1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙጋቤ ከገዢው ፓርቲ ሊቀ-መንበርነታቸው ተሻሩ

እሑድ፣ ኅዳር 10 2010

የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከገዢው ፓርቲ ሊቀ-መንበርነታቸው ተባረሩ። የዛኑ-ፒኤፍ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ ባካሔደው ስብሰባ ሙጋቤን ሽሮ ኤመርሰን ምንጋግዋን ሊቀ-መንበር አድርጎ መርጧል። የሮበርት ሙጋቤ ባለቤት ወ/ሮ ግሬስ ሙጋቤም ከፓርቲው ተባረዋል።

https://p.dw.com/p/2ntYH
Simbabwe Robert Mugabe hält Rede an der Uni
ምስል picture-alliance/dpa/AP/T. Mukwazhi

ማዕከላዊ ኮሚቴው ሮበርት ሙጋቤ እስከ ነገ እኩለ ቀን ድረስ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን እንዲለቁ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ዚምባብዌን ለ37 አመታት የመሩት ሙጋቤ የተባለውን ካላደረጉ በሕጋዊ መንገድ ከሥልጣናቸው የማውረድ ሒደት እንደሚጀመር ማዕከላዊ ኮሚቴው አክሎ ገልጧል። የጀርመን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው በቅርቡ ከምክትልነት ሥልጣናቸው የተባረሩት ኤመርሰን ምንጋግዋ የፕሬዝዳንትነት መንበረ ሥልጣኑን ከሙጋቤ ለመረከብ እጩ ሊሆኑ ይገባል ብሏል። የሮበርት ሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤ በበኩላቸው ጥላቻን እና መከፋፈልን ይሰብካሉ የማይገባቸውንም ሥልጣን ተመኝተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ቀዳማዊት እመቤቲቱ ከዛኑ-ፒኤፍ የሴቶች ክንፍ ኃላፊነታቸውም ተሽረዋል። ዛሬ የተላለፈው ውሳኔ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሔድ የፓርቲው ልዩ ጉባኤ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከጉባኤው በፊት የዚምባብዌ አርበኞች መሪ ክሪስ ሙትስቫንግዋ፦ ሙጋቤ ከመርፈዱ በፊት ዚምባብዌን ለቀው እንዲወጡ አሳስበው ነበር።  አሻፈረኝ ካሉ ግን በሙጋቤ ላይ ሕዝብ እንደሚያስነሱባቸው ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ