1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕዝበ ዉሳኔ በአብዬ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2006

ደቡብና ሰሜን ሱዳንን የምታወዛግበዉ የነዳጅ ሃብት ያላት ግዛት አብዬ ሕዝበ ዉሳኔ አካሂዳለች። ረዥም ጊዜ የተጠበቀዉ ይህ ታሪካዊ ህዝበ ዉሳኔ የግዛቷ ኗሪዎች የወደፊት እጣ ፈንታቸዉን ከሰሜን ወይም ከደቡብ ሱዳን ጋ እንመራለን ብለዉ እንዲመርጡ የሚያደር ይሆናል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1A7lC
ምስል picture alliance/AP Photo

ሁለቱም ሱዳኖች ምክንያታቸዉን ይፋ ባያደርጉም በሂደቱ ለመሳተፍ አልፈለጉም። ርምጃዉን ያልደገፉት የተመድም ሆነ የአፍሪቃ ኅብረት ተወካዮችም አልተገኙም።

Luka Biong
ምስል picture-alliance/dpa

አብዛኞቹ በግብርና የሚተዳደሩትና በደቡብ ሱዳን መንግስት የሚደገፉት የናጎክ ዲንካ ጎሳ አባላት አብዬ መገኛ ምድራቸዉ እንደሆነች ያምናሉ። ትስስራቸዉ ከኻርቱም መንግስት የሆነዉ በአርብቶ አደርነት የሚታወቁት የአረብ ሚስራይ ጎሳ አባላትም አብዬ የአያት የቅድመ አያቶቻችን ግዛት ናት ባይ ናቸዉ። አወዛጋቢዋ ግዛት አብዬ ይፋዊ ያልሆነ የተባለዉን ሕዝበ ዉሳኔ ካለፈዉ እሁድ ጀምራ እያካሄደች ነዉ። የአፍሪቃ ኅብረት «ለሰላም ጦስ ነዉ» ያለዉን ይህን ርምጃ የግዛቷ የሕዝበ ዉሳኔ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሉካ ቢዮንግ ሂደቱ የአብዬ ግዛት ሕዝብ ወደፊት ከየትኛዉ ወገን ለመሆን እንደሚሻ የገለጸበት እንጂ ሌላ ነገር የለዉም ይላሉ። የደቡብ ሱዳን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚንም እንዲሁ ያለ ጁባ ግፊትና ጣልቃ ገብነት ሕዝቡ የራሱን ዉሳኔ የሰጠበት መሆኑን ይናገራሉ፤

«አብዬ በየሆነዉ ጉዳይ ደቡብ ሱዳንን የሚመለከት አይደለም። ሲቪል ማኅበረሰቡ ነዉ። ያለ ደቡብ ሱዳን መንግስት ራሱ የአብዬ ህዝብ ነዉ ያደረገዉ። ስለዚህ የደቡብ ሱዳን መንግስት ለብቻዉ ህዝበ ዉሳኔዉን እንዳካሄደ ተደርጎ መወሰድ አይኖርበትም። ካለእኛ ተደርጓል ወደማን ይሄዳሉ የሚለዉን ዉጤቱ ይመራል።»

የአብዬ ግዛት ኗሪዎች ድምጽ ለመስጠት በርከት ብለዉ ነዉ የወጡት። ኻርቱምና ጁባ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2005ዓ,ም የሰላም ስምምነታቸዉን ናይሮቢ ኬንያ ላይ ከተፈራረሙ አንስቶ የዚህች ግዛት ይዞታ ጉዳይ ሲያነታርካቸዉ ቆይቷል። የአብዬ ሕዝበ ዉሳኔ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ማቦር ማዉት የግዛቷ ኗሪዎች ለተጓተተዉ ሕዝበ ዉሳኔ ድምጻቸዉን ለመስጠት ቆርጠዉ መዉጣታቸዉን ይገልጻሉ። ሕዝበ ዉሳኔዉም የኻርቱም አቋም ተፅዕኖ አያሳርፍበትም ባይ ናቸዉ፤

«የሱዳን መንግስት ቢስማማም ባይስማማም በዉሳኔ ህዝቡ መግፋት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ይህ ማንኛዉም ሰዉ ምንጊዜም ያለዉ መብት ነዉ።»

ለከብቶቻቸዉ የሳር ግጦሽ ከወዲያ ወዲህ በመመላለስ የሚኖሩት የሚስራይ አረብ ጎሳ አባላት ግን ሕዝበ ዉሳኔዉን አልተቀበሉትም። ዛካሪያ ዲንግ የደቡብ ሱዳን ተመራማሪ ናቸዉ፤ እናም ሕዝበ ዉሳኔዉ ለምን እንደተካሄደ ይገባኛል ይላሉ።

Gipfel zu Ölstreit zwischen Südsudan und Sudan
ምስል picture-alliance/dpa

«ማኅበረሰቡ ጉዳዩን ግልፅ አድርጓል። በእነሱ አስተያየትም ይህን ጉዳይ እነሱ እነሱ ብቻ ሊያደርጉት እንዲችሉ ሊፈቀድላቸዉ እንደሚገባ በግልጽ ተረድተዋል። የዘጠኙ ናጎክ ዲንካ የጎሳ መሪዎች ወገን ስለሆኑም በግልፅ እምቢተኝነታቸዉን ማሳየታቸዉ ነዉ።»

ናጎክ ዲንካ በአብዬ ግዛት ተደላድሎ የሚገኘዉ ዋናዉ ጎሳ ነዉ። ይህ በእንዲህ እንዳለም የሱዳን ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር የአብዬን እጣ ፈንታ ለመወሰን አብረዉ ለመሥራት የደቡብ ሱዳን አቻቸዉን ጠይቀዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ስለምርጫ ያሉት ነገር የለም። ይፋ ባልሆነዉ ሕዝበ ዉሳኔ ታዛቢዉን ያልላከዉ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ንኮሳንዛና ድላሚኒ ዙማ ሕገወጥ ያሉት ድምጽ አሰጣጥ ጉዳዩ ባልተቋጨዉ ግዛት መፈጸሙ ዳግም ጦርነት እንዳይጭር አስጠንቅቀዋል። ዙማ በተናጠል የተደረገዉ ሕዝበ ዉሳኔ ተቀባይነት የሌለዉና ኃላፊነት የጎደለዉ ተግባር ነዉ ሲሉም ተችተዋል። የተመድም ቀደም ብሎ በተናጠል የሚወሰድ ማንኛዉም ርምጃ ዉጥረት የሚያባብስና አካባቢዉን የሚያበጣብጥ፤ የሰሜንና የደቡብ ሱዳንን ሰላምም የሚያደፈርስ እንዳይሆን አስጠንቅቋል።

ጀምስ ሽማንዩላ/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ