1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ጥር 1 2009

ማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓትን በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ በ2002 ዓ/ም አዋጅ ወጥቶለትና መዋቅር ተዘጋጅቶለት ነበር። ግን ሥርዓቱ በገጠሙት አንዳንድ ችግሮች የተነሳ እስከአሁን ስራ ላይ አልዋለም።

https://p.dw.com/p/2VXBu
Äthiopien Frau stillt das unterernährte Kind
ምስል Reuters/E. Blair

The Defected Soc. Health Ins. of Ethiopia - MP3-Stereo

ምክንያቱንም ለማወቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጥቂት ጊዜ በፊት የተሾሙትን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን ሐሙስ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ምክር ቤቱ ጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቁ ይታወቃል።

ሥርዓቱ እስካሁን ተግባራዊ ያልሆነው «በቂ ቅድመ ዝግጅት ስላልተደረገለት፣ የሠራተኞች ግንዛቤ አናሳ ስለሆነና የመድኃኒት አቅርቦትና ከጤና ተቋማት አካባቢ እንከኖች ስላጋጠሙት» ነዉ ሲሉ ሚንስትሩ አስረድተው፣ ሥርዓቱ ምናልባት በሌላ ሊተካ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሌላዉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የሚባለዉ በገጠር ያሉት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ለመጥቀም የታሰበ ሲሆን በሙከራ ፕሮከክት ከ18 ሚልዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን በጤና ጥበቃ ሚንስቴር የህዝብ ግኑኙነትና የኮሙኒኬሼን ዳይሬክቴር አቶ አህሜድ ኢማኖ ይናገራሉ። ይህም መድን ከዚህ ዓመት ጀምሮ፣ አዋጅ ወጥቶለት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ስራ ላይ መዋል እንደሚጀመር ዳይሬክቴሩ ጠቅሰዋል።

በአገሪቱ ያሉት የመድን ድርጅቶች ለተወሰኑ ሰዎች የጤና መድን አገልግሎት ቢሰጡም ወደ 100 ሚሊዮን ህዝብ ያለበት አገር ዉስጥ የነሱ አገልግሎት ብዙም ትርጉም እንደሌለዉ የጤና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ይገረሙ አበበ ለዶቼ ቬሌ ገልጸዋል። ለዚህም መንግስት ሁለት አይነት መድኖችን ማለትም፣ ማኅበራዊ የጤና መድንና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ቢመሰርትም «መጨረሻ ላይ ሁለቱም ተዋህዶ አንድ አገራዊ መድን» እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር ይላሉ ደክተር ይገረሙ። የማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓት እስካሁን ስራ ላይ እንዳይዉል ያሰናከሉ ሌሎች ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ነው ዶክተር ይገረሙ ያስረዱት።

አገሪቱ በጤና ዘርፍ ፕሮግራሟን ለማስፈፀም በአብዛኛዉ የዉጭ ርዳታ ላይ ጥገኛ እንደሆነች እና ይህም በዚህ መልክ ሊቀጥል እንደማይችል የሚናገሩት ደክተር ይገረሙ ማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓትን ማስተዋወቅ በጣም ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።

 

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ