1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜርክል ያጋጠማቸው ፈተና

ማክሰኞ፣ ጥር 17 2008

ሜርክል በጎርጎሮሳዊው 2015 ጀርመን በርካታ ስደተኞችን በማስገባትዋ ጥሩ ስም አትርፈዋል ። በሃገር ውስጥም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የህዝብ ፍቅር የሚቸራቸው መሪ ነበሩ ።አሁን ግን ተወዳጅነታቸው እየቀነሰ መምጣቱን ነው የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የሚያሳዩት ።

https://p.dw.com/p/1Hk2C
Angela Merkel im Regen Porträt Berlin Deutschland
ምስል Getty Images/S.Gallup

ሜርክል ያጋጠማቸው ፈተና

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስደተኞች በብዛት ወደ ጀርመን መግባት ከጀመሩበት ከዛሬ ስድስት ወር ወዲህ በሃገር ውስጥም ሆነ በአውሮፓ ደረጃ የሚገጥሟቸው ፈተናዎች እየጠነከሩ ሄደዋል። በተለይ ከእህት ፓርቲያቸው ከክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በኩል ጠንካራ ተቃውሞ እየተሰነዘረባቸው ሲሆን አቋማቸውን እንዲቀይሩም ግፊቱ በርትቷል ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በጀርመን የስደተኞች ቀውስ በሜርክል ላይ ያስከተለውን ጫናና መዘዙን ያስቃኘናል ።

በሦስተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ላይ የሚገኙት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በመራሂተ መንግሥትነት 10 አመት ፣በፓርቲያቸው በክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት CDU ሊቀ መንበርነት ደግሞ 15 ዓመታት ቆይተዋል ።በሥልጣን ዘመናቸው ፣በአመራር ስልታቸውና ባስገኟቸውም ውጤቶች ባለፈው አመት በግንቦት ወር ፎርብስ የተባለው መፅሄት ለ5 ተኛ ጊዜ በጣም ጠንካራዋ ሴት ፖለቲከኛ ሲላቸው ታይም የተባለው ታዋቂ መፅሄት ደግሞ የጎርጎሮሳዊው 2015 ታላቅ ሰው በማለት ሰይሟቸዋል። በርግጥም ሜርክል የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ቀውስ ውስጥ በወደቀበት ወቅት የሰከነ አመራር በመስጠት እንዲሁም ጀርመንም ያን ከባድ ወቅት ያለ አንዳች ችግር እንድትወጣ በማድረግ ይመሰገናሉ ። በጎርጎሮሳዊው 2015 ጀርመን በርካታ ስደተኞችን በማስገባትዋም ጥሩ ስም አትርፈዋል ። በሃገር ውስጥም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የህዝብ ፍቅር የሚቸራቸው መሪ ነበሩ ።አሁን ግን ይህ ተወዳጅነታቸው እየቀነሰ መምጣቱ ነው የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የሚያሳዩት ። ሂደቱን የሚከታተለው የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው የሜርክል ተወዳጅነት እየቀነሰ እንዲመጣ ያደረገው የሚያራምዱት የስደተኞች ፖለቲካ እና ያስገኘው ውጤት ነው ።

Winterklausur der CSU-Landtagsfraktion Horst Seehofer und Angela Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/P. Kneffel

ከ6 ወር በፊት ጀርመን ድንበሯን ለስደተኞች ስትከፍት ከጊዜ በኋላም ከዚህ ቀደም ከተገመተው በላይ ቁጥር ያለው ስደተኛ ሲገባ ፣እርምጃውን በቅጡ ያልታሰበበትና አቅምን ያላገናዘበ ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ፖለቲከኞች መቃወም ጀመሩ ። ከሁሉ የበረታው ግን በተለይ ስደተኞች በብዛት የሚገቡበት የደብብ ጀርመኑ የባየርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ የCSU ተቃውሞ ነው ። አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ማለትም የCDU እህት ፓርቲ CSU ፣ሊቀመንበር ና የባየርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ኾርስት ዜሆፈር ሜርክል ጀርመን ድንበሯን ለስደተኞች ክፍት እንድታደርግ የደረሱበትን ውሳኔ የተቃወሙት ገና ከመነሻው ነበር ።

«ይህ ስህተት ነበር ። ሊደገም የማይገባው ስህተት ።የስደተኞቹ ቁጥር እየጨመረ አሁን እንደሆነው ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል ።»

ሜርክል ግን ለእህት ፓርቲያቸውም ሆነ ለህዝቡ ደጋግመው የሚያስተላፉት መልእክት አንድ ነው ። «እንችላለን » የሚል።

«ጀርመን ጠንካራ ሃገር ናት ። ጉዳዩን በሚመለከት ልንከተለው የሚገባን አካሄድ ይህ ሊሆን ይገባል እስካሁን ብዙ ነገሮችን ማድረግ ችለናል ፤ ይህንንም ማድረግ እንችላለን ፤ እናደርገዋለንም መንገዳችንም ላይ መሰናክል ካጋጠመን መወጣት ይኖርብናል ። ይህ ነው መደረግ ያለበት»

ሜርክል ደጋግመው ማድረግ እንችላለን ቢሉም ፤ ያስመሰገናቸውና የዓመቱ ታላቅ ሰውም እስከ መባል ያደረሳቸው ስደተኞችን በብዛት ማስገባታቸው ፣በሃገር ውስጥም ሆነ በአውሮፓ ደረጃ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ ነው የከተታቸው።ጀርመን ባለፉት 6 ወራት 1.1 ሚሊዮን ስደተኞችን ማስገባቷ ብቻ ሳይሆን አሁንም በሯን ለስደተኞች ክፍት ማድረጓ አጠባቂኝ ውስጥ አስገብቷቸዋል ። በከባዱ ክረምት ምክንያት አሁን ወደ ጀርመን የሚመጣው ስደተኛ ቁጥር በመጠኑ ቀነሰ እንጂ አልቆመም ።በጎርጎሮሳውያኑ ጥር ብቻ ከ40 ሺህ በላይ ስደተኞች ጀርመን መግባታቸው ነው የተነገረው ። ችግሩን ይበልጥ ያወሳሰበበው ደግሞ በአውሮፓ ህብረት ደረጃ ለችግሩ ማቃለያ የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብም ተግባራዊ አለመሆኑ ነው ። የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ስደተኞችን ለመከፋፈል በተለያዩ ጊዜያት በውዴታም ሆነ በግፊት ቃል ቢገቡም በፍጥነት መተግበር ግን አልቻሉም ። ይህም ሜርክልን በሃገር ውስጥም ሆነ በአውሮፓ ደረጃ እንዲገለሉ አድርጓቸዋል ።በነዚህና በሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ሜርክል በስደተኞች ጉዳይ ላይ ከእህት ፓርቲያቸው ከCSU ጋር መግባባት አለመቻላቸው በርካታ መዘዞችን ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ይገመታል ። ሶስት ነገሮች ሊደርሱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል ይላል ይልማ።

Deutschland Flüchtlinge Flughafen Schönefeld Berlin
ምስል DW/K. K. Ferguson

የጀርመን ጎረቤቶችም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ስደተኞችን ቢቀበሉም የስደተኞቹ ምርጫ ጀርመንና ሌሎች ሃብታም የአውሮፓ ሃገራት መሆናቸው ችግሩን ይበልጥ እያወሳሰሰበ ነው ።

የስደተኞች ቀውስ በጀርመን ብሄረተኛ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ አድርጓል ። ። ችግሩ ሜርክል በሃገር ውስጥም ይሁን በአውሮፓ ደረጃ የከፋ ውዝግብ ውስጥ እንዲገቡ ከማድረግም በላይ መገለልንም አስከትሎባቸዋል ። ከፓርቲያቸው አባላት ሳይቀር የተቃውሞ ደብዳቤም እየተጻፈባቸው ነው CSUም ጫናውን አጠናክሯል ። ሜርክል አቋማቸውን እንዲቀይሩ እስከ መጋቢት ጊዜ ሰጥቷቸዋል ።የሜርክል ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ማወቅ ያዳግታል ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ