ሙርሲና የቀጠለው ተቃውሞ
ሰኞ፣ ኅዳር 17 2005ማስታወቂያ
የግብፁን ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲን ድንጋጌ በመቃውም በተካሄዱ ሰልፎች የተገደሉት 2 ግብፃውያን የቀብር ስነ ስርዓት በሺዎች የሚቆጠሩ ግብፃውያን በተገኙበት ዛሬ ተፈፀመ ። በስነ ስርዓቱ ላይ ከፊሉ ሲያነባ ከፊሉ ደግሞ የፍትህ ጥያቄ ሲቀርብ ተሰምቷል ። ዳማንሆር በተካሄደው በአንደኛው የቀብር ስርዓት ላይ የሞርሲ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ተጋጭተዋል ። ካለፈው ሳምንት አንስቶ በሞርሲ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በተካሄደው ግጭት 444 ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል ። በምርጫ የግብፅ ፕሬዝዳንት የሆኑት የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲው ሞሐመድ ሙርሲ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሥልጣናቸውና ውሳኔያቸው አንዳችም ህጋዊ ተቃውሞ ሊቀርብበት እንደማይችል ከደነገጉ በኋላ ነበር ህዝቡ ተቃውሞውን ማሰማት የጀመረው ። ፕሬዝዳንት በዚሁ ድንጋጌ ላይ ከሃገሪቱ ከፍተኛ ዳኞች ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ዘግይቶ በደረሰን ዜና መሰረት የግብፅ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንቱ ድንጋጌ እንዲሻር የቀረቡትን ክሶች በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመረምር አስታውቋል ። የግብፅ ዜና አግልግሎት ሜና እንደዘገበው ከ12 የሚበልጡ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበዋል ።
ሒሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ