1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ምስቅልቅል

ሰኞ፣ መጋቢት 30 2011

ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሐብታም፣ አረባዊት ሐገር የታጣቂዎች መፈንጫ፣የአሸባሪዎች መናኸሪያ፤ የወሮበሎች መፈልፈያ፤ የስደተኞች መታረጂያ፤የሠላማዊ ሰዎች መሰቃያ ስትሆን ለሊቢያ ሕዝብ ሠላም እና ዴሞክሲ ተዋጋን የሚሉት NATO ሊቢያ የለም። አሜሪካ የለችም።ብሪታንያ።ፈረንሳይ ሁሉም የሉም።

https://p.dw.com/p/3GTP6
Libyen Antonio Guterres und General Haftar
ምስል Reuters/Media office of the Libyan Army

ሊቢያ፣ ዛሬም ጦርነት

መስከረም 15 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ድርጅት (NATO)ጦር ሊቢያን እንዲወርር ካዘዙት ሁለቱ ጠቅላይ አዛዦች ቤንጋዚ-ምሥራቅ ሊቢያ ገቡ።«ፈረንሳይ አጋራችሁነች።እንደምትደግፋችሁም ልነግራችሁ እወዳለሁ።»የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኒካላይ ሳርኮዚ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቀጠሉ ዴቪድ ካሜሩን ቀጠሉ።«አምባገነኑን አስወግዳችሁ ነፃነትን በመምረጣችሁ፣ ከተማችሁ ለዓለም የድንቅ አስተሳብ መፍለቂያ አብነት ሆናለች።» ድል አድራጊዎቹ ቤንጋዚዎችን ባስፈነደቁ በወሩ የሲርቱ ጠንካራ ገዢ ሲርት አጠገብ ተደፉ።» ሊቢያ።ዛሬስ? ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ። 
                         
ኮሎኔል ኸሊፋ ቤልቃሲም ሐፍጣር እንደ ጦር አዛዥ ቻድ ዘምተዉ እንደጦር ምርኮኛ በአሜሪካኖች ጫናና ድጋፍ ከእስር ከተለቀቁበት ከ1987 ጀምሮ ሸማቂ አደራጅተዉ የቃዛፊን ሥርዓት ወግተዋል።ዛኢር፣ ኬንያ፣ ኋላ ሲአይኤ ጠቅላይ ፅሕፈት ቤት አጠገብ አንዴ ፎልስ ቸርች ሌላ ጊዜ ቪና (ሁለቱም ቨርጂኒያ) እኖሩ፣ አሜሪካዊ ሆነዉ በአሜሪካኖች ገንዘብ፣በአሜሪካኖች ስለላ፣ በአሜሪካኖች ዲፕሎማሲ እየተረዱ የቀድሞ ጓዳቸዉን ሥርዓት ለማስወገድ ብዙ ታግለዋል።
በተለይ መጋቢት 1996 ምሥራቃዊ ሊቢያ ዉስጥ ያቀጣጠሉት አመፅ ጋዛፊን ሲዖል፣ ሐፍጣርን ቤተ መንግስት የሚዶል መስሎ-የዋሽግተን፣ ቴል አቪቭ፣ የለንደን-ፓሪስ ደጋፊዎቻቸዉን አስፈንድቆ ነበር።ከሸፈ።በ2011 የሊቢያ ሕዝብ እንደ ጎረቤቶቹ ያነሳዉ አመፅ ሰበብ ሆኖ የፓሪስ፤ ለንደን፣ ዋሽግተን መሪዎች የዓለምን ምርጥ ጦር ሲያዘምቱ የቀድሞዉ ኮሎኔል የጄኔራል ማዕረግ ለጥፈዉ ቤንጋዚ ገቡ።
የፈረንሳይና የብሪታንያ መሪዎች የድል ብስራታቸዉን መስከረም 2015 ለቤንጋዚ ሕዝብ ሲያጋሩ፣ ጄኔራሉ እዚያዉ ቤንጋዚ አጠገብ  የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን የተበታተነ ጦር ለአማፂነት ያደራጁ ነበር።የቃዛፊ  ሥራዓት ፈርሶ፣ ጠንካራዉ ገዢ ተገድለዉ ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሐብታም፣ አረባዊት ሐገር የታጣቂዎች መፈንጫ፣የአሸባሪዎች መናኸሪያ፤ የወሮበሎች መፈልፈያ፤ የስደተኞች መታረጂያ፤የሠላማዊ ሰዎች መሰቃያ ስትሆን ለሊቢያ ሕዝብ ሠላም እና ዴሞክሲ ተዋጋን የሚሉት NATO ሊቢያ የለም። አሜሪካ የለችም።ብሪታንያ።ፈረንሳይ ሁሉም የሉም።
የቀድሞዉ የአሜሪካ ዲፕሎማት ጂም ጀትሪል እንደሚሉት የሊቢያ ሕዝብ ዛሬ የሚገደል-የሚግደለዉ፣ አፍሪቃዊ ስደተኛ  የሚቀላዉ፣ እንደባሪያ የሚሸጥ፣ እንደ ከብት የሚገረፍ፣የሚታጎረዉ የፓሪስ፣ለንደን፤ ዋሽግተን መሪዎች በዲሞክራሲ ስም ላይጨርሱ በጀመሩት ጦርነት ምክንያት ነዉ።«ይሕ ከዉጪ፣ ኃይል የተመላበት የሥርዓት ለዉጥ ሲደረግ የተፈጠረ ነዉ።ሊቢያ ዉስጥ በ2011 የተወሰደዉ እርምጃ ዉጤት ነዉ።ይሕ ሙሉ በሙሉ ዴቪድ ካሜሩን፤ ኒኮላይ ሳርኮዚ፤ ሒላሪ ክሊንተንና በርግጥ ባራክ ኦባማም በወሰዱት እርምጃ ማግስት የሆነ ነዉ።«ለሊቢያ ሕዝብ ዴሞክራሲ»-ያሉት ዘመቻ ዉጤት የጠቀመዉ ነገር የለም።(ይልቅዬ) ያተረፈዉ የዓመታት ኹከት፣ግድያ፤የርስበርስ ጦርነት ነዉ።ያሁኑም የዚያ ተቀጥላ ነዉ።»
እንዲያዉም የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይላት ጦር ጠመንጃ-መትረየስ ትሪፖሊ አጠገብ  እገጭ-እጓ ሲል ትናንት  ትሪፖሊ አጠገብ መርከብ ላይ ሠፍሮ የነበረዉ የአሜሪካ ጦር ከካባቢዉ  ዉልቅ አለ።ጄኔራሉ ግን ሊቢያን ከነዳጅ አፍላቂነት ወደ ወሮበሎች መፈልፈያነት፣ ከሐብት ማዕከልነት ወደ ስደተኞች መታረጂያ-መፈንጋየነት የተንከባለችበትን ጎዳና ይጠርጉ ነበር።7 ዓመት ከመንፈቅ።ዛሬም እዚያዉ ናቸዉ። እንደ ብዙ የጦር አበጋዞች ሐገራቸዉን ቁል ቁል በደፈቁ ቁጥር እሳቸዉ ሽቅብ ይሽቀነጠራሉ።አሁን ፊልድ ማርሻል ናቸዉ።ኸሊፋ ቤልቃሲም ሐፍጣር። 
ሻለቃ ሙዓመር ቃዛፊ በ1969 የንጉስ ኢድርሲን መንግስት አስወግደዉ የመሪነቱን ሥልጣን የያዙት በያኔዉ የግብፅ መሪ በኮሎኔል ገማል አብድናስር እርምጃና አስተምሕሮ ተማርከዉ፣ ተነቃቅተዉም ነበር።በ2011 የሊቢያ ሕዝብ በኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ አገዛዝ ላይ ያመፀዉ ከቱኒዚያ ይልቅ የግብፅ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ገዢዉን የፊልድ ማርሻል ሆስኒ ሙባረክ አገዛዝን በአደባባይ ሠልፍ ማስወገዱን ካየ በኋላ ነዉ።
ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ ለፊልድ ማርሻል ሐፍጣር አብነት (ሞዴል) መሆን አለመሆናቸዉን በርግጥ አናዉቅም።ብዙዎች እንደሚስማሙበት የግብፅ ሕዝብን አብዮት ቀልብሰዉ፣ በግብፅ ሕዝብ የተመረጡትን መሪ በኃይል አስወግደዉ፤ የግብፅ ሕዝብን በብረት ጡጫ የሚገዙት አል ሲሲ የሐፍጣር ሙሉ ደጋፊ፣ አስታጣቂ፣ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚንቆረቆረዉን ገንዘብና ጦር መሳሪያም ለሐፍጣር ጦር አስተላላፊ መሆናቸዉ ግን እርግጥ ነዉ።
አል ሲሲ በፋንታቸዉ በምዕራባዉያን በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ መደጋፋቸዉም ገሐድ ነዉ።በአልሲሲ በተዘዋዋሪ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉት የ75 ዓመቱ አዛዉንት የሊቢያ ብሔራዊ  ጦር (LNA በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ያሉትን ኃይል ተጠቅመዉ እንደ አልሲሲ ቤተ-መንግሥት ለመግባት ከዚሕ ቀደም በተደጋጋሚ ሞክረዉ ነበር።ሙከራቸዉ መንበሩን ቶብሩክ ካደረገዉ የሊቢያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ከተባለዉ መንግስት አከል ስብሰብ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነት ሥልጣን አትርፎላቸዋል።
የተባበሩት  መንግስታት ድርጅት የሊቢያ ብሔራዊ የስምምነት መንግስት ያለዉ ቡድን የትሪፖሊን ቤተ-መንግስት ሲቆጣጠር ሐፍጣር ወደ ቤተ-መንግስቱ የሚያስጠጋቸዉን ሥልጣን በተለይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦርነቱን  ሹመት ለመያዝ ሳይከጅሉ አልቀረም።የፕሬዝደንታዊ ምክር ቤት የተባለዉ የብሔራዊ ስምምነቱ መንግስት ሥራ-አስፈፃሚ ሊቀመንበር ፈይዝ ሳራጅ ትናንት እንዳሉት መንግስታቸዉ ሐፍጣርን ጨምሮ ከተለያዩ የሊቢያ አንጃዎች ጋር ራግማ፣ፓሪስ፣ ፓሌርሞና አቡዳቢ ላይ ያደረገዉ ዉይይት ለስምምነት አልበቃም።በሌላ አባባል የፊልድ ማርሻል ሐፍጣርን ፍላጎት አላረከም።እና «ንሳ» አሉ ጦራቸዉን።ትሪፖሊን ያዝ።
«ትሪፖሊ አጠገብ በሁሉም አቅጣጫ የሠፈርከዉ ጦራችን ሆይ፤ ዛሬ በፈጣሪ ፍቃድ የድል ጉዛችንን የምናጠናቅቅበት ጊዜ ነዉ።የትግልና የዉጊያ ጉዞችንን።ዛሬ ቃል በገባነዉ መሠረት ተስፋዉ እየተሟጠጠ የመጣዉ የዉዷ ከተማችን ተወዳጅ ሕዝባችን ላደረገልን ጥሪ መልስ የምንሰጥበት ወቅት ነዉ።ዛሬ ለእዉነት ለተደረገልን ጥሪ መልስ የምንሰጥበት ቀን ነዉ።»
ትሪፖሊን ለመያዝ የገሰገሰዉ ጦር ርዕሠ ከተማይቱ አጠገብ የምትገኘዉን ሡቀልአሕመር የተባለችዉን አነስተኛ ከተማ ባለፈዉ ቅዳሜ ተቆጣጥሯል።የትሪፖሊን አዉሮፕላን ማረፊያ ለመያዝና ላለማስያዝ የሚደረገዉ ዉጊያ ግን ላጭር ጊዜ ጋብ ብሏል።የተፋላሚ ኃይላትን መሪዎች ያነጋገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ግን ተኩስ አቁሙ እንዲፀና ከመጠየቅ እኩል ሥጋታቸዉንም አልሸሸጉም።«ከትሪፖሊና አካባቢዋ ደም አፋሳሽ ግጭትን ማስወገድ አሁንም ይቻላል የሚል ተስፋ አለኝ።በሊቢያ የተለያዩ ወገኞችን የሚያስተባብር ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማግኘት በሚደረገዉ ጥረት ለመሳተፍ የተባበሩት መንግስታት ድጅት ምንግዜም ዝግጁ ነዉ»
የአዉሮጳ ሕብረት፣የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትና ኃያላን መንግስታትም ተፋላሚዎች ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመለሱ እየተማፀኑ ነዉ።እስካሁን ግን ሰሚ እንጂ ተቀባይ አላገኙም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እዉቅና አለዉ የሚባለዉ መንግስትም እንኳን ለድርድር ዝግጁነቱን በይፋ አላስታወቀም።የስብስቡ  መሪ ፋይዝ ሳራጅ ጀርባችንን ለመዉጋት የተሰነዘርብንን «ጩቤ» ቀለብስነዉ ይላሉ።
«የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊን በምናስተናግድበት ወቅት የሊቢያ ሕዝብ መልካም ዜና ይጠብቅ ነበር።ይሁንና ጀርባችን ለመዉጋት ሴራ ተሸረበብን። የተቃጣብንን ሴራ አከሸፍን።ከሐፍጣር በተነገረዉ የጦርነት መልዕክት የታጀበዉን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስናይ በጣም ነዉ የተገርምነዉ።የሐፍጣር ቃላት የአምባገነኑን እና የፈላጭ ቆራጩን ዘመን የሚያስታዉሱ ናቸዉ።ሐፍጣር ድል እናደርጋለን፣ ከተማችንን ከአሸባሪዎችና ከወንጀለኞች ነፃ እናወጣለን እያሉ ነዉ።»
የእግረኛዉ ዉጊያ ዛሬ ጋብ ብሎ መዋሉ ተዘግቧል።ሳራጅ የሚመሩት መንግሥት የጦር ጄቶች ግን ሚስራታ አካባቢ የሠፈረዉን የሐፍጣርን ጦር ይዞታ መደብደቡን የሐፍጣር ጦር አዛዦች አስታዉቀዋል።አብዛኛዉን ምስራቃዊና ደቡባዊ ሊቢያን የሚቆጣጠሩት ፊልድ ማርሻል ሐፍጣር የትሪፖሊን ቤተ-መንግስት ካልተቆጣጠሩ እንዳማያርፉ ረዳቶቻቸዉ እየተናገሩ ነዉ።ዓለም አቀፍ የፖሊሲ ጥናት የተሰኘዉ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ካምራን ቡኻሪ እንደሚሉት ሐፍጣር እንደማንኛዉም የሚሊሺያ አዛዥ መታየት፣ ሌላዉ ቀርቶ ከትሪፖሊ መንግስት መሪዎች እኩል መቆጠሩን አይፈልጉትም።ምክንያትም አላቸዉ።
«ሁሉም ለሥልጣን የሚሻኮቱ በደርዘን የሚቆጠሩ ሚሊሺያዎች በየስፍራዉ ባሉበት ሐገር፣ጄኔራል ሐፍጣር ልዩ ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል።ይሕ ጥሩ እድል ፈጥሮላቸዋል።በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ከአካባቢዉ ሐገራትም፣ከምዕራባዉያንም ከተወሰኑ ወገኖች ተቀባይነትና ክብር አግኝተዋል።ስለዚሕ ይሕን በመጠቀም እኔ ከሌሎቹ የሚሊሺያ መሪዎች እኩል አይደለሁም እንዲሉ አድርጓቸዋል።ሌላዉ ቀርቶ ዓለም አቀፍ እዉቅና ካገኘዉ መንግሥት መሪዎች እኩል እንኳን መታየት አይፈልጉም።»
ከፍ ማለት ነዉ ዓላማ ፍላጎታቸዉ።በ1969ኙ መፈንቅለ መንግስት እንደ አብዛኛዉ የሊቢያ ወጣት የጦር መኮንን የቃዛፊን እርምጃ አድናቂ፣ ደጋፊ ተባባሪም ነበሩ።በ1986 በኮሎኔል ማዕረግ ቻድን የወረረዉ ጦር አዛዥ ሆነዉ ዘመቱ።ከ300 መቶ መኮንኖች ጋር ተማረኩ።ቃዛፊን ከዱ።ካሜሪካኖች ተወዳጁ።አሜሪካ «ሲንደላቀቁ» ኖረዉ፣ የሊቢያ ወጣት ሕይወቱን የገበረለት ሕዝባዊ አብዮት ቃዛፊን ሲያሽቀነጥር የጄኔራልነት ማዕረግ ለጥፈዉ ቤንጋዚ ገቡ።ሊቢያ እየተበጣጠሰች ቁልቁል ስትዘቅት ሰዉዬዉ ሽቅብ ተንቻረሩ።ግን አልበቃቸዉም።ከዚያ በላይ ይሻሉ።የት ይቆሙ ይሆን? ቸር ያሰማን !

Libyen: Kämpfer der LNA
ምስል Getty Images/AFP/A. Doma
Libyen Bewaffnete Gruppen aus Misrata ziehen um, um Tripoli zu verteidigen
ምስል Reuters/I. Zitouny
Libyen Mohamed Ghnouno GNA-Sprecher
ምስል Reuters/H. Amara

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ