1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማህበራዊ መገናኛዎች ስለቡራዩ እና አካባቢው ጥቃት

ዓርብ፣ መስከረም 11 2011

ኢትዮጵያውን የአዲሱን ዓመት ሁለተኛ ሳምንት የጀመሩት በመርዶ ነው። ሳምንቱ በርካታ ወገኖቻቸው ዳግም በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሰሙበት ነበር። ለወትሮው እንዲህ አሳዛኝ ክስተት ሲሰማ በእውኑ ጥቁር ተለብሶ፣ ፍራሽ ተነጥፎ፣ ሀዘን እንደሚቀመጡት በማህበራዊ ድረ ገጾችም ተመሳሳይ አካሄዶች ይስተዋሉ ነበር።

https://p.dw.com/p/35JRL
Äthiopien Proteste in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

ማህበራዊ መገናኛዎች ስለቡራዩ እና አካባቢው ጥቃት

አሳዛን ክስተቶችን ተከትሎ ፕሮፋይል ፒክቸሮች ይቀየራሉ። የብዙዎች የፌስ ቡክና የትዊተር ግድግዳ በሻማ፣ በጥቁር ምስል እና በሟቾች ፎቶዎች ይሞላል። አንጀት የሚበሉ መልዕክቶች ይተላለፋሉ። እስከመቼ በዚህ አይነት ሁኔታ እንደሚቀጠል የሚጠይቀው ይበዛል። ጥቂቶች የመሰላቸውን፣ መፍትሄ ያሉትን ጽፈው ያስነብባሉ። 

አዲስ አበባ አጠገብ በቡራዩና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ቁጥራቸው እስካሁንም በትክክል የማይታወቅ ሰዎች ከሞቱ በኋላ የሆነው ግን ከወትሮው አካሄድ ያፈነገጠ ነው። የጥቃት፣ ሞቱ፣ የድረሱልን፣ መፈናቀሉ ዜና በመደበኛዎቹ መገናኛ ብዙሃን ከመነገሩ አስቀድሞ ተከታታይ መረጃዎች ይወጡባቸው በነበሩ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አይሎ ይታይ የነበረው ቁጣ፣ የመጠቃት ስሜት እና ስሜታዊነት ነበር። ጥቃቱን ለመቆጣጠር ዳተኝነት አሳይቷል በሚል በመጀመሪያ ብዙዎች የኮነኑት መንግስትን ነው። 

Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ጉዳዩ ብዙዎች ዘንድ በደረሰበት እሁድ ዕለት በፌስ ቡክ ገጻቸው ባስነበቡት ጽሁፍ “መንግስት እንደሀገር ሽማግሌ መምከር ሳይሆን፣ ህግ ማስከበር አለበት” ብለዋል።

“እየሆነ ያለው በፍጹም ከሰብአዊነት ውጭ ነው፡፡ ሰው እንኳን በወገኑ ላይ እንዲህ ያለውን ዘግናኝ ግፍ አይሰራም፡፡ ጅጅጋ፣ አዋሳ፣ ሻሸመኔ፣ ቡራዩ/ አሸዋ ሜዳ!  ግድያን፣ ዝርፊያን፣ የእናቶችንና እህቶችን መደፈር የእለት - ተእለት መዝገበ ቃላችን አካል እየሆነ እየለመድነው ነው፡፡ ያስፈራል፡፡ ህግ የሚያስፈልገው ደካሞችን ከጉልበተኞች፣ ሰላማዊ ዜጎችን ከግፈኞች ለመጠበቅ ነው፤ መንግስት የሚያስፈልገው ደግሞ ህግን ለማስፈጸም ነው፡፡ በየሰዉ ውስጥ ያለው የአውሬነት ባህርይ በመንግስት የህግ ልጓም ከግልቢያው መገታት አለበት፡፡ መፈክርና ምክር ለሰለጠነ ሰው ነው፡፡ በእያንዳንዱ የዜጎች ጥቃት ተጠያቂዎችን እና የተሰጠውን ፍትሀዊ ፍርድ መንግስት ለህዝቡ እስካልገለጸ ድረስ፣ በየጥቃቱ ማግስት የሚሰጥን ትርጉም የለሽ መግለጫ የግፉ አካል እስኪመስል ድረስ እየተደጋገመ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። 

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየታዩ ላሉ መሰል ጥቃቶች መንግስት እየሰጠ ያለው ምላሽ ካልስደሰታቸው መካከል በፌስ ቡክ ሸንቋጭ ጽሁፎቿ የምትታወቀው ህይወት እምሻው ትገኝበታለች። የአዲስ አበባ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከቡራዩ እና አካባቢው ጥቃቱን ሸሽተው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተጠለሉ ነዋሪዎችን መጎብኘታቸውን ተመልክታ “ምን ጉድ ነው?!” ስትል መገረሟን ገልጻለች። “የመንግስት ዋና ስራ ዜጎቹን መጠበቅ እንጂ ከሞት የተረፉትን መጎብኘት ነው እንዴ?!” ስትል የጠየቀችው ህይወት “የመንግስት ያለህ” ብላለች። 

ኦርቾ አራ የተሰኙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም የመንግስትን ህልውና አጠይቀዋል። “ህዝብ መንግስትን የሚመሰርትበት(የሚፈልግበት) የመጀመሪያዉ ምክንያት በህይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲያስከብርለት ነዉ። ሲቀጥለም ንብረት የማፍራትና የመያዝ መብቱ እንዲከበርለት ይፈልጋል። ይህን ማድረግ የማይችል መንግስት እንደሌሌለ ይቆጠራል። በዚህ ወቅት በተለያየ የሃገራችን ክፍል የሚታየዉን ህገ ወጥነትና የደቦ ጥቃት መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ ነዉ። ቆፍጠን ያለ አስተዳደራዊ እንዲሁም የፍትህ እና የፀጥታ እርምጃዎች መዉሰድ አለበት። ቅድሚያ መሰጠት ላለበት ቅድሚያ መስጠት የግድ ይላል” ብለዋል። ሲሳይ መንግስቴ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “የቡራዩ ነገር በእጅጉ ያስተዛዝባል” በሚል ርዕስ ባጋሩት አስተያየታቸው መንግስትን እና የጸጥታ ኃይሎችን ወቅሰዋል። “ዜጎች በወሮበሎች በግልጽ ሲገደሉ እና ንብረታቸው ተዘርፎና ተቃጥሎ ሲፈናቀሉ የፌዴራል ፖሊስም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ ነበር?” ሲሉ ጠይቀዋል። “የደህንነቱ መስሪያ ቤትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ሰዎችስ ለምንድነው የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ ያልወሰዱትና ድርጊቱ መፈጸም ሲጀምርም ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችል ስራ ፈጥነው በቦታው በመድረስ ጭምር ማከናወን ያልቻሉት?”ሲሉ በሁኔታው ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል።

Äthiopien Polizei
ምስል imago/Xinhua

መንግስት ላይ የበረታ የመሰለው ትችት ድርጊቱን ፈጽመዋል በሚል ጣት ወደተቀሰረባቸው የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮዎች) የዞረው ወዲያውኑ ነበር። በዚህ ስሜት ውስጥ ተሁኖ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ይባል፣ ይጻፍ የነበረው እስካሁንም ያላባራ ንትርክ፣ ስድድብ፣ ብሽሽቅ፣ አትንኩኝ ባይነት እና ዛቻን አስከትሏል። በኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ዘንድ ጎራ ለይቶ መወዛገብ የተለመደ ቢሆንም በዚህ ሳምንት የነበረው ግን መረር ብሎ ተስተውሏል። “የእኔ እውነት ብቻ ነው ትክክል” የሚሉት ወገኖች አገኘነው በሚሉት መረጃዎች ላይ ተመስርተው የሚወርውሯቸው አስተያየቶች ነገሮችን ይበልጥ ሲያጋግሉ ታይቷል።

የመንግስት እና የክልል ባለስልጣናት ድርጊቱ ብሔርንም ሆነ የወጣቶችን ስብስብ አይወክልም በሚል ይሰጧቸው የነበሩ መግለጫዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች ሲያጠያይቁ ነበር። እንዲህ አይነት አገላለጾችን ከተቹት ውስጥ ግዛው ለገሰ አንዱ ናቸው። ሰኞ ዕለት በፌስ ቡክ ገጻቸው ካወጡት ጽሁፍ ተከታዩን ቀንጭበናል። “ሻሸመኔ ላይ የሰው ልጅ ዘቅዝቀን የሰቀልነው እኛ ነን፤ ጅጅጋ ላይ ኢትዮጵያዊ ከነ ነፍሱ ያቃጠልነው እኛው ነን፤ ቡሬ ላይ ጨፍጭፈን የገደልነው እኛ ነን፤ ቡራዩ ላይ በቀውጢ ሁኔታ ውስጥ ሴት ለመድፈር [የተንደረደርን] እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ በጥቂቶች ማሳበቡን ትተን ያለንበትን የዘቀጠ የሥልጣኔ ደረጃ እንመን። የተደረገው ሁሉ በይፋ በታማኝ ሚዲያ ይዘርዘርና ሁላችንም የተደረገውን እንደዜጋ እናውግዝ፤ ያኔ ብቻ ነው ዛሬ የሆነውን ነገ የማንደግመው!

ገዳይም ሟችም እኛው ነን፤ ይሄ ነው የሥልጣኔ ደረጃችን፡፡ ኢቲቪ ላይ 'ገደሉ፣ አረዱ፣ ሚስትን ከባል ነጥለው ደፈሩ' ሲባል መስማት አስደንጋጭ ነው፡፡ ማን ናቸው? ‘የብሔር ግጭት ለማስነሳት በደንብ የተደራጁ ናቸው’ የሚለውም አይገባኝም! ከመንግስት በላይ አደረጃጀት ካላቸው፣ መንግስት የለም ማለት ነው፡፡ ቄሮን አይወክሉም ካልን፣ ቄሮም ቢሆን የረባ አደረጃጀት የለውም ማለት ነው፡፡

Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

በአንድ በኩል ብዙዎች በቄሮ ቢያሳብቡ ይፈረድባቸዋል? ከቄሮ በላይ ስልት እና ስትራቴጂ ያለው ቡድን ካለ ሕዝቡ በቄሮ እምነት ቢያጣ ይገርማል? ለዚህ ሁሉ መፍትሔው እገሌ እየተባሉ በስም እየተጠቀሱ ለፍርድ ሲቀርቡ ብቻ ነው? በሻሸመኔ ክስተት የተቀጣ ሰው አለ? በቡራዩ ለሆነው ግለሰቦች ተጠያቂ ለማድረግና አሳልፎ ለመስጠት ቄሮ ምን ሚና እየተጫወተ ነው? ታዲያ ሕዝቡ መንግስትንም ሆነ ቄሮን እንዴት ይመን? በመንግስትም ሆነ በቄሮ ጥረት እና የለውጥ ስኬት የኮራን ብዙዎች ነን፤ ታድያ ኩራታችንን እንዴት እናስቀጥል? እናም መንግስት በሁለት እግሩ ይቁም፤ እኛም እንደ ሕዝብ ለመሰልጠን እንጣር!” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል። 

ቅራኔዎችን በሰለጠነ አካሄድ ለመፍታት ሩቅ መሄድ እንደማያስፈልግ የጋሞ ሽማግሌዎች እና አባቶች ባለፈው ሰኞ በአርባ ምንጭ ከተማ ያደረጉት በምሳሌነት ደጋግሞ ሲወደስ ሰንብቷል። በቡራዩ እና አካባቢው በአብዛኛው ጥቃት የደረሰባቸው የጋሞ ተወላጆች በመሆናቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች ሀዘናቸውን ለመግለጽ እና ድርጊቱን ለመቃወም በዕለቱ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር። በጥቃቱ የተቆጡ የከተማይቱ ወጣቶች በአካባቢያቸው የተመለከቱትን የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እና የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ለማጥቃት ሲሞከሩ የተመለከቱ የጋሞ ሽማግሌዎች እና አባቶች ጣልቃ ይገባሉ። በጋሞ ባህል መሰረት እርጥብ ሳር በእጃቸው ጨብጠው ከወጣቶቹ ፊት በመንበርከክ የንብረት ውድመት እንዳይደርስ ተከላከሉ። በፎቶ እና ቪዲዮ የተደገፈውን የሽማግሌዎቹን ተማጽኖ ብዙዎች ተቀባብለውታል። 

በርካቶች በተመለከቱት ነገር ስሜታቸው እንደተነካ ገልጸዋል። ፎቶዎቹ እንዳስለቀሷቸው የጻፉም ነበሩ። ታደለች አበበ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “ብዙ የምንማርበት ኢትዮጵያዊነት፣ የሀገር ሽማግሌነትን በተግባር ያየንበት” በማለት ሲያሞካሹት ዘሪሁን ገመቹ ደግሞ የጋሞ ሽማግሌዎችን “የሀገር ዋልታ የሆኑ አባቶች” ሲል አድንቋቸዋል። ቤቲ አብርሃም በትዊተር “ይሄ ነው የሽማግሌ ወግ፣ ተዉ! አብረን እንኑር ነው የትልቅ ሰው ወግ” ስትል ጽፋለች።

አዲስ ቸኮል በፌስ ቡክ ገጹ “የሀገር ሽማግሌ፣ የሀይማኖት አባት፣ አባገዳ፣ ኡጋዝ የመንግሥት ቅኝትን እየተከተሉ በሚንቀሳቀሱበት እና በግጭት አፈታት የነበራቸውን ወሳኝ ታሪካዊ ሚና ወደ ዜሮ ባወረዱበት ዘመን ጋሞ ውስጥ ግን ሽማግሌዎች እንደባህላቸው ወጣቶችን ከጥፋት ጎዳና እየመለሷቸው ነው” ብሏል። ያዕቆብ በቀለ “እነዚህ ሰዎች ያደረጉትን አይተን መለወጥ ካልቻልን አገር አደጋ ላይ ትወድቃለች። በተለይ ተማርን የምንል። ክብር አርቀው አይተው እርምጃቸውን ለሚያስተካክሉ አገር ወዳድ ሰዎች” ሲሉ በዚያው በፌስ ቡክ ምስጋናቸውን አጋርተዋል። 

Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

ፌስ ቡክን በመሰሉ ማህበራዊ ድረ ገጾች በቀልን ከሚያስቀሩ ይህን መሰል እሴቶች እና እሳቤዎች ይልቅ የጥላቻ መልዕክቶች በርክተዋል ያሉ ስጋታቸውን ሲያስደምጡ ቆይተዋል። በአዲስ አበባ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በተጠራ ተቃውሞ አምስት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የተንቀሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን እንደ እፎይታ የወሰዱም ነበሩ። የኢንተርኔት አገልግሎቱ ከአንድ ቀን በኋላ ሲለቀቅ ባዩት ነገር ከተከፉት ውስጥ ዘውዳለም ታደሰ አንዱ ነው።  

“ፌስቡክ ላይ ለፍትህ የሚጮህ ብዙ ነው። በሃላፊነት ስሜት የሚጮህ ግን ጥቂት ነው። ፌስቡክ የቅዠት አለም ነው። የሰውን መንፈስ ያሸብራል። ነገሮች የሚጋነኑበት መጠን ልክ የለውም። ሃላፊነት የሚሰማው ሰው የለም። መንግስት እንደመንግስት፣ ህዝብ እንደህዝብ፣ ግለሰብም እንደግለሰብ ሃላፊነት እንዳለበት የገባው ሰው ጥቂት ነው። እቺን ሁለት ቀን ሰላም ነበርኩ። በዋይፋይ ፌስቡክ መጠቀም ብችልም አልፈለኩም ነበር። ከፋንታሲው አለም ወደምድር ወርጄ ሐገሬን በራሴ አይን ተመለከትኳት። ከጥቂት ድንጋጤ ከፈጠራቸው መዋከቦች ውጪ ሁሉም ሰላም ነው። 

ሐገሬ ከሞላ ጎደል ሰላም መሆኗን አይቼ ትንሽ ረፍት ቢጤ ይሰማኝ ሲጀምር ቴሌ ኢንተርኔቱን ለቀቀው። ፌስቡክ ሎግኢን ብዬ አምስት ደቂቃ ሳልቆይ ከሁለት ቀን በፊት የነበረው መጥፎ ስሜቴ ተመለሰ! ሰው ተግቶ ይሰዳደባል፣ ይጠላላል። ይራገማል። በብሔር ተቧድኖ ጥላቻን ይዘራል። ጠኋት በፌስቡክ ሲሰድበው የዋለው ልጅ ከሰአት በደምፍላት የአንዱን ብሔር ሰው ቢገድለው ያው ተሳዳቢ መልሶ ድርጊቱን ሊያወግዝ ይመጣል።

ሁላችንም ከአፋችን ስለምትወጣው እያንዳንዷ ቃል ጥንቃቄ የምናደርግበት ሰአት ነው። ኢትዮጵያ በኛ ዘመን አልተጀመረችም። በኛም ዘመን አታበቃም። ሐገራችን ከዚህ የባሱ እልፍ ችግሮችን አልፋ ነው ዛሬ እዚህ የደረሰችው። የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በእጁ ያለች የመሰለችው ሰው ካለ እሱ ሰነፍ ነው! ህዝብን ከህዝብ ማጫረስ፣ ማገዳደል፣ ማጣላት፣ ይቻል ይሆናል። ህዝብን ለዘመናት አብሮት ከኖረው፣ ከተጋባው፣ ከተዋለደው ህዝብ መነጠል ግን ፈፅሞ እንደማይቻል ለማሳየት ከሰሞኑ የኤርትራ ጉዳይ በላይ ምሳሌ ይኖረን ይሆን?” ሲል ጠይቋል። 

የዕለቱን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የምናጠቃልለው የኦሮሞ ፖለቲካ አራማጁ (አክቲቪስቱ) ገረሱ ቱፋ ትላንት ምሽት በፌስ ቡክ ባሰፈረው መልዕክት ይሆናል። “ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈናል።አሁን ያለንበትንም ሁኔታ እናልፋለን። ልክ አሁን ያለንበት አርማጌዶን ወይም የፍፃሜው ጦርነት አድርጎ ከዚህ በኋላ በምንም ነገር ላይ አብረን የማንሰራና በጋራ የማንኖር ይመስል የምንጠቃማቸው ቃላቶች ዘላቂ ቁስል የሚያኖሩ ሆነዋል። ይህ የመጨረሻ ችግራችን አይደለም። ይህ ሁሉ አልፎ ሁሉንም ነገሮች በተረጋጋ መንፈስ የምናይበት እና በሁሉም በኩል ያሉ ስህተቶችን የምናርምበት ዕድል ይመጣል።

ስለዚህ ሁላችንም ልክ የመጨረሻ ጦርነት እንደሚዋጉ ጠላቶች የመጨረሻውን አስቀያሚ ቃላት መለዋወጣችን ከመቋሰል ውጪ ምንም ጥቅም የለውም። ነገም እንዳለ መርሳት የለብንም። እነዚህ ነገሮች አልፈው አብረን እየሰራን አብረን መኖሩን እንቀጥላለን። ያኔ አሁን የተቋሰልነውን ለማከም ተጨማሪ ጉልበት እና ጥረት ራሳችን ላይ ከመጨመር ውጪ የሰሞኑ ነገራችን ትርፉ ማህበረሰባዊ በሽታ ነው” ሲል ገረሱ አስተያየቱን ደምሟድል። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ