1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እና አዲሱ ቀውስ

ማክሰኞ፣ መስከረም 10 2009

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጋብ ብሎ የቆየው ውጊያ ሰሞኑን ማገርሸቱ ተነገረ። እንዳዲስ በመደራጀት ላይ ናቸው የሚባሉት የቀድሞዎቹ የሴሌካ ዓማፅያን ከጥቂት ቀናት በፊት በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ከፊል የሚገኘውን የካጋ ባንዶሮን አካባቢን እና ባቅራቢያው ያሉትን መንደሮች አጥቅተዋል።

https://p.dw.com/p/1K5UL
Zentralafrikanischen Republik Bangui - Schütze in Bunker
ምስል picture-alliance/AA/Stringer

[No title]

በዚሁ ጥቃታቸው ቢያንስ ስድስት ሰዎች ገድለዋል፣ ንብረት እና የቀንድ ከብቶች ዘርፎዋል፣ በርካቶችንም ከቀያቸው አፈናቅለዋል። ይህን ተከትሎ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ጦሩን በዚያ ያሰማራው የተመድ ተልዕኮ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሰሞኑን እንደገና የተቀሰቀሰው ግጭት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ጓዱን ማጠናከሩን ገልጾዋል።

የሀገሪቱ ፕሬዚደንታዊ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው፣ የቀድሞ የሴሌካ ተዋጊዎች በካጋ ባንዶሮ ከቤት ቤት እየገቡ ባካሄዱት ጥቃት የሞተው ሰው ቁጥር 26 ነው። የተመድ ተልዕኮ ግን ቁጥሩ ስድስት ብቻ መሆኑን ነው ያመለከተው። አካባቢው ከሴሌካ አፈንግጦ የወጣው እና ራሱን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ተሀድሶ ሕዝባዊ ግንባር ብሎ የሚጠራው ቡድን ጠናካራ ሰፈር ነው። የዚሁ ቡድን መሪ ኑረዲን አዳም እጎአ በ2013 እና 2014 ዓም በሀገሪቱ በተፈፀመው ግድያ ተጫውተውታል ለተባለው ሚና ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
የቀድሞ ሴሌካ ተዋጊዎች የሚያካሂዱት የግድያ እና ዝርፊያ ተግባር እና ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች የሚወስዱት አፀፋ ርምጃ የሀገሪቱን ቀውስ ይበልጡን እያባባሰ መሆኑን የማ አ ሬ አዋቂ እና መንበሩን ፓሪስ ያደረገው የፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተመራማሪ ቲየሪ ቨርኩሎ ታጣቂዎቹ ትጥቅ እስካልፈቱ ድረስ ውዝግቡ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
« ማዕከላዩ ችግር ያለው ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን የሚፈቱበትን እና በመደበኛው ኑሮ ውስጥ መልሰው የሚዋሀዱበትን መርሀግብር እንዲቀበሉ በማድረጉ ጥረት ላይ በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል እስካሁን አንድ ዓይነት ስምምነት መድረሱ ላይ ነው። በወቅቱ ሁለቱም ወገኖች ከዚሁ ገላጋይ ሀሳብ እጅግ ርቀው ነው የሚገኙት። »
ሚሊሺያዎቹ በመንግሥቱ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን እና በጦሩም ውስጥ ለመዋሀድ ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ ቢያጎሉም፣ ቨርኩሎን እንዳሉት፣ ሀሳቡ ችግር አዘል በመሆኑ ከመንግሥት በኩል ያን ያህል ተቀባይነትን አላገኘላቸውም።
« ይህ ዓይነቱ ስምምነት በርግጥ ጥሩ አይደለም። ነገር ግን ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የተመድ፣ በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል አንድ ገላጋይ ሀሳብ ላይ እንዲደረስ በመወትወት ላይ ናቸው። ምክንያቱም የተቀናቃኞቹ ታጣቂ ቡድኖችን የኃይል ርምጃ ማብቃት አልቻሉም። »
ታጣቂዎቹ ቡድኖች በፈፀሙት የኃይል ተግባር ቢያንስ 6,000 ሰዎችን በጭካኔ መግደላቸው በሀገሪቱ ነዋሪዎች አዕምሮ የማይጠፋ ጠባሳ መተዉን የመዲናይቱ ባንጊ ሊቃነ ጳጳሳት ዲየዶኔ ንሳፓላይንጋ ያስታውሳሉ።
« እኛ ያሳለፍነው በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ እንደሚችል ቦምብ በውስጣችን ተቀርጾ ቀርቶዋል። »
በወቅቱ የኃይሉ ተግባር ባልተለያት ማ አ ሬ ሕዝብ መካከል አንድ አምስተኛው፣ ማለትም ፣ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ አሁንም ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎዋል ወይም ወደሌላ ሀገር ተሰዶዋል። ሁለት ሚልዮን ተኩሉም በምግብ ርዳታ ላይ ጥገኛ ነው። የተመድ ተልዕኮ ስምሪት አንዳችም መረጋጋት ባላስገኘባት ማ አ ሬ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎቹ ቡድኖች በመንግሥቱ ላይ ግፊታቸውን ለማጠናከር ሲሉ አውሮጳዊው ዓመት 2016 ሳያበቃ በፊት በባንጊ ላይ አዲስ የጥቃት ዘመቻ ሊጀምሩ ይችሉ ይሆናል በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ያሉት ታዛቢዎች ይህ ለሀገሪቱ ሕዝብ ስቃይና መከራ ማብዛት ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ የሰላም ጥረትም ትልቅ ክሽፈት እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

Zentralafrikanischen Republik - Flüchtlingslager Benz-Vi
ምስል picture-alliance/dpa/J. Bätz
Zentralafrikanische Republik Menschen in der Hauptstadt Bangui UN Blauhelme
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Medichini

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ