1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች እሮሮ

ዓርብ፣ ነሐሴ 4 2010

ላለፉት ሦስት ዓመታት ሊቢያ ውስጥ የሚገኙ ከኢትዮጵያ፤ ኤርትራ እና ሶማሊያ የተሰደዱ ከ150 የሚበልጡ ወገኖች ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ አመለከቱ። ተሰዳጆቹ እንደሚሉት ወደ አውሮጳ ለመሻገር ከ150ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር ለሕገ ወጥ አሸጋጋሪዎች ከፍለዋል።

https://p.dw.com/p/32zJJ
Algerien, Niger &  Libyen | Thema Flüchtlinge in der Sahara
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

ወደ አውሮጳ ለመሻገር እስከ 200 ሺህ ብር ከፍለዋል

 በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ስር ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ለዶይቼ ቬለ የገለፁት እነዚህ ወገኖች በዚህ ሁኔታ ለሦስት ወራት ቢቆዩም ከየትኛውም ወገን አንዳች መፍትሄ በማጣታቸው በመላው ዓለም ያለ ወገን ይድረስልን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አላማቸው ሩቅ ነው፤ ሰው መዋጥ የለመደበትን ሜዲትራኒያን ባህር በሆነ ተአምር ተሻግረው አውሮጳ መግባት። ለዚህም በተደጋጋሚ ለሕገ ወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ ከፍለዋል። የበረሃ ሐሩር አሸዋውን ፣ ከውኃ ጥም እና ጠኔው ጉዳት ጋር ተጋፍጠው ሞትን ለጥቂት አምልጠው ሊቢያ ቢገቡም የረጋ መንግሥት ካጣች ዓመታት የተቆጠሩባት ሰሜን አፍሪቃዊት አረባዊት ሀገር የምድር ሲኦል ሆኖባቸዋል። ኤርትራዊው እና ኢትዮጵያው ተሰዳጆች እየተቀባበሉ ችግራቸው ለማስረዳት ይጥራሉ። እነሱ እንደሚሉትም ለረዥም ጊዜ በዚህ ስቃይ ውስጥ መቆየታቸው ሞትን እንዲጋፈጡ ገፋፍቷቸዋል።

በታሰሩበት ምድር ቤት ቁጥራቸው በርካታ ሆኖ ተፋፍገው በረሃብ እና ጥም መሰቃየቱ ሲጠናባቸው በአድማ ወሰድነው ባሉት ርምጃ ካሉበት ወጥተው እነሱ በድንጋይ አጋቾቻቸው በጥይት ተፋልመው፤ የተጎዱ ተጎድተው ቀሪዎቹ በመሰባሰብ በአቅራቢያቸው መስጊድ ውስጥ በመግባት ሙጥኝ ይላሉ። ከዚያም የUNHCR ባልደረቦች መሆናቸውን የገለፁላቸው አካላት ወደ አንድ መጠለያ እንደወሰዷቸው እና ቢጫ ወረቀት እንደሰጧቸውም ገልጸዋል።  

Mittelmeerroute - Flüchtlinge im Boot
ምስል picture-alliance/dpa/AP/E. Morenatti

ወደ አውሮጳ እናሻግራችኋለን በማለት ገንዘብ በየጊዜው እንዲከፍሏቸው ከሚያሰቃዩዋቸው አረመኔዎች እጅ በሞት ሽረት ፍጥጫ መላቀቃቸውን የሚናገሩት እነዚህ ወገኖች ከትሪፖሊ ብዙም አይርቅም ባሉት ቀሲር ቢን አል ቀሺር በተባለ ስፍራ ወደሚገኝ እነሱ እስር ቤት ወዳሉት የማቆያ ጣቢያ ካዛወሯቸው በኋላ የUNHCR ባልደረቦችንም አይተዋቸው እንደማያውቁ በምሬት ዘርዝረዋል። ከዛሬ ነገ ም ወደ ሌላ ስፍራ እንዛወራለን በሚል ተስፋ ለሦስት ወራት ተመልካች ማጣታቸውንም ያስረዳሉ። ከሕገ ወጥ ሰው አሸጋጋሪዎቹ  እጅ መትረፋቸውን እንደ አንድ ጥሩ ነገር ቢቆጥሩትም አሁን ባሉበትም የሊቢያ ፖሊሶች ዱላ አልቀረላቸውም።  እነዚህ ተሰዳጆች የሊቢያ የባህር ጠረፎች እንደበፊቱ በቀላሉ እንደማይታለፉ ከፍተኛ ጥበቃ እንዳለባቸው ያውቃሉ፤ ግን UNHCR መንገድ አያጣም ባዮች ናቸው። ዛሬ ዕለቱ ዓርብ በመሆኑ እና በሊቢያ የሥራ ቀን ባለመሆኑ ጉዳዩን ያውቃል የተባለውን የUNHCR ቢሮ በስልክ ለማነጋገር ያደርግነው ጥረት አልተሳካም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ