላቸው ተፎካካሪዎች በግልጽ መለየት መቻላቸው ነበር። እነዚህ ሦስቱም ተፎካካሪዎች ሁሉም ከአንድ በላይ ፓርቲዎችን ያቀፉ ነበሩ። ገዢው ኢሕአዴግ የአራት ክልላዊ ፓርቲዎች ግንባር ሲሆን፥ ሌሎች በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገቡ አጋሮችም ነበሩት። ቅንጅት እና ኅብረት በሚል በአጭሩ የሚጠሩት ተፎካካሪዎችም የተለያዩ ፓርቲዎችን ለምርጫ በማሰባሰብ የያዙ በተመሳሳይ የምርጫ ምልክት የሚወዳደሩ አካላት ነበሩ። ይህ ሁኔታ በወቅቱ ከነበረው የፖለቲካ ድባብ ጋር ተደማምሮ ለመራጮች ግልጽ እና በቁጥር ያልበዙ አማራጮች እንዲሆኖሯቸው አስችለዋል።

አሁን እንደምርጫ ቦርድ ገለጻ ወደ 70 የሚደርሱ ሰርተፊኬት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ሆኖም ታኅሣሥ 27፣ 2012 በወጣ ማስታወቂያ በሁለት ወር ውስጥ የተሻሻለው የምርጫ አዋጅ 1162ን ተከትሎ በወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ እንዲመዘገቡ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸዋል። ይህም ማለት የካቲት መጨረሻ ላይ ለምርጫ ለመወዳደር ብቁ የሆኑት እና ያልሆኑት ፓርቲዎች ይለያሉ። ሆኖም ኦነግ፣ ኦፌኮ እና ኦብፓ የተሰኙት ድርጅቶች እንደሚመሠርቱት የተነገረው ትብብር፣ ሕወሓት አቋቁመዋለሁ ያለው የፌዴራሊስት ኀይሎች ትብብርን የመሳሳሉ ጉልህ ፓርቲዎች የጥምረት ሰርተፊኬት ብቻ ሳይሆን የየራሳቸውን ሰርተፊኬትም በአዲሱ ሕግ እና መመሪያ መሠረት ማሳደስ መቻል አለባቸው። ስንቶቹ ይሳካላቸው ይሆን?

የሆነ ሆኖ በመጋቢት ወር ላይ ከ25 ያልበለጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ይኖራሉ ብሎ ማሰብ ለስህተት አይዳርግም። ብዙዎቹ ፓርቲዎች በፖለቲከኞቹ አጠራር "ሱቅ በደረቴ" ናቸው። ከጥቂት የቤተሰብ አባላት በቀር የእውነት አባላት የሌላቸው ናቸው። ተጣርተው ከሚተርፉት ውስጥ ደግሞ አገር ዐቀፍ ፓርቲዎቹ ዐሥርም አይሞሉም። በጥምረት ከተሳሰሩ ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ይሆናል። ይህ ለመራጮች መርዶ አይደለም፤ እንዲያውም ለፉክክር በጣም የተመቸ እና ግልጽ ነው። ድምፃቸውን አላግባብ ከመበታተን ያድነዋል።

የፉክክሩ አስኳል

የ1997ቱ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር ነበረው። ነገር ግን ፉክክሩ በከተሞች አካባቢ ያየለ ነበር፤ ስለዚህ አዲስ አበባ የጡዘቱ ማዕከል ነበረች። ዋና ዒላማውም የፌዴራል መንግሥቱ ነበር። የ2012ቱ ምርጫ ፉክክር ግን በክልሎች ውስጥ የተባባሰ ነው የሚሆነው። በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራ እና ሶማሊ ተቃዋሚዎች እና ገዢዎቹ መሳ ለመሳ በሆነ አቅም ነው የሚጋጠሙት። የመጀመሪያው የፉክክር አስኳል የመደራጃ መሥፈርቱ ራሱ ነው። የዘውግ ብሔርተኝነት እና በዜግነት መደራጀት ላይ መራጮች ሪፈረንደም ያካሒዳሉ ብሎ ማለት ይቻላል። ፖሊሲ በአሁኑ ፖለቲካ የብዙዎችን ቀልብ ላይማርክ ይችላል፤ ይህንንም የኦነግ ሊቀመንበር በድፍረት ተናግረውታል። ውክልና በፖሊሲ ሳይሆን በማንነት ነው የሚል አስተያየት በብዛት እየተስተናገደ ነው። በውጤቱም የክልሎቹ ምክር ቤቶች ባልተለመደ ሁኔታ በአንድ ድርጅት ቁጥጥር ውስጥ መውደቃቸው ላይቀር ይችላል። በተግባር የለም ሲባል የነበረው ፌዴራሊዝም የሚፈተንበት ጊዜ ተቃርቧል። የኢትዮጵያ ፖለቲካም የኃይል ሚዛን ከምርጫው በኋላ ተጠቃሎ ወደ ክልሎች ሊዞር ይችላል።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

በፍቃዱ ኃይሉ