1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለተበዳሪ ሃገራት የሚደረገው የብድር ስረዛ

sdestaሐሙስ፣ መስከረም 13 1997

ቡድን ሰባት በመባል የሚጠሩት በእንዱስትሪ የበለፀጉት ሃገራት በመጪው ሳምንት ሲሰበሰቡ የዕዳ ስረዛ ውሳኔ እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል ። ይህንን ዕቅድ የሚደግፉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ለድሃ ሃገራት የተሰጠው ብድር ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ይገኛሉ

https://p.dw.com/p/E0fN

ከተጀመረ ስምንት ዓመት ባስቆጠረው እና ዕዳ የተቆለለባቸው ሃገራት እንዲቀነስላቸው በተነደፈው ዓለም አቀፉ መርሃ ግብር መሰረት እስካሁን ሃያ ሰባት ሃገራት የዕዳ ቅነሳ ተደርጎላቸዋል ። ከነዚሁ ሃገራት ከአንድ ቢሊዮን ዕዳ ውስጥም ወደ ሰላሳ ቢሊዮኑ ዕዳ ተቀናሽ ሆኗል ። አብዛኞቹ ሃገራት የተበደሩትን ገንዘብ ለማህበራዊ አገልግሎት ከማዋል ይልቅ ብድርን ለመክፈል ይበደራሉ የሚሉት መንግስታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች አሁን ግን ይህ መቆም አለበት ይላሉ ። በዩናይትድስቴትስ እና በብሪታንያ የተደገፈው እቅድ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል ። ከነዚሁ መካከል አክሽን አፍሪካ ፣ ኦክስፋም እና የህክምና ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብት የተባሉት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይገኙበታል ።

የብድር ስረዛው እቅድ ዘግይቷል ያሉት የአክሽን አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ሳሊህ ቡከር እስካሁን የሚደረጉት የዕዳ ቅነሳዎች በቂ እንዳልነበሩ ይገልጻሉ ። በድሃ ሃገራት ላይ የሚቆለለው ዕዳ በተለይ በአፍሪካ የተስፋፋውን የኤች አይቪ በሽታ ስርጭት ከመቋቋም ይልቅ እያባባሰው ነው ብለዋል ። እሳቸው እንደሚሉት ሃገራቱ በሚያገኙት ገንዘብ የጤና ዘርፎችን እና አገልግሎቶችን ከማጠናከር ይልቅ ዕዳ ለመክፈል ይታትራሉ ። በመሆኑም ኤች አይቪ ኤይድስን ለማግታት የሚያደርጉትን ጥረት ያሳንሳል ። በድሃ ሃገራት ዘንድ ዕዳ ከሞት ጋር የተያያዘ ነው ያሉት የህክምና ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብት የዋሽንግተን ቅርንጫፍ ዳይሬክተርም ይህንኑ ሃሳብ ያጠናክራሉ ። ዳይሬክተሯ ሆሊ ቡርካሃልተር በድሃ ሀገራት ላይ የተጫነው ዕዳ በችግር ላይ ያለውን የጤና ዘርፍ ችግር ውስጥ ከቶታል ብለዋል ። ዕዳው ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ለሚጠይቀው ደብዳቤም ከመላው ዓለም የአንድ መቶ ሃምሳ የህክምና ዶክተሮች ፊርማ ተሰባስቧል ።

የዕዳ ስረዛውን የደገፉ ሌሎች ተሟጋች ድርጅቶችም የዕዳ ስረዛው በሰላሳ ሶስት ሃገራት ብቻ መወሰን የለበትም ይላሉ ። እቅዱ ሁሉንም ተበዳሪ ሃገራት እንኳን ባይመለከት ቁጥሩ መጨመር ይገባዋል ሲሉ ጠይቀዋል ። ተሟጋች ድርጅቶቹ የዕዳ ስረዛው ውሳኔ መስተጓጎል የለበትም ለማለት የተነሳሱት ጉዳዩ በይበልጥ በዩናይትድስቴትስ ተደግፎ በመቅረቡ ነው ። የፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ባወጠው ይፋ መግለጫ ለድሃ ሃገራት በተለይ ለኢራቅ የብድር ዕዳው እንዲነሳላት ፍላጎቱን አንፀባርቋል ። ኢራቅ ከአንድ መቶ ቢሊዮን በላይ የብድር ዕዳ አለባት ። የኢራቅ የብድር ስረዛ ጥያቄ በመጀመሪያ የቀረበው ባለፈው ሰኔ በጆርጂያ በተካሄደው የቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ በብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር በቶኒ ብሌር ነበር ።

የዕዳ ስረዛው እቅድ በዩናይትድስቴትስ እና በብሪታንያ ቢደገፍም ለውሳኔ ለመብቃት ግን ችግር ሊገጥመው እንደሚችል በመጠቆም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስጋታቸውን ይገልጻሉ ። የስጋታቸው ምንጭ እየተነሳ ያለው ተቃውሞ ነው ። አበዳሪ የገንዘብ ተቋማቱ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዕዳን ሙሉ በሙሉ መሰረዝ አስቸጋሪ መሆኑን በመግለፅ ላይ ናቸው ። እንደ እነሱ ምክንያት በአንድ በኩል የገንዘብ ተቋማቱን የማበደር አቅም የሚፈታተን ይሆናል ። በሌላ በኩል ደግሞ ተበዳሪ ሃገራቱም ያላቸውን የተጠያቂነት ድርሻ የሚሽረሽር ነው ። ከዩናይትድስቴትስ እና ከብሪታንያ ውጭ ያሉት የቡድን ሰባት አባል ሀገራትም ተመሳሳይ እምነት እና አቋም ያንጸባርቃሉ ። የቡሽ አስተዳደር የብድር ስረዛውን በመደገፍ የኢራቅን ዕዳ ለማሰረዝ ለሽፋን ይጠቀምበታል የሚል እምነትም አላቸው ። በመሆኑም ለኢራቅ ሙሉ በሙሉ የዕዳ ስረዛ ሊደረግላት አይገባም የሚል አቋም እንደያዙ ይነገራል ። በተለይ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ዣክ ሽራክ የዕዳ ስረዛ የሚያስፈልጋቸው የባሰባቸው ድሃ ሃገራት እያሉ ለኢራቅ ቅድሚያ ሊሰጣት አይገባም የሚል አቋም አላቸው ።

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የኢራቅ ወረራን ተከትሎ ከአትላንቲክ ወዲህ እና ከአትላንቲክ ማዶ ባሉት ሃገራት መካከል የነበረው ውጥረት በዕዳ ስረዛ ሳቢያ እንዳይባባስ በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል ። የብድር ስረዛውን እቅድ የደገፈው እና ‘’ ሃምሳ አመት ይበቃል ‘’ የተባለው ተሟጋች ድርጅት ይህንን ስጋቱን የገለፀው ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው በሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ። ድርጅቱ የገንዘብ ተቋማትን አበዳሪነት በመቃወም በየጊዜው ስሞታውን ያሰማል ። ይኸው ድርጅት አሁን ሊደረግ የታቀደው የብድር ስረዛ ልክ ብድር ለመስጠት ይቀርብ እንደነበረው ቅድመ ሁኔታዎች ሊበጅለት አይገባም ሲልም አሳስቧል ። ለሁሉም የዕዳ ስረዛው ዕቅድ የመጨረሻ ውሳኔ የቡድን ሰባት ሃገራት የገንዘብ ሚንስትሮች መስከረም ሃያ አንድ ሲሰበሰቡ ይለይለታል ።