1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐቅን ፍለጋ

ዓርብ፣ ጥር 26 2009

ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ በፌስቡክ በየቀኑ ባለመታከት ይጽፋል። የጽሑፎቹ ዋነኛ ማጠንጠኛዎች በመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ የተጣረሱ ጽሑፎችን እየተከታተሉ እና እያነፃፀሩ መንቀስ ብሎም ማጋለጥ ነው። ለበርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ ደግሞ ለፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች እንግዳ አይደለም። ሙሉ ስሙ እሸቱ ሆማ ቀኖ ይባላል። 

https://p.dw.com/p/2Wt86
Screenshot Eshetu Homa Keno Facebook
ምስል Facebook/Eshetu Homa Keno

ሐቅን ፍለጋ

በዋናነት ትኩረቱ የመንግሥት ተቋማት ተደጋጋሚ ኅጸጾችን እና ግድፈቶችን እየተከታተለ  ማጋለጥ ነው። በምዕራቡ ዓለም እንዲህ አይነቱን ተግባር ባለሞያዎች በተደራጀ መልኩ የሚከታተሉት ሲሆን፤ ሐቅን ማጣራት (fact checking) ይሉታል።  ብዙውን ጊዜ መገናኛ ዘዴዎች ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች ይዘወተራል። እሸቱ ግን በሞያው ጋዜጠኛ አይደለም። የተጣረሱ ጽሑፎችን እየተከታተለ የሚያጋልጠውም በግሉ ከሥራው ጥቂት ፋታ ሲያገኝ ነው። አጠር ያሉ ሐረጋት እና አረፍተ ነገሮችን በመጠቀም በቀን ውስጥ ተደጋጋሚ መልእክቶችን በጽሑፍ ሲያወጣ አይታክተውም። የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በተለይ እርስ በእርስ የሚጋጩ የመንግሥት ተቋማት መልእክቶችን በሚያጋልጡት የፌስቡክ ጽሑፎቹ ያውቁታል። እሸቱ ሆማ ቀኖ። 

ለበርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ ደግሞ ለፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች እንግዳ አይደለም። እጥር ምጥን ብለው የሚቀርቡት ሸንቋጭ ጽሑፎቹን በጉጉት የሚጠባበቁ ተከታታዮቹም ብዙ ናቸው። ምንም እንኳን በሞያው የሕግ ሰው ቢሆንም፤ በጽሑፎቹ የምርመራ ጋዜጠኛ የሚሉት ጥቂት አይደሉም። እሸቱ ሆማ ቀኖ ዕለት በዕለት ከሚያቀርባቸው ጽሑፎቹ የተጣረሱ መልእክቶችን ለማጋለጥ ምን ያህል እንደሚታትር አመላካች ናቸው። 

ሩቅ ሳንሄድ እሸቱ ትናንት በፌስቡክ ገጹ ካሰፈራቸው ጽሑፎቹ ማለዳ ላይ ያቀረበውን አጠር ያለ ጽሑፉን መመልከት በቂ ነው። የኢህአዴግ ጽ/ቤት በፌስ ቡክ ገጹ «ከአንዳንድ የበለጸጉ ሃገራት በተሻለ ሥራ አጥነትን ችግር» ተቋቁሞ በ«ህዳሴ ወደፊት መገስገስ» መቀጠሉን የገለጠበትን አጠር ያለ ጽሑፍ እሸቱ በተመሳሳይ አጠር ያለ ጽሑፍ ሆኖም ጥልቅ በሆነ መልኩ ይተቻል። እንዲህ በማለት፦

Symbolbild Justitia Justizia
ምስል picture-alliance/dpa

«በኢህአዴግ በኩል የሚደረጉትን እንደዚህ አይነት በጣም የተጋነኑ ፕሮፓጋንዳዎችን ምን ያህል ኃላፊነት በጎደለው መልኩ እንደሚጽፉ ለማሳየት ሞክሬ ነው እዛ ላይ ያቺን ትንሽዬ ሐሳብ የገለጥኩት። በጣም ያሳዘነኝ ክፍል 5.9 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ሰአት የምግብ እጥረት ችግር ውስጥ ሆኖ፤ መንግሥት ራሱ ከደጋፊዎቹ (donors) ጋር ሆኖ ርዱኝ ሲል መግለጫ ከሰጠ ሳምንት እንኳን አይሞላውም። እና በዚህ በኩል ረሐብን ታሪክ አድርጌዋለሁ፣ ተቋቁሜዋለሁ እያልክ እያወራህ፤ በዛ በኩል ትልቅ ርዳታ ያስፈልገኛል  እያልክ ስትጮኽ ሁለቱን ለማነፃፀር ስለፈለግሁ ነው። አሁን እዚህ አሜሪካ ሰሞኑን ሰምተህ እንደሆነ  አማራጭ ሐቆች (alternative facts) የሚባል ነገር አለ። ከ[ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ]ትራምፕ መምጣት በኋላ እየተወራ ያለ ነገር ነው። ማለት እውነተኛው ጉዳይ እዛ አለ፤ ሌላ እንደ ተጨማሪ እውነት [ብለህ] ደግሞ እዚህ  እየመጣህ ማወናበድ አይነት ነገር  ስለመሰለኝ ነው ያቺን ትንሽዬ ነገር የጻፍኩት።»

በእርግጥም እሸቱ በሚኖርበት አሜሪካን ሀገር «ሐቅ» እና «አማራጭ» የሚሉ ሁለት ቃላት የማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ የሰሞኑ ሰፊ መነጋገሪያ ሆነዋል። መነጋገሪያ የሆኑትም የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አማካሪ ኬሊያነ ኮንዌይ NBC የተሠኘው ማሰራጪያ ጣቢያ ቀርበው ቃለ-ምልልስ ከሰጡ በኋላ ነበር። ኬሊያነ በቃለምልልሱ ወቅት የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ሾን ስፓይሰር በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በዓለ-ሲመት ወቅት የነበረውን ታዳሚ ቁጥር አግንነው መናገራቸውን ሊያስተባብሉ ይሞክራሉ። ጠያቂ ጋዜጠኛውን እንዲህ በማለት፦ «አንተ ሐሰት ነው ትላለህ፤ ቃል አቀባያችን ሾን ስፓይሰር ለዚያ አማራጭ ሐቅን ሰጥቷል» ጠያቂ ጋዜጠኛውም ዋዛ አይደለም፦ «አዩ፤ አማራጭ ሐቅ በእርግጥም ሐቅ አይደለም። ቅጥፈት እንጂ» ይላቸዋል። እናም ከአንድ ሐቅ ውጪ «አማራጭ ሐቅ» የሚባል ነገር እንደሌለ፤ የቃላት ማጭበርበር እንደሆነ ጋዜጠኛ ቹክ ቶድ ለመንግሥት አማካሪዋ እቅጩን ነግሯቸዋል። እሸቱ ሆማ ቀኖ በበኩሉ ተከታትሎ ካጋለጣቸው  በርካታ ኅጸጾች መካከል ለአብነት አንዱን እንዲህ ይጠቅሳል።

«አንድ ትንሽ ቀላል ምሳሌ ልንገርህ። ባለፈው በኢትዮጵያ 2007 አቆጣጠር ሐምሌ አካባቢ የፋና ብሮድካስቲንግ ምን የሚል ዜና ሠርቶ ነበር? በዚህ በአሉቶ  ላንጋኖ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በ2 ቢሊዮን ብር ወጪ ተሠርቶ ኃይል ማመንጨት ጀመረ የሚል ዜና ተሠርቶ ነበር ሐምሌ ላይ 2007 ዓም ከዛ በኋላ ከሁለት ዓመት በኋላ ባለፈው መስከረም ወር  በዚሁ ጉዳይ ላይ ዜና ሠሩ። ያ ዜና ግን ምንድን ነው የሚለው?  የአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት  ኃይል ማመንቻ ፕሮጀክት በቅርቡ ሥራ ሊጀምር ነው  የሚል ዜና ነው የሠሩት።  እንግዲህ ማየት ትችላለህ። ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ ጀመረ የተባለለት ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ  ሊጀምር ነው የሚል አይነት ዜና ተሠራ። እና እንዴት እንደዚህ አይነት ነገር ሊሆን ይችላል? ሥራ ከጀመረ በኋላ ተቋርጦ ነው የሚል ሐተታውን ወደ ውስጥ ብትገባ  እንደዛ እንኳን የሚል ነገር የለውም። ልክ እንደምንም ያኛውን የድሮውን ዜና ምንም እንዳልተሠራ ተደርጎ  ተቆጥሮ እረስተውት ነው እንደ አዲስ ይሄንን የሠሩት። እና እንዲህ አይነት ነገሮች በጣም ብዙ አሉ።»

Screenshot Eshetu Homa Keno Facebook
ምስል Facebook/Eshetu Homa Keno

እሸቱ ሆማ ቀኖ የጀመረው የተጣረሱ መልእክቶችን የማጋለጥ ሒደት ከፍ ወዳለ ደረጃ ሲደርስ ሐቅን ወደ ማጣራት ይሸጋገራል። አሜሪካን ሀገር ሐቅን ማጣራት በሚል የተቋቋሙ ተቋማት ያለአንዳች ገደብ ይንቀሳቀሳሉ። ከእነዚህ ተቋማት መካከል ሐቅን ማጣራት (fact check) የተሰኘው ይገኝበታል። ይህ ተቋም በአብዛኛው የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ጋዜጠኞች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የመገናኛ አውታር ባለሞያዎችን በአባልነት ያሠራል። ተጋባዥ ጋዜጠኞችን እና ጸሐፍትንም ያሳትፋል።  ጥልቅ በሆነ ምርመራ እና ክትትልም ፕሮፓጋንዳዎችን እና ቅጥፈቶችን በተጨባጭ መረጃ እና ሐቅ ያጋልጣል። እሸቱ ወደዚያ ከፍ ያለ እርከን ለመሻገር ከወዳጆቹ ጋር እየተነጋገረ ነው።

«አሁን ባለው ኹኔታ እንዲሁ ጊዜ ባገኘሁ ቁጥር እየሠራሁ  ነው፤ ግን የእኔን የጽሑፍ መልእክቶች ከሚያነቡ ሰዎች ብዙ  አስተያየቶችን እየተቀበልኩ ነው። አሁን አስተያየቶቹን ከሰማሁ በኋላ ለምንድን ነው በተደራጀ መልኩ  ቢያንስ ብዙ ሊረዳው ወይንም ብዙ ሰው ሊደርሰው በሚችል መልኩ ይኼን ነገር ማስኬድ የሚቻል ከሆነ በሚል አንዳንድ ሐሳቦች ሰዎች እየሰጡኝ ስለሆነ  ቢያንስ ቢያንስ የሆነ መስመር ያለው ነገር ሆኖ  ይህንን ነገር ሥራዬ ብለው መከታተተል ለሚፈልጉ ሌሎች ሰዎችም እንደ ምሳሌ እንደ ማሳያ ሊሆን ይችላል በሚል ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር በመሆን አንዳንድ ነገሮችን እያሰብን  ነው። እና  ምናልባትም በቅርብ ጊዜ ወይ  በድረ-ገጽ መልኩ በውጪው ዓለም እንደምናየው ሐቅ ማጣራት (fact checking) ድረ-ገጽ አይነት ተቀርጾ ብቻ ውሳኔ ላይ ባንደርስም  በዛ መልኩ እያሰብንበት እንደሆነ ነው በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው።»

እሸቱ በጋዜጠኝነት ትምኅርት ወይንም መደበኛ ልምምድ ባይኖረውም የመገናኛ አውታሮችን  እየተከተለ ኅጸጾችን መንቀስ የጀመረው ግን ገና ከልጅነቱ አንስቶ ነው። አሁን ሥራዬ ብሎ በግሉ ለተያያዘው ሐቅን ፍለጋ ጥረት ሕግ ማጥናቱ ብቻ መነሻ እንዳልሆነው ይናገራል። 

«ዋናው ነገር ከልጅነቴ ጀምሮ ትምህርት ቤት ገብቼም ከትምኅርት ቤት ከወጣሁም በኋላ ሚዲያዎችን የመከታተል ዝንባሌ ነበረኝ። እና በሀገሪቱ ውስጥ የሚደረጉ ነገሮችን በመንግሥት የመገናኛ አውታር፤ ድሮ በአብዛናው በሬዲዮ ነበር የምትሰማው። እና ከምታየው ነገር ጋር የማይገኛኙ ነገር ሲሆኑብህ የበለጠ ፍላጎቱ እያደረብኝ መጣ እንጂ ፍርድ ቤት ውስጥ ወይንም ሕግ ትምኅርት ቤት መሄዴ ብቻውን ያመጣው ነው ብዬ አላስብም።»

የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምኅርት አጠናቋል እሸቱ። ኢትዮጵያ ሳለ ከረዳት ዳኝነት አንስቶ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውስጥ የሲቪል እና ሥራ ክርክር የሚባሉ ችሎቶች ውስጥ በዳኝነት ለአራት ዓመታት ግድም ሠርቷል። ቤልጂየም ተጉዞም በመልካም አስተዳደር እና ልማት ሁለተኛ ዲግሪውን አጠናቋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማቅናት ለሁለተኛ ዲግሪዉ ያጠናው የዓለም አቀፍ ሕግ ትምኅርት ነው። የጋዜጠኝነት መርኆዎችን ግን ያጠይቃል። 

Screenshot Eshetu Homa Keno Facebook
ምስል Facebook/Eshetu Homa Keno

«ጋዜጠኛ ስትሆን መጠየቅ አለብህ። አንድ ሁልጊዜ የምትገርመኝን ነገር ልንገርህ። በዚሁ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ነው የሆነው። ምንድን ነው ያሉት? በደቡብ ክልል 21 ሚሊዮን ሔክታር  መሬት በደን ተሸፈነ የሚል ዜና ሁሉም ሠሩ።  ኢ.ዜ.አ.ም ሠራው፤ ፋናም ተቀበለው፤ ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን  ጉዳዮች ሚንሥትር ፖስተር ሠርቶ ሁሉ ፌስቡክ ላይ ለጠፈው።  21 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በደን ተሸፈነ ብሎ። በጽሑፍ ነው ይሄን የገለጡት እና ዞር ብዬ እንዴት ነው ይኼ ነገር 21 ሚሊዮን ሊሆን የሚችለው? የደቡብ ሕዝቦች  ክልል ራሱ ጠቅላላ የቆዳ ስፋቱ በሔክታር  ከ12 ሚሊዮን አይበልጥም። እና በምን ስሌት ነው 21 ሚሊዮን ሔክታር በደን ተሸፈነ  ሊባል የሚችለው?...ይኼ የሚያሳይህ ሥራዬ ብለው፤ ሆን ብለው የሚሠሩት ፕሮፓጋንዳ ስለሆነ ብቻ ነው። ይኼንን ነው እኔ ጊዜዬን ወስጄ ለማሳየት የምሞክረው።»

መሰል ችግሮች በመንግሥት መገናኛ አውታሮች ላይ ጎልተው ይውጡ እንጂ፤ የመንግሥት ያልሆኑት ከኅጸጽ የጸዱ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ተናግሯል። ወደፊትም አቅም ሲገኝ እነሱ ላይም ክትትል እናደርጋለን ብሏል። 

«በሚዲያ በኩል የመንግሥት ላይ ያተኮርኩበት ምክንያት ትልቁ ጉዳት እየደረሰ ያለው በመንግሥት በመንግሥት ሚዲያዎች ላይ ነው ብዬ ስለማምን እንጂ ሌሎች ሚዲያዎችም እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ አልገቡም  በሚል አስተሳሰብ አይደለም። የሚቻል ከሆነ ሁሉንም ሚዲያ፤ እኔ ሁሉም ሰው ተጠያቂ  ሆኖ ትክክለኛውን እና ለእውነት በጣም የቀረበውን መረጃ ብቻ ለህዝብ እንዲሰጥ   የሚል እምነት ነው ያለኝ። እና ይሄ ማለት ሌሎች ከመንግሥት ጋር ንክኪ የሌላቸው ሚዲያዎች ከእዚህ ነጻ ናቸው እና  እኔም ልከታተላቸው ሌሎችም ሊከታተሏቸው አይገባም  የሚል ነገር ውስጥ አልገባም። ስለዚህ በተቻለ መጠን ሁሉንም  ሽፋን ለመስጠት  እንሞክራለን። ግን አሁን ባለን አቅም መንግሥት እና ከመንግሥት ጋር ተያይዘው የሚሠሩ ሚዲያዎች ላይ ነው  ለጊዜው ትኩረት እያደረግን ያለነው።»

ሐቅን የማጣራት ሥራ ጊዜን፤ ጉልበትን እና ገንዘብን በማስወጣት ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠይቃል። ይኽን ኃላፊነት ለመወጣት እሸቱ በግሉ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰነባብቷል። ምናልባትም እንዳሰበው ሆኖሎት በተደራጀ መልኩ ከፍ ወዳለ ደረጃም ያሳድገው ይኾናል። 
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ