1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርምር በ አይ ኤስ ኤስ እና የጀርመን ተሳትፎ

ሐሙስ፣ ኅዳር 4 2007

በሙያ የአፈርና ቋጥኝ እንዲሁም የእሳተ- ገሞራ ተማራማሪ ነው-- «ጂዎፊዚስት»፤ ጠፈርተኛ ፣ አሌክሳንደር ጌርስት! ካለፈው ዓመት ግንቦት 20 ቀን 2006 ዓ ም አንስቶ ግን፣ እስካለፈው እሁድ፣ ከምድር አናት ላይ ሆኖ ፣ ማለት 418ኪሎሜትር ከፍ ብሎ ነበረ ምርምሩን ሲያካሂድ የቆየው።

https://p.dw.com/p/1DlzR
ምስል picture-alliance/dpa/Alexander Gerst/ESA

በጠፈር ጣቢያ 6 ወራት ገደማ ሲያካሂድ የቆየበትን ተልእኮ አጠናቆም እንሆ ከትናንት በስቲያ ጎሕ ሲቀድከባልደረቦቹ ሩሲያዊው ማክሲም ሱራየቭና አሜሪካዊው ሬይድ ዋይዝማን ጋር ባይኮኑር ካዛኽስታን በጤና ወደ ምድር ለመመለስ በቅቷል። ከከዛኽስታን ወደ ጀርመን በመመለስም ፤ የጀርመን የጀርመን የሕዋ ምርምርና የጠፈርተኞች ማሠልጠኛ እሚገኝበት ኮሎኝ ገብቷል።

Raumfahrtzentrum in Baikonur Russland
ምስል AFP/Getty Images/Kirill Kudryavtsev

እሁድ ሌሊት ለሰኞ አጥቢያ ጎሕ ሲቀድ ፣ ISS በሚል የእንግሊዝኛ ምህጻር ከምትታወቀው የጠፈር የምርምር ጣቢያ አንስቶ ፤ መሬት ላይ በካዛኽስታን ለማረፍ የወሰደው ጊዜ 3 ሰዓት ተኩል ነው።

የጀርመንና የሕዋና ከባቢ አየር እንዲሁም የበረራ መ/ቤት የቦርድ ሊቀመንበር ዮሐን ዲትሪኽ ቮዖርነር የአሌክሳንደrር ጌርስት ፣ ተልእኮ ተሳክቶ መንኮራኩሯ ሶዩዝ፣ በእቅዱ መሠረት ፣ አሌክሳንደርንና ሁለቱን ጠፈርተኞች ፣ አሣፍራ ያለሳንክ መመለሷ እጅግ ነው ያስደሰታቸው። ለአሌክሳንደር ጌርስት፣ ከባድ ኃላፊነት ይሰማቸው እንደነበረ የገለጹት ዮሐን ዲትሪኽ ቨኧርነር ይህን ነበረ ያሉት----

«በእቅዱ መሠረት ፤ ከሌሊቱ ለ 11 ሰዓት 2 ደቂቃ ጉዳይ ላይ መንኮራኩሯ ተመልሳ ምድር ላይ ማረፏ በተረጋጋ ሁኔታ ነው የተነገረው። ይሁንና ጉዞው የተለያዩ ሳንኮች ሊያጋጥመው ይችል እንደነበረ ሊዘነጋ አይገባም። መንኮራኩሩ፤ ወደ ምድር ከባቢ አየር ሲገባ ትክክለኛ ማዕዝን ተክትሎ መብረር ይኖርበታል። ከአየር ወደ ምድር መውረጃው ልዩ ጃንጥላ መከፈት መቻል አለበት፤ የመንኮራኩሯ ፍጥነት መግቻ መሳሪያም በትክክል መሥራት ይጠበቅበታል። ይህ ሁሉ ያላንዳች ሳንክ የሚከናወን ነው ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ስለሆነም ፣ አሁን ከጭንቀት በመገላገሌ ደስ ብሎኛል። »

Alexander Gerst, Maxim Surajew/Russland und Reid Wisemann/USA // ISS
ምስል Reuters

አሌክሳንደር ጌርስት ፤ 6 ወር ገደማ ምን ነበር ሲያካሂድ የቆየው? በሕዋ የሚደረገው ምርምር ውጤት በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ እስከም ን ድረስ ነው? ከምድር ርቆ ፣ ክብደት ትርጉም የለሽ በሆንበት፣ ማለትም የስበት ኃይል ፈጽሞ በሌለበት ቦታ ፣በሰው ሰውነት ውስጥ ፣ ምን ዓይነት ለውጦች ናቸው የሚታዩት? ጠፈርተኞች በሕዋ ረጅም ጊዜ ቆይተው ወደ ምድር ሲመለሱ የስበት ኃይል መኖርና አለመኖር ምን ያስከትልባቸዋል? እርግጥ ነው የስበት ኃይል በሌለበትና የሚተነፈስ ንጹህ አየር (ኦክስጂን) ለሴኮንድም ቢሆን ችላ የማይባል እጅግ አስፈላጊ ስንቅ በሆነበት ሕዋ ፤ ኑሮ በፍጹም በምድር የተለመደው ዓይነት አይደለም። ለዚህም ነው ፣ ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት፣ ትናንት ኮሎኝ መዳረሻ -ፖርትዝ፣ በሚገኘው ቤተ -ሙከራ እንደደረሰ ፣ አጠቃላይና ሰፊ የጤና ምርምራ እንደሚደረግለት የተገለጠው።። ስለምርመራው ዓይነት ---የጀርመን የአየር ምርምርና የሕዋ ጉዞ ጉዳይ ማዕከል የቦርድ ሊቀመንበር፣ ዮሐን ዲትሪኽ ቨኧርነር---

«ምርመራው የሚያተኩረው፤ በሚያስደንቅ ሁኔታ በጠፈር ጣቢያ ፣ ብዙ የቤተ ሙከራ ተግባራት ተካሂደዋል። ከተተኮረባቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል፤ በተለይ የሰውነት አካላት ቶሎ የማርጀት ጉዳይ ዋናው ነው። የቆዳ መጨማተር የአጥንት መሟሸሽ በአፋጣኝ የሚከሠተው ከመሬት ይልቅ በሕዋ ነው። ስለሆነም በአንድ በኩል ለጠፈርተኞች ደሕንነት ማሰቡ እንዳለ ሆኖ፣ በህክምና ረገድ የሚደረገው ሰፊ ምርምርም ትልቅ ትርጉም ነው የሚሰጠው ። ቀስ በቀስ በምድር ላይ ካለው ብርቱ የስበት ኃይልም ሆነ ክብደት ጋር እንደገና የመለማመዱ ሂደት በጥሞና ክትትል የሚደረግበት ይሆናል። 6 ወራት ከስበት ኃይል ቁጥጥር ውጭ የቆየ ሰው ፣ ወደ ምድር ሲመለስ በመጀመሪያ ግር የሚያሰኝ ሁኔታ ያጋጥመዋል። ልብ በሉ፤ ሰው ሲጋደም የራስ ቅሉ፤ ከቀሪው የሰውነቱ ክፍል ሁሉ፤ የተዘቀዘቀ መስሎ ሲሰማው! አስገራሚ ስሜት ነው! 6 ወራት ገደማ አንዳች የስበት ኃይል በሌለበት ፤ ራስ ፣ እግር ፣ ላይ ታች የሚባል ሁኔታ በሌለበት ቦታ ቆይቶ አሁን በምድር ባለው የስበት ኃይል ሳቢያ እንቅሥቃሤውን ለማስተካከል ቀስ በቀስ መለማመድ ይኖራል። የስበት ኃይል በሌለበት በሕዋ፣ ደም ሲዘዋወር ፤ ባመዛኙ ወደ ጭንቅላት ነው የሚሠራጨው ።

ISS Internationale Raumstation
ምስል Nasa/dpa

በመሬት ጭንቅላት ከላይ እግር ከታች ሆኖ ነው ደም በመላ ሰውነት ውስጥ የሚዘዋወረው። ታዲያ የቦታ ለውጡ በጤንነት ላይ የሚያስከትለው ፣ የሆነ ሳንክ እንዳይኖር በጥሞና መከታታል ተፈላጊ ይሆናል። ወደፊት በተሟላ ጤንነት ለመኖር ጥንቃቄ ያሻልና!»

ምዕራባውያን ጠፈርተኞች ፤ ከሕዋ መልስ ፣ ለምርመራ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የበረራና የሕዋ አስተዳደር መቤት (NASA) ነበረ የሚላኩት። አሁን ግን በፖርትዝ ፣ ኮሎኝ በሚገኘው፤ Envihab በመባል በታወቀው ዘመናዊ ልዩ ቤተ ሙከራ ነው ምርመራው የሚካሄደው። ስሙ

ከእንግሊዝኛው Environment እና Habitat ከተሰኙት ቃላት ተቀንጭቦ የተሰወሰደ ነው። ልዩውን የህክምና ምርመራ ለማከናወን ብቃቱ ያላቸው ሃኪሞች መኖራቸውን ጀርመናውያን NASA ን ማሳመን እንደቻሉም ነው የገለጡት።

Alexander Gerst feiert die Weltmeister mit
ምስል picture-alliance/AP Photo

መልስ ጉዞው፤ በሕዋ ጣቢያ (ላቦራትሪ) ም መሥራቱም ቢሆን ፣ ሁሉም ከአደጋ ነጻ ነው ማለት አይቻልም። ጥቅምት 19 ቀን 2007 ፣ ስንቅ አመላላሺው መንኮራኩር የደረሰበትን መሰናክል አስመልክቶ አሌክሳንደር ጌርስት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ፣ ከዚያ የከፋ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችል እንደነበረ የዘነጋበት ጊዜ አለመኖሩን ነው የጠቀሰው። ከሳይንሳዊ ምርምሩ በተጨማሪ ፣ ጌርስት በተለያዩ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፤ ስለአስደናቂው ሕዋ ፤ ብርቅ -ድንቅ ስለሆነችው ሰማያዊዋ ፕላኔት (ምድር) እርሷን የመጠበቅ ፣ የመንከባከብ ብርቱ ኀላፊነት መሸከም እንደሚያስፈልግ ባለፉት 6 ወራtwe ያስተላለፋቸው መልእክቶች አለቆቹን ጭምር አርክቷል። አሌክሳንደር ጌርስት ባለፈው የዓለም ም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር፣ የጀርመንን ብሔራዊ ቡድን በማበረታታት፣ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን እንደበቃም በትዊተር የደስታ መግለጫ መልእክቱን ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።

Sojus Kapsel Landung 14.05.2014
ምስል Reuters/Dmitry Lovetsky/Pool

ለመሆኑ፤ ተጓዦችንና ታዛቢዎችንም አስደማሚ ከሚመስለው ጉዞ ባሻገር ፣ በዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ(ቤተ-ሙከራ)የሚካሄደው ምርምር በምድር ላይ ለምንኖር ሰዎች ምን ጠቀሜታ አለው?

«በመጀመሪያ ሳይንስ ምንጊዜም ሰዎችን እንደሚጠቅም፣ እንደሚረዳ ነው የምገነዘበውና ተስፋም የማደርገው። ። በዚህ ረገድ የሚቃረን ጉዳይ የለም።በዓለም አቀፍ የሕዋ ቤተ-ሙከራ(ISS) የሚካሄደው ምርምር ፣ ምድር ላይ ሰዎችን ይጠቅማል። ለምሳሌ የደም ግፊትን ጉዳይ እንመልከት።

የስበት ኃይል በሌለበት ፣ ሥፍራ የደም ግፊት ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው እንዲሁም በሰውነት ውስጥ በሽታን የሚከላከሉ ሕዋሳት ተግባር እንዴት እንደሆነ ማወቁ ይበጃል። ምድር ላይ በሽታ የመከላከሉ ተግባር ሲዳከም AIDS ተከሠተ እንላለን። አንዳንዴም የመከላከያው ኃይል በተለይ ቀዶ ጥገና ሲደረግ ያይላል። በሕዋ ሰውነት በሽታን የሚከላከልበት ሂደት የተለዬ ነው። እናም ልዩነቱን ጠንቅቆ በማወቅ የሳይንስ ጠበብት ፣ በምድር ላይ የሚገኙ ሰዎች በሕክምና ረገድ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበትን ዘዴ እንዲሹ ሊረዳ ይችላል።

በሕዋ የብረታ -ብረት ዓይነቶችን ባህርይ መርመርና ማወቅ ተፈላጊ ነው። የተለያየ ክብደት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን የሚለያዩበት ሁኔታ አለ። ስለሆነም፣ ለምሳሌ ያህል፣ የአይሮፕላን አንቀሳቃሽ ሞተሮችን በቀላሉ አሻሽሎ ለመሥራት ፣ በሕዋ በብረታ-ብረቶች ላይ ምርምር ማድረጉ ይጠቅማል።»

ገና ብዙ ያልታወቁ ፤ ምላሽ ያልተገኘላቸው ጉዳዮች ስላሉ ፣ ሰዎች ወደፊት ቅድሚያ በመስጠት የሚያርፉት ጨረቃ ላይ እንደሚሆን የጠቆሙት ቨኧርነር ፣ የማርስ ጉዞ የዘመናት ሕልም ቢሆንም ፣ እንደማይቀር ፤ ሆኖም ብርቱ ፈተናን የሚደቅን መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም። ወደ ማርስ የሚደረግ ጉዞ አሉ ቨኧርነር--

Blick auf Gaza von der ISS
ምስል picture-alliance/dpa/ESA/NASA

«ሰኞ ፤ ማክሰኞ፤ በማንኛውም ቀን ሊሆን ይችላል። ጊዜውን፤ ቀኑን በዚህ ዓመት ወርና ዕለት ብሎ ለመግለጽ ካሁኑ አስቸጋሪ ነው። አሁን ባለን የሥነ-ቴክኒክ ደረጃ ማርስ ደርሶ ለመመለስ 2 ዓመት ነው የሚወስደው። እስካሁን ሰው በሕዋ 6 ወር ስላሰለፈበት ሁኔታ ነው የተነጋገርን። ታዲያ እጅግ ሰፊ ልዩነት አለ። በሽታ ቢያጋጥም ፣ ከዓለም አቀፉ የሕዋ ቤተ ሙከራ ወደ ምድር ለመመለስ የጥቂት ሰዓቶች ጉዳይ ነው። ወደ ማርስ በሚደረግ ጉዞ በሽታ ቢያጋጥም፣ ከ 2 ዓመት በፊት ምንም ማድረግ አይቻልም።

Drei Raumfahrer von der ISS in Kasachstan gelandet 11.09.2014
ምስል Reuters/M. Shipenkov

ይህ ነው አንዱ የሚያሳስበውና የሚያመራምረው ጉዳይ! ደርሶ ለመመለስም ማርስ ላይ ሮኬት ያስፈልጋል። እንደሚመስለኝ በሚመጡት 20 እና 30 ዓመታት ገና ብዙ መደረግ አለበት። ግራም ነፈሰ ቀኝ ሰዎች የማወቅ ጉጉታቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ጉዞውን ፣ አንድ ቀን ተግባራዊ ለማድረግ ከመጣር አይቦዝኑም ። ለዚህም በሕዋው ISS የሚደረገው ምርምር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ቤተ -ሙከራው በአርግጥ ለታሰበው ዓላማ እጅግ ጠቃሚና የተሟላ ሁኔታ ያለው የምርምር ጣቢያ ነው።»

ጌርስት፤ በዓለም አቀፉ የሕዋ የምርምር ጣቢያ በነበረበት ጊዜ ምን እንደናፈቀው ተጠይቆ ፣ ፒሳ መግመጥና ቢራ መጎንጨት መሆኑን ገልጦ ነበረ። ይሁንና ይህን ፍላጎቱን መሬትን ከረገጠ በኋላም ወዲያው ማሟላት አልቻለም ፤ ስለማይፈቀድ!

እስካሁን ንፁህ የሚጠጣ ውሃ ፣ እርሱንም ቢሆን ቀስ በቀስ እያረፈ እንዲጎነጭ እንጂ ባንድ ጊዜ ብዙ ውሃ እንዲጠጣ አልተፈቀደለትም። በሚመጡት ቀናት ግን ቀስ በቀስ የናፈቀውን እንዲያገኝ ይፈቀድለታል። አንጀቱን የሚያውክ ባጠቃላይ ጤንነቱን የሚያቃውስ ሁኔታ ድንገት እንዳያጋጥም ሥጋት በመኖሩ ነው የተከለከለው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ