1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙጋቤ፡ አምባገነን መሪ ወይስ የነፃነት አርበኛ

እሑድ፣ የካቲት 16 2006

የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ትናንት ዘጠናኛ ዓመታቸውን አከበሩ። ምዕራቡ ዓለም ጨካኝ አምባገነን አድርጎ የሚመለከታቸው ሮበርት ሙጋቤ በአፍሪቃ ብዙ ደጋፊዎች አሉዋቸው። ይሁንና፡ ሙጋቤ አምባገነን ናቸወ የሚለውን አነጋገር በለንደን የሚታተመው ሳምንታዊ መጽሔት «ኒው አፍሪካ» ዋና አዘጋጅ ባፉር አንኮማ መሠረተ ቢስ ሲል አጣጥሎታል።

https://p.dw.com/p/1BDb4
Robert Mugabe
ምስል picture-alliance/AP Photo

« የምዕራባውያኑን መገናኛ ብዙኃን ስታነብ እኒህ ሰው የሀገራቸውን ሕዝብ ለቁርስ፣ ለምሳ እና ለራት የሚበሉ አውሬ የሆኑ ያህል ሊሰማህ ይችላል። ግን፣ ፊት ለፊት ቀርበህ ስታነጋግራቸው ሌላ ልዩ አቀራረብ ያላቸው ሰው ነው የምታገኘው። »

እንደ ባፉር አንኮማ ገለጻ፣ ፕሬዚደንት ሙጋቤ በጣም የሚያስገርመው መጠነ ሰፊ ስብዕና ያላቸው ግለሰብ ናቸው።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ፈፅመዋል በሚል የኤኮኖሚ ማዕቀብ ጥሎባቸው የነበሩትን የፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ እንደ ነፃነት አርበኛ የሚያደንቁት የጋና ዜጋ የሆነው ጋዜጠኛ ባፉር አንኮማ እና መጽሄታቸው እና « ኒው አፍሪካ » መጽሄት ብቻ አይደሉም። መጽሔቱ እአአ በ2004 ዓም አንባቢዎቹ ዋነኛ የሚሉዋቸውን 100 አፍሪቃውያንን እንዲመርጡ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ፕሬዚደንት ሙጋቤ ከሟቾቹ የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ እና የቀድሞው የጋና ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማህ ቀጥለው ሦስተኛውን ቦታ ይዘዋል። በዚህ አንፃር ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ትናንት 90 ኛ ዓመታቸውን ባከበሩበት ጊዜ ከምዕራቡ ዓለም ብዙም የደስታ መልዕክት አልደረሳቸውም። በ80 ኛዎቹ እና በ90 ኛዎቹ ዓመታት ግን ሁኔታው ሌላ ነበር። የምዕራባውያት ሀገራት ዚምባብዌ ነፃነቷን ከተጎናፀፈች እአአ ከ1980 ዓም ወዲህ በሥልጣን ላይ ካሉት ሙጋቤ ጋ ያኔ መልካሙ ግንኙነት ነበራቸው። እንዲያውም፣ የብሪታንያ ንግሥት ኤሊዛቤት ዳግማዊ ሙጋቤን ከፍተኛውን የንጉሣዊw ቤተሰብ የሚሰጠውን ማዕረግ እና የክብር የዶክትሬት ማዕረግ እንደሰጡዋቸው የሚታወስ ነው። ያኔ የዚምባብዌ ወታደሮች በ80ኛዎቹ ዓመታት ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ በዋነኛው ተቀናቃኛቸው ጆሹዋ ንኮሞ ደጋፊዎች ላይ ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ያዘዙበት ድርጊት ያኔ ምዕራባውያኑን አላሳሰበም ነበር። ምዕራቡ ዓለም ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን እንደ አምባገነን መሪ መመልከት የጀመረው ፣ እአአ በ2000 ዓም የነፃነት ታጋይ የነበሩ የዚምባብዌ ዜጎች በሀገሪቱ በጥቂት ነጮች እጅ የነበረውን ግዙፍ የእርሻ ቦታ በፕሬዚደንቱ ስምምነት በኃይል ከያዙ ወዲህ ነው።

Robert Mugabe und Queen Elizabeth Ritterschlag 1994
ምስል picture-alliance/photoshot

ይሁንና፣ የፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ መንግሥት አመራር ሰለባ የሆኑት ነጮች ብቻ አልነበሩም። እአአ በ2005 ዓም የዚምባባዌ መንግሥት በመዲናይቱ ሀራሬ እና በሌሎች የሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ተስፋፍተው በነበሩት ጎስቋላ ሠፈሮች በነበሩት ነዋሪዎች አንፃር በወሰደው የኃይል ርምጃ ከ50,000 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶችን ማፈራረሱ፣ 30,000 ሰው ማሰሩ እና ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብንም ካለ መጠለያ ማስቀረቱ አይዘነጋም። ያኔ ተቺዎች እንደገመቱት፣ መንግሥት ይህን ርምጃ የወሰደው በጎስቋሎቹ ሠፈሮች የሚኖረው ሕዝብ የመንግሥቱ ተቃዋሚ ቡድን ደጋፊ ሆኖ በመታየቱ ነው። በሀገሪቱ የሙያ ማህበራት እና የተቃውሞ ቡድን አባላት ይታሰሩ የነበሩበትም ድርጊት በምዕራቡ ዓለም አሉታዊ አስተያየት ነው ያሰከተለባቸው። ከዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ ድህነቱ ተስፋፍቶ ነበር። በዓለምም ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት ያላት ሀገር ነበረች። በ2008 ዓም በዚምባብዌ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ አገልግሎት ተንኮታኩቶ ስለነበረ ከ3000 የሚበልጥ ሰው ሕይወት አጥፍቷል።

Enteignung weißer Farmer in Simbabwe
ምስል AP

ይህም ቢሆን ግን፣ አፍሪቃ ውስጥ የሙጋቤ ዝና አሁንም እንደበፊቱ እንደገነነ ነው። የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ባለፈው ጥር ወር በአዲስ አበባ ባካሄዱት ጉባዔ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን የህብረቱ ወቅታዊ ምክትል ፕሬዚደንት አድርገው መርጠዋቸዋል። መሪዎቹ በዚሁ ጊዜ ግልጽ እንዳደረጉት፣ የአውሮጳ ህብረት በቅርቡ ከአፍሪቃ ሀገራት ጋ በብራስልስ ፣ ቤልጅየም ሊያደርገው ወዳቀደው ጉባዔ ሮበርት ሙጋቤን ካልጋበዘ፣ አፍሪቃውያኑ ከጉባዔው ይርቃሉ። የዛምቢያ ወጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋይልቡር ሲሙሳ በዚያን ወቅት ለአውሮጳ ህብረት ያስተላለፉት መልዕክት ዚምባብዌ ካልሳተፈች አፍሪቃም ወደ ብራስልስ አትሄድም የሚል ነበር።

ሙጋቤ በሚከተሉት ብልህ የፖለቲካ ሥልት እና ባላቸው መልካም ግንኙነት የተነሳ የሌሎች አፍሪቃውያን መሪዎች ድጋፍ አልተለያቸውም። ቀድሞ ሮዴዝያ ትባል በነበረችው ሀገራቸው በነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ አንፃር ባካሄዱት የነፃነት ትግል ወቅት በአህጉሩ ከነበሩ ሌሎች በርካታ የነፃነት ንቅናቄዎች ጋ ግንኙነት መመሥረታቸው የሚታወስ ነው። ሙጋቤ ለብዙ አሠርተ ዓመታት በደቡብ አፍሪቃ በውሁዳኑ ነጮች አገዛዝ አንፃር ከተገለው ከአፍሪቃውያኑ ብሔረተኞች እንቅስቃሴ፣ « ኤ ኤን ሲ » ጎን ቆመዋል። በነፃነቱ ትግል ወቅት ሙጋቤ ወደ ታንዛንያ እና ወደ ሞዛምቢክ ሸሽተው እንደነበር ይታወቃል። ዛሬ እነዚሁ አፍሪቃውያን የነፃነት የትግል ጓዶቻቸው ዛሬ የሀገር መሪዎች እና ፖለቲከኞች ሲሆኑ፣ ባላቸው መልካም ግንኙነት የተነሳ ሙጋቤን አሁንም ይደግፋሉ።

Joachim Chissano ehemaliger Präsident von Mosambik
ምስል OFW

« አስታውሳለሁ፣ ዴሞክራሲያዊ አመራር የተከተሉትን የቀድሞውን የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት ጆአኪም ቺሳኖን ኢዴሞክራሲያዊ ከሆኑት እና የሰብዓዊ መብትን ከማያከብሩ ሮበርት ሙጋቤን ከመሰሉ ጋ እንዴት ወዳጅ ሊሆኑ እንደቻሉ ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር፤ እና በጣም በመቆጣት ምን ዓይነት ሰው ነው አንድን ወዳጅ በችግሩ ጊዜ ጥሎት የሚሄድ ሲሉ ነበር የመለሱልኝ። »

ሙጋቤ በምዕራቡ አንፃር የሚሰጡት አስተያየትም ቢሆን በከፊሉ የአህጉሩ ሕዝብ ዘንድ ተቃባይነትን አግኝቶላቸዋል። ሙጋቤ አፍሪቃውያን መሬታቸውን እና የተፈጥሮ ሀብታቸውን በተመለከተ ለምዕራባውያን ተፅዕኖ ሳይንበረከኩ ራሳቸው መወሰን አለባቸው የሚሉበት አነጋገራቸው የአፍሪቃውያንን ስሜት የሚነካ ነው። ምክንያቱም፣ ይላል የ « ኒው አፍሪካ » መጽሔት ዋና አዘጋጅ ባፉር አንኮማ፣ በአፍሪቃ ቅኝ አገዛዝ ከበቃ ከአንድ ግማሽ ምዕተ ዓመት ከበለጠ ጊዜም በኋላ ድህነት እና ያልተስተካከለው ከተፈጥሮ ሀብት የሚገኘው ገቢ ክፍፍል ዛሬም በብዙ ሀገራት የሚታይ ትልቅ ችግር ነውና።

« ባለፉት 20 ዓመታት በሰሩት ፣ ማለትም፣ መሬታቸውን በቅኝ ገዢዎች ተነጥቀው ለነበሩት ሕጋዊ ባለቤቶቹ በመመለሳቸው ብዙ አፍሪቃውያን፣ በተለይ በደቡባዊ አፍሪቃ የሚገኙት ናሚቢያን የመሳሰሉ ሀገራት ሕዝቦች ያደንቁዋቸዋል። »

ብዙ ሀገራት በመሬት ጉዳይ ላይ ያን ያህል መሻሻል አላሳዩም። ለምሳሌ ናሚቢያ እአአ በ1990 በውሁዳኑ ነጮች ተገዛ ከነበረችው ደቡብ አፍሪቃ ነፃነቷን ባገኘችበት ጊዜ ወደ ግማሽ የሚጠጋው የሀገሪቱ የእርሻ መሬት ው,d 3,500 በሚጠጉ ነጮች ገበሬዎች እጅ ነበር። ። ጥቁሮቹ የናሚቢያ ዜጎች በጀርመናውያኑ እና በደቡብ አፍሪቃውያኑ ቅኝ አገዛዝ ዘመን መሬት የመያዝ ዕድል አልነበራቸውም። እርግጥ፣ ሀገሪቱ የመሬት ማደላደል ተሀድሶ መርሀግብር አስተዋውቃለች። ይሁንና፣ መርሀግብሩ አሳሪ ባለመሆኑ እስከዛሬ በጣም ጥቂት ነጮች ገበሬዎች ብቻ ናቸው መሬታቸውን ለሽያጭ ያቀረቡት። ሁኔታው በደቡብ አፍሪቃም ከዚህ የተለየ አይደለም። እርግጥ፣ የአፓርታይድ አገዛዝ ከተገረሠሠ በኋላ በስራ ላይ የዋለው የመሬት ማደላደል ተሀድሶ መርሀግብር በጣም አዝጋሚ ነው። ይህ ሲታሰብ ታድያ ፕሬዚደንት ሙጋቤ የሚከተሉት ፖሊሲ ለቀጣዮቹ ብዙዎችንን ሊያማልል ይችል ይሆናል።

ዳንኤል ፔልስ/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ