1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርምሩ የቀጠለው ኤችአይቪ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 2011

በአሁኑ ጊዜ በዓለም 37 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ በደሙ ውስጥ የኤች አይቪ ተሐዋሲ እንደሚገኝ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በጎርጎሪዮሳዊው 2017ዓ,ም ብቻ በተሐዋሲው አዲስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1,8 ሚሊየን እንደሚደርስ ነው የተነገረው። መረጃዎች የሚጠቁሙት ሐዋሲው በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የሚያውቁት 75 በመቶው ብቻ መሆናቸውን ነው።

https://p.dw.com/p/3EsDS
AIDS Medikamente
ምስል ImmunoLogik

«የሰዎች ግንዛቤ በፊት ከነበረው ይሻላል»

ከሰሞኑ ይፋ የሆነ የምርምር ውጤት የኤድስ አማጪው ኤች.አይ.ቪ ተሐዋሲ ያለበትን ግለሰብ በህክምና ዘዴ ከተሐዋሲው ነጻ ማድረግ መቻሉን ያመለክታል። ተመራማሪዎቹ  እንደገለፁት ኤችአይቪ ተሓዋሲ በደሙ ውስጥ የነበረበትን ግለሰብ ከዚህ ነፃ ማድረግ የተቻለው፤ ኤችአይቪን በተፈጥሮ መቋቋም ከሚችል ሰው መቅኒ ሴሎችን ወስደው በማባዛት ነው። ይህን ዘዴ ተጠቅመው ሴሎቹ ወደ ሰውነቱ እንዲዛወሩ የተደረገለት ሰው ላለፉት 18 ወራት አንዳች የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ሳይውጥና ሳይወስድ መቆየቱም ተነግሯል።

በዚህ የህክምና ዘዴ የመጠቀም ዕድል ያገኘው አሜሪካዊው ቲሞቲ ሬይ ብራውን ምንም እንኳን የሚያስገኘው ውጤት አጓጊ ቢሆንም ሕክምናውን ለሁሉም ሰዎች የማዳረሱ ነገር ግን አዳጋች መሆኑን ይናገራል።

«ስለዚህ ታካሚ በጣም ደስ ብሎኛል። ይሁንና ግን በርካታ ሰዎችን የሚያድን መድሐኒት አይደለም። ምክንያቱም ይህን የሕዋሳት ዝውውር ለማከናወን የሕክምና ሥነ-ምግባር እንደመኾኑ የደም ካንሰር ሊኖርብህ ይገባል።»

በተመሳሳይ የህክምና ዘዴ አዎንታዊ ውጤት ሲመዘገብም ይህ ለሁለተኛ መሆኑ ነው። የቲሞቲ ሬይ ብራውንን ሃሳብ በአዲስ አበባ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሀኪም ቤት የበሽታዎች መከላከል ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አስቴር ሸዋአማረ  ይጋራሉ። እንዲህ ያሉ የምርምር ጥረቶች በተለይ በተሐዋሲው ለተያዙ ሰዎች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም የሕክምናውን ረቂቅነት እና ውድነት ሲታሰብ ለምን ያህሉ ሕዝብ ይደርሳል የሚለው ማነጋገሩ እንደማይቀም ያስረዳሉ።

«እነዚህ የምርምር ነገሮች በጣም «እንትን» መደረግ አለባቸው፤ እንግዲህ ይሄ ሙከራ የተደረገው በሁለት ሰው ነው። ለሌላ ሰዎች ይሠራል ወይ የሚለው ግን ሁሉ ነገር መታየት አለበት።»

የምርምሩን ውጤት ይፋ ያደረጉት ሳይንቲስቶች ያገኙት ውጤት በአንድ በኩል ቢያስደስታቸውም ሙሉ ለሙሉ ግን ታማሚው ከኤችአይቪ ተሐዋሲ ፈፅሞ ድኗል ለማለት አሁን መቸኮል የለብንም እያሉ ነው።

Kind mit HIV-Medikamenten in Moskau
ምስል imago/ITAR-TASS/V. Prokofyev

የHIV AIDS ተሐዋሲ በወረርሽኝ መልክ መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ70 ሚሊየን የሚበልጡ  ሰዎች በተሐዋሲው ተይዘዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ገሚሱ ማለትም 35 ሚሊየን የሚሆኑት አልቀዋል። በአሁኑ ጊዜ 37 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ HIV ተሐዋሲ በደሙ ውስጥ እንደሚገኝ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ከነዚህ ውስጥ 1,8 ሚሊየኑ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው። ምንም እንኳን ካለፉት በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ወዲህ በተሐዋሲው አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ቢነገርም፤ የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው አሁንም በየዓመቱ 5 ሺህ ሰዎች በኤች አይቪ ተሐዋሲው ይያዛሉ። 

በጎርጎሪዮሳዊው 1988 ዓ,ም የመጀመሪያው የኤድስ ቀን ሲታሰብ ዓለም ስለበሽታው ያለው አመለካከት አሁን ካለው እጅግ የሚለይ ነበር። ስለኤችአይቪ የመተላለፊያ መንገዶችም ሆነ ስለበሽታው ምንነት ሰዎች በግልፅ ይናገራሉ፤ መረጃዎችም ይዳረሳሉ፤ በሽታውን ለማወቅ የሚደረገው ምርመራም ቢሆን ዛሬ በቀላሉ ይደረጋል፣ ከሕክምናው አኳያም ሲታይ የተለያዩ የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት አቅርቦቱ እያደር ተስፋፍቷል። ኢትዮጵያ ውስጥም ኅብረተሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱን ዶክተር አስቴር ይናገራሉ።

«የሰው ግንዛቤ አሁን ላይ የተሻለ ነው። ሁሉ ሰው ስለኤችአይቪ ሰምቷል በተለያዩ ነገሮች ሰምቷል። ከማንበብም፣ ከሚዲያዎችም፣ ከኢንተርኔትም የተሻሉ ነገሮች አሉ። እውቀቶቹ አላቸው። አሁን ላይ ሁሉም ግንዛቤ አለው። ግን ይሄንን አውቄያለሁ ብሎ አንድ ሰው ዛሬ ላይ ለኤችአይቪ መጋለጥ የለበትም።»

HIV Labor Screening Wissenschaft
ምስል picture-alliance/dpa/G. Bally

በአሁኑ ጊዜ ፀረ ኤችአ ይቪ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱ ይነገራል። እንደ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃም የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች በጎርጎሪዮሳዊው 2017ዓ,ም ቁጥራቸው 21,7 ሚሊየን ደርሷል። የተሐዋሲው ከነፍሰጡር እናት ወደ ልጅ የመተላለፍ መጠኑም እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ሰዎች ስለኤችአይቪ መተላለፊያ መንገዶች እና መከላከያ ስልቶች በተለያዩ መንገዶች መስማታቸው ቢታመንም ዛሬም ግን በሽታው በተለይ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሃገራት አሳሳቢ ከሆኑት የጤና ችግሮች ዋነኛው መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። አፍሪቃ ውስጥ ብቻ ተሐዋሲው በደማቸው የሚገኝ 23 ሚሊየን ሰዎች ናቸው።

በነገራችን ላይ በቅርቡ ሳይንቲስቶች ይፋ ያደረጉት የምርምር ውጤት እንደሚያመለክተው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች ተሐዋሲውን የመግደል ወይም ፈጽሞ ማጥፋት የሚችሉ አይደሉም። ዋናው ሥራቸው ተሐዋሲው በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች በየቀኑ የሦስት መድኃኒቶችን ድብልቅ የሚወስዱት ተሐዋሲው እራሱን ማባዛት ወይም ማራባት እንዳይችል ለማድረግ ነው። እናም ይህ መድኃኒቱን በጥንቃቄ መውሰድ ለሚችሉ ሰዎች አዎንታዊ ለውጥ ነው። በአእምሮ ጤና መታወክም ሆነ በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ምክንያት መድኃኒቱን በትክክል በየዕለቱ መውሰድ ለሚያስታጉሉ ታማሚዎች ደግሞ አዲስ ስልት ቀርቧል። ይኸውም በወር አንድ ጊዜ በመርፌ የሚሰጥ ሲሆን ተሐዋሲው ላይ ለረዥም ጊዜ ጫና ማሳደር የሚችል አንቲሪትሮቫይራል ህክምና በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ATLAS ብለውታል። በ16 ሃገራት ሙከራ ተደርጎም ውጤት አሳይቷል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ዶክተር አስቴር ሸዋማረን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ