1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውያን አቤቱታ በሱዳን

ረቡዕ፣ ሐምሌ 26 2009

ሱዳን ውስጥ የሚኖሩ በርካታ የኢትዮጵያ ስደተኞች ለመታወቂያ እድሳት የሚከፍሉት ገንዘብ መጨመሩ እንዳማረራቸው በተደጋጋሚ ለዶይቸ ቬለ ገልጸው ነበር። ኢትዮጵያውያኑ እንደሚሉት ከዋጋው መጨመር ባሻገር ያለአግባብ በፖሊስ እየተያዙ እና መታወቂያቸውን እየተቀሙ ይገኛሉ።ችግሩ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ደግሞ እንደ አዲስ ተነስቷል።

https://p.dw.com/p/2hXN0
Unterzeichnung des Nichtangriffpaktes zwischen Sudan und Südsudan
ምስል picture alliance/Maximilian Norz

በሱዳን የሚኖሩት የስደተኞቹ ቁጥር በውል አይታወቅም። አንዳንዶቹ በህጋዊ መንገድ ሱዳን ገብተው ቪዛቸው ሲቃጠል የኢትዮጵያ ፓስፖርታቸውን ደብቀው የስደተኛች መታወቂያ ያወጡ ናቸው፤ ሌሎች ከመጀመሪያውም በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ። ከተወሰኑ ወራት አንስቶ ግን ሁለቱም ከፍተኛ ስጋት ላይ ይገኛሉ። ይህ ለስደተኞች የሚሰጠው መታወቂያ ለአንድ ዓመት የአገልግሎት ጊዜ ያለው ሲሆን አይነቱም ይለያያል።ስደተኞቹ ከፍለው የሚያወጡት መታወቂያ እንዲሰሩ አይፈቅድላቸውም። ያነጋገርናቸው ስደተኞች እንደገለፁልን፤ እነሱ አሁን  በ2030 የሱዳን ፓውንድ ከፍለው የሚያወጡት መታወቂያ መወደዱ ብቻ ሳይሆን የሚያበሳጫቸው ከዛ ጋር በተያያዘ እየገጠማቸው ያለው እንግልት እና ዝርፊያ ነው።

ለሶስት ቀን ወህኒ ቤት ታስሮ እንደተፈታ የነገረን አንድ ስደተኛ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገረው የተጠየቀውን 5000 የከፈለው ጓደኞቹ አሰባስበውለት እንደሆነ ገልጾልናል። ገንዘብ የሌላቸው ደግሞ አሁንም አል-ሁዳ በተባለው እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። የኢትዮጵያውያኑ ስጋት ተቆጣጣሪ ነን ብለው መንገድ ላይ የሚያስቆሟቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። ሰሙኑን የወታደር ልብስ የለበሱ ሰዎች ወደቤታቸው እየገቡ እንደሚዘርፏቸው ነው ኢትዮጵያውያኑ የገለጹልን። ስማቸውን ያልነገሩን ስደተኛ እንደገለጹልን፤ ለተወሰነ ጊዜ ጋብ ብሎ የነበረው ቁጥጥር ሰሞኑን ደግሞ እንደ አዲስ ጀምሯል።
በሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያውያኑ ጥያቄ መፍትሄ እያፈላለገ እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ ገልጾ ነበር። ይሁንና ኤምባሲው የደረሰበትን ውጤት ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ወደ ኤምባሲው ያደረግነው የስልክ ጥሪ ምላሽ አጥቷል። እንዲሁ አብዛኞች የኢትዮጵያ ስደተኞች የታሰሩበት የአል-ሆዳ እስር ቤትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ  ቀርቷል። እስር ቤቱ በርካታ የሰብዓዊ ጥሰቶች ይካሂዱበታል በመባል ይተቻል። 

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ