1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕወሓት የአማራ አካባቢዎችን እንደተቆጣጠረ ነው

ሐሙስ፣ መጋቢት 29 2014

የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ በሚል «ግጭት ማቆማ» ያለው ውሳኔ ላይ ቢደርስም፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አሁንም ከትግራይ ክልል ውጪ ከያዛቸው ቦታዎች ባለመውጣቱ የርዳታ አቅርቦት ሥራ ላይ ችግር መፍጠሩ ተገለጠ።

https://p.dw.com/p/49cdh
Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

«ሕወሓት በዞኑ ከያዛቸው 4 ወረዳዎች አልወጣም»

የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ በሚል «ግጭት ማቆማ» ያለው ውሳኔ ላይ ቢደርስም፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አሁንም ከትግራይ ክልል ውጪ ከያዛቸው ቦታዎች ባለመውጣቱ የርዳታ አቅርቦት ሥራ ላይ ችግር መፍጠሩ ተገለጠ። ከተኩስ አቁሙ ውሳኔ በኋላ ሰብአዊ ርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ወደ መቀሌ ቢጓዙም፤ ሕወሓት ከአፋርና ከአማራ አካባቢዎች በኃይል ከያዛቸው አካባቢዎች እንዲወጣ የተቀመጠለትን ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ አላደረገም ሲሉ ባለሥልጣናት ከሰዋል። ይህ በመሆኑም በሕወሓት ቁጥጥር ስር በሚገኙ ስፍራዎች ያሉ ነዋሪዎችን ማገዝ እንዳልተቻለም አክለው ተናግረዋል። የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው ካልተመለሱና በሕወሓት ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎች ነፃ ካልወጡ በቀጣይ ዓመት በአካባቢዎቹ አሁን ካለው የባሰ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችልም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል። የባህር ዳር ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል። 

መንግስት በቅርቡ የ«ግጭት ማቆም» ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት ሕወሓትም በኃይል ከያዛቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች እንዲወጣ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡ ይታወሳል። በወቅቱ ለይቼ ቬለ (DW)አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪዎች «የግጭት ማቆም ውሳኔው በምግብ ለተጎዱ የትግራይ አካባቢዎች ርዳታ ለማድረስ መልካም ርምጃ ነው ቢሉትም የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ሕወሓት አይተገብረውም» ብለው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የተኩስ አቁም ርምጃ ተከትሎ የርዳታ እህል ወደ መቀሌ መድረስ መጀመሩ ሰሞሙን ተገልጧል። ይሁን እንጂ ሕወሓት የተቀመጠለትን ቅድመ ሁኔታ እስካሁን እንዳላማላ በአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ዞን አመልክቷል። የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታ ተረፈ ሕወሓት በዞኑ ከያዛቸው 4 ወረዳዎች አልወጣም እንዴያውም ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሕወሓት ቁጥጥር ስር ካሉ ወረዳዎች መካከል የፃግብጂ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ገብረኪዳን በበኩላቸው ሕወሓት ይልቁንም የአካባቢውን ነዋሪዎች በተኩስ ሲያስደነግጥና ያለቻቸውን ሲነጥቅ ነው የሚውል ነው ያሉት።

ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ለትግራይ የሚያደርጉትን ያህል ለዋግኽምራ ችግረኞች ተመሳሳይ ስሜት የላቸውም ሲሉም ይከሳሉ። በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአበርገሌ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ መኳንንቴ በበኩላቸው በህወሓት ቁጥጥር ስር ያሉ ነዋሪዎች በተለያዩ ችግሮች ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል።ችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ካላገኘ ቀጣይ ዓመት በአካባቢዎቹ የባሰ ቀውስ እንደሚፈጠር ኃላፊው አስጠንቅቀዋል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ጌታወይ ዘገዬ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አጭር ማብራሪያ ታጣቂው ኃይል የያዛቸውን አካባቢዎች አለቀቀም፣ ለመልቀቅም ዝግጁነት የለውም፣ በየቀኑም በርካታ ተፈናቃዮች በሕወሓት ስር ካሉ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ወደ ሰላማዊ ወረዳዎች እየመጡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ