1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሠራተኞች፣

ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2005

ዛሬ በመላው ዓለም ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች በከባድ ሥራ እንዳይማቅቁ የሚከልክለው ደንብ የሚታሰብበት ዕለት ነው። በዓለም ዙሪያ በ 10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጆች፤ በቤት ሠራተኝነት ፤ የባርነት ቀንበር ተጭኖባቸው እንደሚማቅቁ፣ የተባበሩት መንግሥታት

https://p.dw.com/p/18oUj
ምስል Roberto Schmidt/AFP/GettyImages

 ፣ ዓለም አቀፉ የሥራ  ድርጅት(ILO) አስታወቀ። ለአካለ መጠን ካልደረሱት ልጆች ሠራተኞች መካከል፣  ከሞላ ጎደል ¾ኛዎቹ ልጃገረዶች ናቸው። ዛሬ ታስቦ ስለዋለው መታሰቢያ ዕለትና ስለልጆች ሠራተኞች ፍዳ -...

በያመቱ ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያት፣  18 ዓመት ያልሞላቸው  ልጃገረዶች ጭምር፣ በሐሰት ሰነድ ዕድሜአቸው ከፍ እንዲል እየተደረገ ወደ ዓረቡ ዓለም እንደሸቀጥ ዕቃ ይጋዛሉ። በዚያም ዘመናዊ ባርነት ነው የሚጠብቃቸው። የተባበሩት መንግሥታት ፣ ዓለም አቀፉ የሥራም ሆነ የሙያተኞች ድርጅት (ILO) እንዳብራራው፤ ብዙዎቹ ለጋ ወጣቶች፤ በቀጣሪዎቻቸው ቤት የሚሰጣቸው ሥራ፤ ማጽዳት፤ ልብስ መተኮስ፤ ምግብ ማብሰል ፣የጓሮ አትክልተኛ መሆን፤  ውሃ መቅዳት፤ ልጆችን መጠበቅ፤ እንዲሁም ሽምግሌዎችንና ባልቴቶችን መንከባከብ ነው። ከቤተሰባቸው ተለይተው በካባድ ሥራ የሚሠቃዩት ለጋ ወጣቶች፤ ድብደባና ዛቻ ብቻ አይደለም የሚያጋጥማቸው። አስገድደው በሚደፍሩም  አሠቃቂ ወንጀል ይፈጸምባቸዋል።

Iran Kinderarbeit Nouruz
ምስል Privat

በሄይቲ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ልጆች፤ ከአሠቃቂው  የምድር ነውጥ የተረፉት ጭምር ፣ከባርነት በማይሻል ሁኔታ በተለያዩ ቤቶች ተቀጥረው ደፋ ቀና ይላሉ። በቡርኪና ፋሶ፤ ጋና ፣ አይቮሪ ኮስትና ማሊ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ። በፓኪስታንና ኔፖል ከከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች፤ በአራጣ ብድር  እጅግ የሚቸገሩ ቤተሰቦች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቻቸውን ባባዕዳን ቤቶች ተቀጥረው  በከባድ ሥራ እንዲጠመዱ ያደርጋሉ። በዓለም ዙሪያ ምን ይህል ልጆች የዚህ እኩይ ዕጣ ሰለባዎች እንደሆኑና የዛሬው መታሰቢያ ዕለት መልእክት ምን እንደሆነ፣-- ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች እንዳይሠሩ ILO የሚያካሂደው የዘመቻ መርኀ ግብር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ኮንስታንስ ቶማስ  እንዲህ ይላሉ።

Blut Diamanten aus Sierra Leone
ምስል picture-alliance/dpa

«እንደምንገምተው፤ 15 ሚሊዮን ያህል እንዲያውም ወደ 16 ሚሊዮን የሚጠጉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች በከባድ ሥራ ይማቅቃሉ። አብዛኞቹ ልጃገረዶች ናቸው። ይህ በቤት ውስጥ በሚከናወን ሥራ ጉልበታቸው አለቅጥ የሚበዘበዝ ልጆች መሆናቸው ነው። በዚህ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች በከባድ ሥራ የሚማቅቁበት ሁኔታ እንዲወገድ ለዓለም በመላ ማሳሰቢያ በሚቀርብበት ዕለት ሰፋ ያለው ዘመቻ አካላ የሆነው ጉዳይ በቤት ውስጥ የሚሠራውም የሚመጥን እንዲሆን ፣ ጥብቅና መቆም ተፈላጊ መሆኑን ነው ለማስገንዘብ የምንፈልገው።»

Indien Kinderarbeit Betteln
ምስል DW

በዓለም ዙሪያ ፣ የልጅ አሽከሮች ወይም ሎሌዎች ከሚሰኙት መካከል 6,5 ሚሊዮኑ  ዕድሜያቸው በ 5 እና 14 ዓመት እርከን ላይ ነው። ይህ እጅግ አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን፣ ኮንስታንስ ቶማስ እንዳብራሩት ፣ ለብዙዎቹ ሃገራት ብሔራዊና ዓለም አቀፍ የልማት ግብም እንቅፋት ነው።

 በዓረቡ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያቱን ልጃገረዶች ፍዳ ፣ ድርጅታቸው እስከምን ድረስ አጢኖበት እንደሆነም  ተጠይቀው ---

«የኢትዮያውያቱን ጉዳይ በተመለከተ   ዝርዝሩን አላውቀውም፤ ግን ብዙ አገሮች ፤ ሴቶችና ወንዶች ዜጎቻቸውን ፤ ለሥራ ወደ ዐረብ አገሮችና ወደሌሎች አማላይ ሃገራት እንደሚልኩ አውቃለሁ። ይህ እጅግ የሚያሳስብ ነው። በፍልሰት የሚገቡ የባሰ ግፍ ነው የሚፈጸምባቸው።  በተለይ  በዐረብ አገሮች የሚገኙ የውጭ ተወላጆች የሆኑ ሠራተኞችይዞታ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ እናምናለን። እነዚሁ አገሮችም፣ በየቤቱ ተቀጥረው የሚሠሩ ሰዎችን  ይዞታ በጥሞና መፈተሽ ይገባቸዋል። እኛ አበክረን  ጥረት የምናደርገው፤ የለጋ ወጣቶችን  በሥራ መሠመራት የሚከለክለው ደንብ  እንዲጸድቅ ለማድረግና  አዲሱ ስምምነት ግንዛቤ እንዲያገኝ ነው።»

Kinderarbeit in Goldminen in Burkina Faso
ምስል DW

የለጋ ወጣቶችን  ሁለንተናዊ  ጤናማ   ዕድገት  በመከታተል፤ በካባድ ሥራ ተጠምደው አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው፤ በአጠቃላይ ለጋ ወጣቶችን ማሸቀል እንዲገታ ምን መደረግ አለበት ፤ ኮንስታንስ ቶማስ ---

«በመጀመሪያ ማድረግ ያለብን ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ቀጥሮ ማሠራት ሊከለከል እንደሚገባ ፣ እያንዳንዱ ግንዛቤም ሆነ እይታ እንዲኖረው ለማብቃት መጣር ነው። ግን የቤት ሥራን የሚመለከት አይመስላቸውም። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ፣ ተቀጥረው በሥራ እንዳይጠመዱ  ማለት ፤ በቤት ውስጥ በሚከናወን የሥራ ዓይነትም እንዳይሠማሩ ማለት ነው።» 

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ