1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መረጋጋቱ የተነገረዉ የቻድ ወቅታዊ ሁኔታ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 6 1998

ሰሞኑን የተቀሰቀሰዉና ትናንት መባባሱ የተነገረዉ የቻድ ወቅታዊ ሁኔታ አሁን የተረጋጋ መምሰሉ ነዉ የተነገረዉ። በአንድ ወር ዉስጥ ይህ ሁለተኛዉ ሙከራ መሆኑ ነዉ ፕሬዝደንት ኢንድሪስ ዴቢን ከስልጣን ለማዉረድ።

https://p.dw.com/p/E0in
ቻድ የሚገኙት የሱዳን ስደተኞች
ቻድ የሚገኙት የሱዳን ስደተኞችምስል AP

ትናንት ማምሻዉንም ዋና ከተማዋን ንጃሚናን ለመያዝ የሞከረዉን የአማፂ ኃይል በቁጥጥር ስር ማድረግ መቻሉን ፕሬዝደንቱ በቴሌቪዥን ገልፀዋል። የከተማዋን ጎዳናዎች በአሁኑ ሰዓት የተባበሩት መንግስታት፣ የቻድና የፈረንሳይ ወታደሮች እየተቆጣጠሩት መሆኑን ነዉ።
ላለፉት ሶስት ቀናት ያህል አማፂያኑ ወደ ዋና ከተማዋ በመምጣት የፕሬዝደንት ዲቤን መንግስት ኃይል በሚፈታተን መልኩ ተዋግተዉ ሊቆጣጠሯት ሞክረዋል።
በመጨረሻም ትናንት ሁሉንም በቁጥጥር ስር ማድረግ መቻሉን ፕሬዝደንቱ ተናገሩ። አያይዘዉም
«ዋና ከተማዋን ንጋቱ ላይ ለመያዝ የሞከረዉ ኃይል ሙሉ ለሙሉ ተደምስሷል። በርካታ ተዋጊዎችና ሱዳን ያስታጠቀቻቸዉን መሳሪያም ማርከናል። ይህም ሱዳን በቻድ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ የግባቷ መረጃ እንዲሆን በመገናኛ ብዙሃን እናሳያለን። የካርቱም መንግስት አቅድ ባለዉ ሁኔታ የአካባቢዉን ሰላም ለማድፍረስ በተደጋጋሚ ሲፈፅመዉ የኖረ ጉዳይ ነዉ።»
ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ የዛሬ 10ዓመት በፈረንሳይ ድጋፍ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዝደንት ተብለዉ ሁለቴ ምርጫ በተካሄደዉ ምርጫ አሸንፈዋል።
ሆኖም የቀድሞዉ የጦር ኃይሉ አባልና መኮንን የነበሩት ዴቢ ሁኔታዎች ባይፈቅዱላቸዉም ለሶስተኛ ጊዜም በምርጫዉ ተሳትፈዉ ስልጣን ላይ ለመቆየት አልመዋል።
ይህን ደግሞ ነባሩ ህገመንግስታቸዉ አይፈቅድም። ይንን በመቃወም ነዉ በምስራቃዊት ቻድ በስፋት እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት የተባበረ ግንባር ለለዉጥ የተሰኘዉ አማፂ ቡድን የኃይል እርምጃዉን የጀመረዉ። የቡድኑ ቃል አቀባይ ከፈረንሳይ እንዲህ ይላሉ
«ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ ከንጃሚና እስኪባረሩ ድረስ ዉጊያችንን እንገፋበታለን። ከዚያም በአገሪቱ በተፋጠነ ሁኔታ የዲሞክራሲዉን ፍኖት በመከተል ነፃና ግልፅ ምርጫ የምታካሂድበትን አዎንታዊ ለዉጥ ይመጣል።»
አሁንም የወታደራዊ እንቅስቃሴዉ ጉዳይ ከበድ እንዳለ ነዉ። ምንም እንኳን ፕሬዝደንቱ አጠቃላይ ሁኔታዉ በቁጥጥር ስር ዉሏል ቢሉም የአይን ምስክሮች ግን የከባድ መሳሪያዎች ድምፅ መሰማቱ መቀጠሉን ተናግረዋል። አልፎ ተርፎም የአማጽያኑ ቃል አቀባይ ለድል መቃረባቸዉን አዉጀዋል!
«ወደፕሬዝደንቱ ቤተመንግስት እየተቃረብን ነዉ። ይህ ደግሞ ለፕሬዝደንት ዴቢ የመጨረሻዉ ሽንፈት ይሆናል። ዛሬዉኑ ሳይዉል ሳያድር ንጃሚና በእኛ ቁጥጥር ስር ትሆናለች።»
በሌላ በኩል የመንግስት ወታደሮች ዛሬ ጠዋት 285 ምርኮኞችንና የሞቱትን አማፅያን በከተማይቱ ብሄራዊ የጉባኤ አዳራሽ በማሳየት ድል የማግኘታቸዉ መረጃ አድርጋዉታል።
ከተማረኩት መካከል አንዳንዶቹም የሚያግዳቸዉ እንደሌለ ተነግሯቸዉ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ በመኪና ተጉዘዉ ቤተመንግሱን ሊቆጣጠሩ እንደመጡ ተናግረዋል።
የገጠማቸዉ ግን በታንክና በሄሊኮፕተር ከሚታገዘዉ የመንግስት ወታደራዊ ኃይል ጋር ከበድ ያለ ዉጊያ ሆነ።
የመከላከያ ሚንስትሩ ቢቻራ ኢሳ ጃዳላ በበኩላቸዉ ዛሬ ይፋ ያደረጉት በግጭቱ የ150 ሰዎች ህይወት ማለፉን ነዉ።
በዛሬዉ እለትም የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ታክሲዎችን ጨምሮ ስራ መጀመሩም ተነግሯል። የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታዉ ምክር ቤትም ግጭቱ እንዲቆም ጠይቋል።
በወር ለሁለት ጊዜ የተሞከረባቸዉን መፈንቅለ መንግስት ማክሸፍ መቻላቸዉን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ መኖሪያቸዉ በአራት ታንክ እየተጠበቀ ነዉ።
ስልጣናቸዉና ኃይላቸዉ ከድንበር ማዶ ዳርፉር በሰፈረዉና በካርቱም መንግስት ይደገፋል በሚሉት ዝቅ ተደርጎ መታየቱም አበሳጭቷቸዋል።
የቀድሞዉ የቻድ አማፂ ቡድን የበላይ የነበሩት ዴቢ የዛሬ 16ዓመት ሱዳን በነበረዉ ኃይላቸዉ አምባገኑ ሂሴኔ ሃብሬን አባረዉ ነዉ መንበሩን የያዙት።
ከስምንት ዓመት በኋላ ደግሞ በሰሜን በኩል የራሳቸዉ የመከላከያ ሚኒስትር የሚመሩት ዲሞክራሲና ፍትህ በቻድ የተባለዉ የአማፂ ቡድን የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ጀመረ።
ዴቢ ከራሳቸዉ የጦር ኃይል ጋርም ግንኙነታቸዉ ስጋትና ዉጥረት የነገሰበት ነዉ። ከሁለት ዓመት በፊት በጦሩ ዉስጥ ሙስናን ለመዋጋት አደረኩት ባሉት ጥረት ግድያ ተሞክሮባቸዋል።
ከቀናት በፊትም 70 የጦር መኮንኖቻቸዉን ከስራ ሲያባርሩ ተሰናባቾቹ ወደሱዳን ዳርፉር በመሄድ ከስልጣን ሊያወርዷቸዉ የሚሞክሩትን አማፅያን ተቀላቀሉ።
ኢንተርናሽናል ትራንስፓረንሲ የተሰኘዉ ድርጅት ባለፈዉ ዓመት ባወጣዉ መረጃ መሰረት በዓለም ግንባር ቀደምትነት በሙስና ከዘፈቁ ሀገራት መካከል ቻድ አንዷ መሆኗን ይፋ አድርጓል።