1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦስትሪያና የወደፊቱ መንግሥትዋ 

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 7 2010

የመንግሥት መሪነትን ሥልጣን በመያዝ ከዓለም ወጣቱ መሪ የሚሆኑት የ31 ዓመቱ ኩርስ ፓርቲያቸውን የመሩት ለ5 ወራት ብቻ ነው። የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩርስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሸነፍ የበቁት ኦስትሪያ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ እወስዳለሁ ባሉት እርምጃ መሆኑ ይታመናል።

https://p.dw.com/p/2m2ID
Österreich Sebastian Kurz nach der Wahl in Wien
ምስል Reuters/D. Ebenbichler

ወደ ቀኝ ያዘማል የተባለው የኦስትሪያ መንግሥት


«ለናንተ አንድ ትልቅ ጥያቄ አለኝ። የዛሬዋን ቀን ለደስታ ተጠቀሙበት። ሁላችሁም ጠንክሮ በመስራት እና በቁርጠኝነት ነው ይህን ያገኛችሁት። በተመሳሳይ ጊዜ ነገ ሥራው እንደሚጀምር ልነግራችሁ ይገባል። የተወዳደርነው ምርጫውን ለማሸነፍ ብቻ አይደለም፤ኦስትሪያን ወደ ነበረችበት ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንጂ።»
ባለፈው እሁድ በተካሄደው የኦስትሪያ የምክር ቤት ምርጫ ያሸነፉት የወግ አጥባቂው የህዝባዊ ፓርቲ መሪ እና የወደፊቱ የኦስትሪያ መራሄ መንግሥት ዜባስትያን ኩርስ ለደጋፊዎቻቸው ካሰሙት ንግግር የተወሰደው ነበር። የመንግሥት ሥልጣን በመያዝ ከዓለም ወጣቱ መሪ የሚሆኑት የ31 ዓመቱ ኩርስ ፓርቲያቸውን የመሩት ለ5 ወራት ብቻ ነው። የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩርስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሸነፍ የበቁት ኦስትሪያ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ እወስዳለሁ ባሉት እርምጃ መሆኑ ይታመናል። ለአጭር ጊዜ የመሩትን ፓርቲያቸውን ለድል በማብቃት በደጋፊዎቻቸው ተወድሰዋል።«ውጤቱ በጣም ጥሩ ነው። ኩርስ መሪ መሆናቸው ያስደስታል። የተቀሩት እጩዎች አጭበርባሪዎች ናቸው።
በርሳቸው ድል ቅር የተሰኙም አልጠፉም።« እውነት ለመናገር ደንግጪያለሁ ተናድጄያለሁም። ከዚህ በላይ ማለት አልችልም። በጣም ቅር ተሰንቻለሁ። ይህ ትክክል አይደለም።
ካለፈው እሁድ የኦስትሪያ የምክር ቤት ምርጫ በኋላ በኦስትሪያ ሊመሰረት የሚችለው ጥምር መንግሥት እያነጋገረ ነው። አሁን ባለው ግምት እና አዝማሚያ በምርጫው 31.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ያሸነፈው ወግ አጥባቂው የመሀል ቀኙ የኦስትሪያ ህዝባዊ ፓርቲ ከቀኝ ጽንፈኛው «የነጻነት ፓርቲ» ጋር ተጣምሮ መንግሥት ሊመሰርት እንደሚችል ነው የሚነገረው። ፀረ ስደተና እና ፀረ እስልማና አቋም ያለው ቀኝ ጽንፈኛው የነጻነት ፓርቲ 26 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው። የመሀል ግራው የሶሻሊስቶች ፓርቲ ደግሞ በ26.9 በመቶ ድምጽ ሁለተኛውን ደረጃ ላይ ይገኛል። 62 መቀመጫዎችን ያሸነፈው«ህዝባዊ ፓርቲ»ም ሆነ 53 መቀመጫዎችን የያዘው የሶሻሊስቶቹ ፓርቲ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተጣምረው መንግሥት ለመመስረት  እንደማይፈልጉ ነው ያሳወቁት። በዚህ የተነሳም መሀል ቀኙ ህዝባዊ ፓርቲ ያለው አማራጭ ከቀኝ ጽንፈኛው የነጻነት ፓርቲ ጋር ተጣምሮ መንግሥት መመሥረት ብቻ እንደሚሆን ነው የሚገለጸው። ይህ ግን የተለያዩ ተጽእኖዎችን ሊያስከትል እንደሚችል እየተነገረ ነው። በተለይ ነባሩን የፖለቲካ አካሄድ ይዘው መቀጠል በሚፈልጉት ተሰሚነት ባላቸው የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ዘንድ  ዘንድ የሚኖራቸው ተቀባይነትም ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አልቀረም። ይህ ወደ ኋላ ላይ የምናነሳው ይሆናል። ከዚያ በፊት ግን የመሀል ቀኙ ህዝባዊ ፓርቲ እንዴት ለማሸነፍ በቃ ኩርስስ እንዴት ሊመረጡ ቻሉ? የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ አስተያያቱን ያጋራናል።
ኩርስ ህገ ወጥ ፍልሰትን ፈጽሞ የሚያስቆም ግልጽ እርምጃ  እንደሚወስዱ አሳውቀዋል። በህገ ወጥ መንገድ ለመግባት የሚሞክሩ ድንበር ላይ ሊታገዱ እና እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ሊመለሱ ይገባል የሚል አቋም ነው ያላቸው። ማን ኦስትርያ መግባት እንዳለበት ወሳኞቹ ህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች መሆን የለባቸውም ሲሉ ደጋግመው ይናገራሉ። ይህ የኩርስ አቋም  በአውሮጳ ህብረት የተለያዩ መርሆዎች ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ አይቀርም ይላል ገበያው።   
የተረጋጋ መንግሥት የመመስረት ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩት ኩርስ በስደተኞች ጉዳይ ላይ የያዙትን አቋም እንደማይለውጡ ሆኖም በአውሮጳ ህብረት ሌሎች አቋሞች ላይ ልዩነት እንደማይኖራቸው ተናግረዋል ። 

Grenze Österreich Italien - Flüchtlinge Brenner Bahnhof
ምስል picture-alliance/dpa/J. Groder
Österreichisch-deutsche Grenze Flüchtlinge
ምስል Reuters/M. Dalder
Österreich Sebastian Kurz mit Untersützern seiner Partei in Wien
ምስል Reuters/L. Foeger

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ